በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች አትክልት እና ፍራፍሬ በውድ ዋጋ ከመሸጥ አልፎ እስከና አካቴው ሲጠፋ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት በመትረፍረፍ ገዥ አጥተው በርካሽ ዋጋ ከመሸጥ አልፎ አምራቹ በማሳ ትቶ ሲገባ ይታያል። አንዳንድ ጊዜ መሰል ክስተቶች በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀትም ይስተዋላል። 50 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ አምራች ገዥ አጥቶ ሽንኩርት በማሳ ትቶ ሲገባ ሸማቹ በውድ ዋጋ ሲገዛ ማየት የተለመደ ሆኗል።
ይህን መሰል ችግሮች በተለይም፣ በሙዝ፣ በማንጎ ፣ በድንች እና በቲማቲም በስፋት ይስተዋላል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መሰል ችግሮችን የገበያ ውድቀት (market failure) በማለት ይጠሩታል። መሰል ችግሮች ለምን ይከሰታሉ? መፍትሄውስ ምንድን ነው? የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የገበያ ውድቀት በነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋል የኢኮኖሚ ክስተት ነው። የኢኮኖሚ ክስተት ከመሆንም ባሻገር ችግር ተደርጎ ይወሰዳል። የገበያ ውድቀት እንዲከሰት የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖራሉ። ለችግሩ መፍትሄዎችም አሉ ይላሉ።
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚሉት፤ የገበያ ውድቀት የብዙ ሀገራት ችግር ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በቴክኖሎጂ ባልበለጸጉ፣ መሰረተ ልማት በሚፈለገው ልክ ባልተስፋፋባቸው እና ሰፊ የቆዳ ስፋት ባለባቸው ሀገራት የገበያ ውድቀት የምርት ብክነት እንዲከሰት ምክንያት በመሆን በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከትላል።
የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከሰሜን ደቡብ፤ ከምዕራብ ምስራቅ የተለያየ አየር ንብረት፣ የተለያየ የገበሬዎች የሥራ ባህል፣ የተለያዩ ምርቶችን የማምረት ልምድ አለ። በየአካባቢዎቹ የሚኖሩ አርሶ አደሮቹ የሚያመርቷቸው በአንጻራዊነት ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉባቸውን ምርቶች ነው። በመሆኑም በአንድ አካባቢ የአንድ ምርት መትረፍረፍ ሲኖር በሌላ አካባቢ የሌላው ምርት መትረፍረፍ ወይም ማጠር ይኖራል። በመሆኑም ክፍተት ይፈጠራል። ምርቶች በሚመረቱባቸው አካባቢዎች እና የምርት እጥረት በሚስተዋልባቸው ቦታዎች ያለውን ክፍተት የሚሸፍነው ንግድ ነው። ስለዚህ በንግድ ስርዓቱ ይህንን ክፍተት መሸፈን አለበት ይላሉ።
በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት አንዱ ሚና የገበያ ውድቀትን ማዳን ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት መምህር ፍሬዘር፤ የገበያ ውድቀትን መከላከል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።የገበያ ውድቀትን መከላከል በአንድ በኩል ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት እንዲያገኝ ሲያስችል በሌላ በኩል አምራቹ ላመረተው ምርት ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ።
እንደ መምህር ፍሬዘር ማብራሪያ መሰል ችግሮችን ለመቆጣጠር መንግሥት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የመረጃ ልውውጥ ስርዓት መዘርጋት አለበት። የዶላር እና የነዳጅ ዋጋ እንደሚነገረው ሁሉ ዝቅተኛ ማህበረሰብ የሚጠቀምባቸውን አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ዋጋ በየአካባቢው ምን እንደሚመስል ቢያሳውቅ ነጋዴውም አምራቹም ሸማቹም መረጃ ይኖረዋል። ሰው በዚያ መረጃ ላይ ተመርኩዞ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ክፍተቱ ይሞላል።
ለዚህም መንግሥት የመረጃ ልውውጥ ሰንሰለቶችን ሊገነባ ይገባል። የመረጃ ልውውጥ ሰንሰለት መዘርጋት የመንግሥት ግዴታ ነው። የት ቦታ የየትኛው ምርት ፍላጎት አለ፣ የት የተትረፈረፈ ምርት ይገኛል የሚለውን የመጠቆም ሥራ መስራት አለበት። ለዚህም የተለያዩ ዘዴዎችን መጠቀም ይችላል ይላሉ።
በአንድ አካባቢ አንድ ምርት የሚወደደው የአቅርቦት እጥረት ስለሚኖር ነው። ይህ እንዳይሆን አቅርቦት ካለባቸው አካባቢዎች፤ አቅርቦት ወደሌለባቸው አካባቢዎች ማንቀሳቀስ ቢቻል ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የመገበያያ ሁኔታ ይኖራል። በዚህ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል። አምራቹም ያመረተው ምርት ሳይበላሽ ለገበያ የሚያቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል።
የመረጃ ልውውጥ ሰንሰለት በመዘርጋት ብቻ ችግሩ ላይቀረፍ ይችላል የሚሉት መምህር ፍሬዘር የመረጃ ልውውጥ ሰንሰለት ችግሩን የማይቀርፍ ከሆነ ጠንካራ የአምራቾች ማህበራት እንዲቋቋሙ በማድረግ አምራቾቹ የቢዝነስ ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ያመረቱትን ምርት ለሸማቾች የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ። አምራቾች ያመረቱትን ምርት ለሸማች የሚያቀርቡበትን ሁኔታ መፍጠር የገበያ ውድቀትን ከመከላከል ባሻገር ደላሎች ጣልቃ በመግባት የሚፈጥሯቸውን ችግሮች ለመከላከልም መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።
አትክልትና ፍራፍሬዎች ማቀነባበሪያዎችን መገንባት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የተሻለ መፍትሄ ነው። ማቀነባበሪያዎች ቢኖሩ ምርቶቹን በማቀነባበር እንዳይበላሽ ከመከላከል ባሻገር ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ድንች በሚመረትባቸው አካባቢዎች የድንች ማቀነባበሪያ፣ ሙዝ በሚመረትባቸው አካባቢ የሙዝ ማቀነባበሪያ እንዲሁም ሽንኩርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ሽንኩርት ማቀነባበሪያዎች እንዲኖሩ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም