በኢትዮጵያ ባህል የቆዳ ውጤቶች በተለይ በገጠሩ ክፍል ለመኝታ ፣ ለስልቻ፣ ለፈረስ ኮርቻና አለንጋ፣ ለአህያ እህል መጫኛ ጠፍር ፣ለልብስ፣ የጠፍር ጫማ ያገለግላል። የበግ ቆዳም ለድብዳብ እንዲሁም አገልግል ሲሰራ ለመሸፈኛነት ይውላል። መሶብና እርቦ ጫፋቸው ዙሪያቸውን በቆዳ ተደርጎ ይሰፋል ። በብርዳማ አካባቢዎች እረኞች የበግ ለምድ ለብሰው ክብርድ እራሳቸውን ይከላከላሉ። የብራና መጽሐፍት የሚዘጋጁትም ከፍየል ቆዳ ነበር።
አሁን ላይ ደግሞ የቆዳ ውጤቶች በተለየ መልኩ ተፈላጊ ናቸው። ለዘመናዊ አልባሳትና ለፋሽኑ ዓለም መዘነጫነት ይፈለጋሉ። አቶ ጌታቸው አድኃና በቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት 12 ዓመት አገልግለዋል። በዲዛይንና በተለያዩ ሙያዎች በማሰልጠን በአሰልጣኝነትም ሰርተዋል። አሁን ደግሞ በኢንስቲትዩቱ የቆዳ አልባሳትና ዕቃዎች ኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ በዳይሬክተርነት እያገለገሉ ይገኛሉ። የፋሽን አምድ ዝግጅት ክፍል የቆዳ ውጤቶች በዲዛይንና በፋሽን ዘርፍ ያላቸውን ተፈላጊነትና ተያያዥ ጉዳዮች በተለይ ደግሞ ኢንስቲትዩቱ ያለውን ሚና አስመልክቶ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸው ነበር።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኢንስቲትዩቱ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ስልጠና ብቸኛው የመንግሥት ተቋም እንደመሆኑ መጠን በርካታ ሰዎችን በቴክኒክና ሙያ (በአጭርና ረጃጅም) ሥልጠና፣ በዲግሪ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪን (ማስተርስ) ብቁ ባለሙያዎችን እያፈራ የሚገኝ ተቋም ነው። በሙያው ሠልጥነው ቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ የተቀጠሩ፣ ሥራ ፈጣሪ የሆኑ፣ ይገኙበታል። ይህም ዘርፉን ከማንቀሳቀስ አንፃር ትልቅ ፋይዳ አለው ሲሉ አቶ ጌታቸው ያስረዳሉ።
“የተቋሙ ሠልጣኞች ብቃታቸው አስተማማኝ ስለሆነ በገበያ ደረጃ ፋብሪካም እንኳን ባይሆን በራሳቸው ደረጃ አንድ ማሽን ገዝተው በራሳቸው ሥራ ፈጥረው ይሰራሉ” የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ተፈላጊ ችሎታ ያላቸው ባለሙያ እንደሚያፈራ ይገልፃሉ። አብዛኛውን የቆዳ አልባሳት ጫማዎችና ቦርሳዎች ሞዴልና ዲዛይን የሚያወጡት የኢንስቲትዩቱ ሠልጣኞች መሆናቸውን በመጥቀስም ለውጤታማነታቸው ምክንያት የትምህርት ጥራቱና የስልጠና ዘዴው መሆኑን ያስረዳሉ።
አሁን ላይ ህብረተሰቡ ለቆዳ ውጤቶች ፋሽንና ዲዛይን ያለው አመለካከት ተለውጧል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። አዲስ ሞዴል ጫማ ወደ ገበያ ሲመጣ ሰው ተረባርቦ ይገዛዋል፤ እንደፋሽን ይጠቀምበታል። በተለያየ ቅርፅና ዲዛይን የቆዳ ውጤቶች ማምረት ካልተቻለ ኅብረተሰቡ ምርቱን እንደ አሮጌ ቁና ያጣጥለዋል፣ ይጥለዋል። ሻጩ ያለው አማራጭ በርካሽ ዋጋ አውጥቶ መሸጥ ወይም መጣል ሊሆን ይችላል። የቆዳ ምርቱ ቦታም ይዞ ገበያውም ቀዝቅዞ እንዳይወድቅ አምራቹና ሻጩ የግድ አዳዲስ ዲዛይን ምርቶችን ያወጣሉ፤ የዚያኔ ፋሽን ይሆንና ገበያውን ይቆጣጠራሉ በማለት በየጊዜው ስለሚሻሻለው የምርት ሂደት ያስረዳሉ።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከፋሽን ከመከተል አንፃር የቆዳ ምርቶች ገበያ ደርቷል፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ የተመረተን ጫማ ከ700 እስከ 3ሺ ብር ድረስ እስከ 3ሺ500 አውጥቶ ይገዛል። እስከ 6ሺ አውጥቶ ቦርሳ ሊገዛ ይችላል። ይህ ደግሞ ጥራት ዲዛይንና ፋሽን ተከትሎ የመጣ ነው።
በዘርፉ የሥራ ዕድልም ተፈጥሯል። ባለሙያዎቹ የፈጠሯቸው ዲዛይኖች ምን ያህል ከውጭ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ እንደሆኑ ማሳያ ናቸው። ፒያሳ፣ 22፣ መገናኛ ፣ስታዲየምና ወደ መርካቶ አመዴ ያሉት የቆዳ ውጤቶች ገበያን ማየት ይቻላል። በርካታ የውጭ ሀገር ገዥዎችም ምርቶቹ በሚታዩባቸው በተለያዩ የገበያ አዳራሾች ጭምር ለዕይታ ለሚገቡ የሚሸጡ ምርቶች ናቸው። ስለዚህ ኅብረተሰቡ በሀገር ውስጥ የቆዳ ምርቶች የመጠቀም አቅሙና ፍላጎቱ እየጨመረ ነው።
“የእኛን ዕውቀት ከማሳደግ ፣የውጭ ሀገር አቻ የሥራ ልምድ ተሞክሮን ከመቅሰም አንፃር ፤የተለያዩ ፕሮጀክቶች መንግሥት ቀርፆ ይተገብራል” የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ የተለያዩ ሀገሮችን ተሞክሮ በማምጣት ምርት እንዲያድግ፣ ጥራቱ እንዲጠብቅ፣ ዲዛይኑ ገበያውን እንዲከተልና ፍላጎት እንዲስብ አዳዲስ ፋሽኖች እንደሚተዋወቁ ይገልፃሉ።
“በቂ የዲዛይን ባለሙያዎች አሉ ብሎ ለመናገር አይቻልም” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ በዲዛይን ደረጃ የቆየና ብቸኛ ተቋም እንደመሆኑ መጠን ብዙ መሠራት ያለባቸው ተግባራት እንዳሉ ያስረዳሉ። ሙያዊ ትስስርን ከመፍጠር አንፃር ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ እንደሆነም ይገልፃሉ። የመጀመሪያ ዲግሪን ከባህር ዳር፣ ከውሎ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት እየሠጡ መሆኑንም ይናገራሉ። የዲዛይነሮቹን አቅም ከማጎልበት አንፃር የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ ነው።
“የማምረት አቅማችን ጫማን ሳይጨምር 1ነጥብ 45 ሚሊዮን አካባቢ እየደረሰ ነው። የቆዳ ጓንት ደግሞ በጥንድ 2ሚሊዮን” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ይህ ሁኔታ ካለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የላቀ ነው ይላሉ። በኤክስፖርት ደረጃ ዘንድሮ 10 ወራት ብቻ በቆዳ ምርቶች ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ 7 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል።
የቆዳ ውጤቶች በአውደ ርዕይ ደረጃ ራሱን ችሎ እስካሁን አልተካሄደም። በሚሊኒየም አዳራሽ የመላው አፍሪካ ሀገሮች የቆዳ ምርቶች የንግድ ፌስቲቫል ተካሂዷል። በዚያ ሁነት ላይ ጫማን ጨምሮ ቦርሳ የቆዳ ልብስ ጃኬት ውጤቶች ታይተዋል። በፋሽን ዙሪያ ያሉ ሞዴሎች ሁነቶች ይዘጋጃሉ። ኔክስት ፍሽን ዲዛይን፣ ሞዛይክ ዲዛይን ያሉበት የፋሽን ሁነቶች ይኖራሉ። ከሌሎች ምርቶች ጋርም ቢሆን በተለያዩ ባዛር ላይ የቆዳ ምርቶች ይቀርባሉ። አቶ ጌታቸው ምርቶችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል የፋሽን አውደ ርዕይ በተለያየ ወቅት እንደሚቀርብ በመጥቀስ ለአብነት በሸራተን ሆቴል ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ባለፈው አርብ የተጠናቀቀውን የፋሽን ውደ ርዕይ ጠቁመውናል።
ማጠቃለያ
አቶ ጌታቸው የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ሠልጣኞች አቅማቸውን አሳድገው የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን በአቅምና በሙያ የበለጠም ተወዳዳሪ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው ይላሉ። በጫማ፣ አልባሳትና በቦርሳ ሥልጠና የሚሰጠው ኢንስቲትዩቱ በቆዳ ዙሪያ ሥራ ፈጠራ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉና ፋብሪካ ለመክፈት ፍላጎት የሚያሳዩ ካሉ ተቋሙ በማማከር እንደሚሠራ ጠቁመዋል። የአዋጪነት ጥናት ከመሥራት ጀምሮ ቅድመ ገበያና ድኅረ ገበያ ጉዳዮችን እንደሚያካትትም ተናግረዋል። ይህ ሂደት በፋሽንና ዲዛይን ሥልጠና መስጠትን ያካተተ እንደሆነ ገልፀዋል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም