(ክፍል ሁለት)
በአርትስ ቲቪ እሁድ 8:00 “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” በሚያቀርበው ፓለቲካዊ አስቂኝ ምጸቱ ከሳምንት ሳምንት ተወዳጅና በጉጉት ተጠባቂ እየሆነ የመጣው ተስፋሁን ከበደ (ፍራሽ አዳሽ) በዚያ ሰሞኑ እንደተለመደው በምጸት አርጩሜው ያለ ርህራሄ እንዲህ ሸንቆጥ አድርጎናል ። ዶሮ ፋንታ የሚባል ምግብ አለ ። እንደ ዶሮ ወጥ ሽንኩርቱ በዛ ተደርጎ ይቁላላና እንደ ምንቸት ወጥ የተፈጨ ስጋ ተጨምሮበት በአናቱ እንቁላል ሲዳላም ቅልጥም ከጎን ተጋድሞ በዶሮ ወጥ ቦታ የሚሰራ ። በዶሮ ፋንታ የሚቀርብ ።
እኛ እንዲህ አንድን ምግብ በሌላ መተካት እንጂ በስልጣን በሰላማዊ መንገድ መተካካት አናውቅም፤ ብሎን እርፍ ። በእኛው ድክመትና ሽንፈት ተሳለቀብን ። አሳለቀብን ። እኛንም አስቆ አሳቀቀን ። ፍራሽ አዳሽ እንደሸነቆጠን በሰላማዊ መንገድ መተካካት የአኬሊስ ተረከዛችን ፤ ስስ ብልታችን ነው ። ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አለማካሄዳችንም እውነት ነው።
በአጼ ሀይለስላሴ ፣ በደርግ ፣ በህወሀት/ኢህአዴግ የተካሄዱ የይስሙላ ምርጫዎች ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን ወይም መተካካትን አላመጡልንም ። የፍራሽ አዳሽ ጎሚ እዚህ ድረስ ሀቅ አለው ። የፊታችን ሰኔ እኩሌታ አካባቢ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው እኔ በአንጻራዊነት የመጀመሪያው ነጻና ተአማኒ ይሆናል የሚል ተስፋ ስላለኝ 1ኛ እናንተ 6ኛ የምትሉት ሀገር አቀፍ ምርጫ በተቻለ መጠን ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የለውጥ ኃይሉ የሄደበትን ርቀት እያየን ነው ። በሱማሊያና በኦሮሚያ ክልሎች ከሚቀርቡ አቤቱታዎችና በአዲስ አበባ የመራጮች ምዝገባ አልፎ አልፎ ከተስተዋለው መዝረክረክ በስተቀር ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ምርጫውን ስኬታማ በማድረግ ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና እንድትወጣ እንተጋለን ሲሉ ደግመው ደጋግመው ቃል ኪዳን /covenant /አስረዋል ። ብልጽግና ከተሸነፈ ተጨባብጦ ለአሸናፊው ፓርቲ ስልጣኑን ያስረክባል ። ተፎካካሪ ፓርቲ ይሆናል በማለት ያለ ምንም ማቅማማት ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ጋር ቃል ኪዳን ፈጥመዋል ።
ልብ አርጉ ሊሻሻል አልያም ሊሻር የሚችል ውል ወይም ኮንትራት አይደለም ። የማይታጠፍና የማይሻር ቃል ኪዳን እንጂ ። ፓርቲያቸው ብልጽግና በ50+1 ካሸነፈ ደግሞ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብሮ ይሰራል ሲሉ መተማመኛ ሰጥተዋል ። መቼም ይህ ቁርጠኝነት በሀገሪቱ ታሪክ ፋና ወጊ ሆኖ የሚጠቀስ ነው ። ሆኖም ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና ትወጣለች ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል ። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትርም ሆኑ ብዙዎቻችን ተስፋ ያደረግንበት ይህ ምርጫ በባዶ ተስፋ ላይ ያነጣጠረ ዝምብሎ ተስፋ አይደለም ። ባለፉት ሶስት አመታት በተከናወኑ ተጨባጭ ተግባራት ላይ የታነጸ እንጂ ።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ወደ ኃላፊነት ያመጣው ለውጥ ከቀደመው አብዮትም ለውጥም ፍጹም ይለያል ። ደርግ ንጉሳዊውን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግስት ገርስሶ በምትኩ የባሰ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ተከለ ። ትህነግ/ኢህአዴግ ሶሻሊስታዊ አምባገነን ገዥ የነበረውን ደርግ ለ17 አመት ነፍጥን ከሴራና ደባ አጃምሎ ለስልጣን ቢበቃም ታገል ሁለት ያለው እኩልነትና ነጻነት ክዶ የአንድን አውራጃ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ለ30 አመታት አንድም ቀን የመንግስትነት ባህሪ ሳያሳይ በአሳፋሪ ሁኔታ ራሱን በራሱ አጥፍቷል ። መንግስት የመሆን ቅን ፍላጎትም አልነበረውም ። ሕገ መንግስት ያለው ብቸኛ ማፊያ ቡድን እንጂ ። በመጨረሻዎቹ የክህደትና የአረመኔነት ቀናት ያረጋገጠልን ይህን ማፊያነቱን ነበር ።
ሆኖም በፓለቲካው መልክዓ የነዛው የጥላቻ ፣ የልዩነትና የመጠራጠር መርዝ በቀላሉ አይረክስም ። እንኳን ለ46 አመታት የተለፈፈ የጥላቻና የፈጠራ ትርክት ፤ በጣሊያን የአምስት አመታት ቆይታ ለዛውም በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ለአንድ ቀን እንኳ ያለስጋት ውሎ ባላደረበት ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው የዘራው የማንነት ጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት በቀላሉ ሰኮናው ሳይነቀል ኖሮ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶሻሊዝም ጋር ተላቁጦ የሀገራችንን ፓለቲካ እስከመበየን ደርሷልና ከዚህ አባዜ ሰብሮ ለመውጣት ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል ።
ይህ ጥረት ግን የአፄ ሀይለስላሴ ፣ የደርግና የትህነግ አገዛዞች ያባከኗቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች ሀገራችንን ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳስከፈሏት በውል ተገንዝቦ ከሶስት አመት ወዲህ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ በብልህነትና በአስተዋይነት መጠቀምን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግን ይጠይቃል ። እዚህ ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ለሚመራው የለውጥ ኃይል ከእነውስንነቶቹ ያለንፍገት እውቅና ሊቸረው ይገባል ። ይሁንና ይቺ ሀገር እንደ ቀደሙት ሶስት የቅርብ አመታት መታጠፊያዎች የምታባክነው እድልም ሆነ አጋጣሚ እንደማይኖርና እንደ ከዚህ በፊቱ ብታባክነው አምባገነናዊ አገዛዝ በመተካት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገር ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን መሆኑን በውል ተገንዝበው የአምባገነንነት ቀለበቱን ሰብሮ ለመውጣት የሚያግዝ ስልት ተልመዋል ።
አሳታፊ ፓለቲካዊ ስርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፓሊሲ ለማስፈን ቆርጠዋል ። እንገጭ እገው እንዳለ ። ቁርጠኝነታቸውንም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና ኢኮኖሚውም ፍትሐዊ እንዲሆን ማሻሻያ ቀርጸው ወደ ትግበራ ገብተዋል ። ሆኖም ለውጡ ከቀደሙ አብዮቶቹም ሆነ ለውጦች በፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተለየ በመሆኑ ፤ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ልዩነትና ጥላቻ ፤ ትህነግ ጥርሱን በነቀለበት ሴራና ደባ መቐሌ ላይ መሽጎ እንዲቀጥል ጊዜ ማግኘቱ ፤ ለውጡ ቢያንስ ሆን ተብሎ የባረቁ ሶስት ለውጦችና አብዮት ዘርፈ ብዙ ቀውስን እንደ ትኩስ ድንች ተቀባብለው ተቀባብለው የጣሉበት ባለዕዳ በመሆኑ የቀውሶች ቋጥኝ ስለ ወደቁበት እና በለውጡ ተዋንያን ወጥ ቁርጠኝነት ባለመያዙ ምልዑ – በኩሌ ሳይሆን ቀርቷል ። ምንም እንኳ የእውነተኛ ለውጥ መንገድ አሚካላና ኩርንችት የበዛበት ቢሆንም የተገኘው አበረታች ውጤት በዚህ ሁሉ እሾህ ታንቆ ያለፈ እንዳይመስል አድርጎታል ።
እንደ መውጫ
የዐቢይ መንግስት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አዕማድ የሆኑ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት ማሻሻያዎችን አድርጓል ። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፣ የፍትህና የዳኝነት ስርዓቱ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽን ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ፣ የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ ተቋም ፣ ፌደራል ፓሊስ ፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ ወዘተረፈ ላይ የተፈጠሩ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጦችን በአብነት ማንሳት ይቻላል ።
የለውጥ ኃይሉ በምርጫ ዋዜማ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፤ ክብርት መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፤ አቶ ዳንኤል በቀለን (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት መሾሙ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በዴሞክራሲ ፣ በፍትሕ ፣ በእኩልነትና በነጻነት ለመዋጀት የቆረጠ መሆኑን ያረጋግጣል ። የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዕማድ የሆኑ እነዚህን ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎች ገለልተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት የለውጥ ኃይሉ ሀገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አርነት ለማውጣት መወሰኑን በተግባር አረጋግጧል ።
የለውጥ ኃይሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በአደረጃጀትና ገለልተኛ አመራሮችን ከመመደብ ባሻገር የትህነግ አገዛዝ ለአፈና መዋቅሩ እንደ መሳሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሕጎች በገለልተኛ ምክር ቤት እንዲሻሻሉ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል ። የሲቭል ማህበራት ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣ የጸረ ሽብር ፣ የአስተዳደር ፣ የምርጫና የፓለቲካ ድርጅቶች አዋጆች የተሻሻሉ ሲሆን ቀሪዎችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው ። እነዚህ የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ ያሉት ለዚህ ተግባር በገለልተኝነት በተቋቋመ ምክር ቤት መሆኑ ፤ የምክር ቤቱ አባላትም በገለልተኝነታቸው የታወቁ ምሁራን ፣ ጠበቃዎችና የሙያ ማህበራት መሆናቸው ፤ በሕግ ማሻሻያ ሒደቱ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች የሙያ ማህበራትና የሕዝብ ወኪሎች በሒደቱ በንቃት መሳተፋቸው ሌላው የለውጥ ኃይሉ አካታች የፓለቲካ እና አሳታፊ የኢኮኖሚ ስርዓት ለመትከል ምን ያህል እንደ ተነሳሳ እማኞች ናቸው ።
የለውጥ ኃይሉ ሀገራችን ድሀ ፣ ኋላቀርና አምባገነናዊ አገዛዝ ሲፈራረቅባት የነበረው ተረግማ ወይም ሕዝቧ ጥቁር ስለሆነ ሳይሆን አሳታፊና አካታች ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ባለመከተሏ መሆኑን በመገንዘብ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት ላለማባከን ቃል ኪዳን ገብቶ እየሰራ ይገኛል ። ሀገራችንን ለዘመናት ቀስፎ የያዛትን ችግር ለይቶ ለማያዳግም መፍትሔ እየሰራ ነው ። በዚህም ስሙ በፋና ወጊነት ሲወሳ ይኖራል ። ምርጫው ነጻ ፣ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ማለቱም አበክሮ የፈጠረውን መደላድል ታሳቢ በማድረግ ነው ። ምርጫው ኢትዮጵያ የምታሸንፍበት ነው ያለውም ወሳኝ መታጠፊያውን በአግባቡ ትጠቀማለች ብሎ ስለሚያምን ነው ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም