በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወርቅ ማውጣት ሥራ ተሰማርተዋል።ከእነዚህ መካከልም ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ። በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የወርቅ ምርት ውስጥ 60 ከመቶ በላይ ድርሻ የሚይዘው በባህላዊ መንገድ የሚመረተው ወርቅ ስለመሆኑም መረጃዎች ያመለክታሉ። ሆኖም የወርቅ አመራረት ሂደቱ በቴክኖሎጂና በመሳሪያ ባለመደገፉ የታሰበውን ያህል ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ አልተቻለም። አብዛኞቹ ወርቅ አምራቾችም በሚፈለገው ልክ አምርተው ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም።
አቶ ቶር ኡዳንግ በጋምቤላ ክልል የአኙዋክ ብሄረሰብ ዞን ዲማ ወረዳ የቶር ኡዳንግ ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ማህበሩ በአብዛኛው ወርቅ እያመረተ የሚገኘው ማሽን በመከራየት ነው። ይሁንና ወርቅ የማምረት ሥራው ውሃና የውሃ ፓምፕ እንዲሁም የማጠቢያና መቆፈሪያ ማሽኖችን የሚጠይቅ በመሆኑ እነዚህን ለማሟላት በመንግሥት በኩል ድጋፍ ያስፈልጋል።
ማህበሩ ወርቅ የሚያመርተው ቀድመው በባህላዊ መንገድ ወርቅ ይመረትባቸው በነበሩ ቦታዎች ሲሆን በሌሎች ወርቅ ይገኝባቸዋል ተብለው በሚታሰቡ አካባቢዎች ላይ በቂ ጥናት ባለመደረጉ አልተገባም። በእነዚህ ቦታዎች ላይ መንግሥት ጥናት የሚያካሂድ ከሆነና በልዩ አነስተኛ ደረጃ ወርቅ ለሚያመርቱ ማህበራት ፍቃድ የሚሰጥ ከሆነ ማህበሩ ገብቶ ይሰራል።
ማህበሩ ከመንግሥት በተለይ የማሽነሪ ድጋፍ ቢያገኝ ወርቅን በዘመናዊ መንገድ በማምረትና ለብሄራዊ ባንክ በማቅረብ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል። በዚህ ዓመት በአስር ወር ብቻ 50 ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ አቅርቧል። ይሁንና የወርቅ ምርት መጠን ከዓመት ዓመት የሚለዋወጥ በመሆኑ በዓመት ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርበው የወርቅ መጠን ከ50 ኪሎግራም ሊያንስ ወይም ከፍ ሊል ይችላል።
በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ የሾላ ቀበሌ ተፋሰስ ባህላዊ የወርቅ አምራች ማህበር ዋና ሰብሳቢ አቶ ቤቴልሄም ቻኮና እንደሚሉት ማህበሩ ሁለት መቶ አባላትን በማቀፍ ወርቅን በባህላዊ መንገድ እያመረተ ይገኛል።
ይሁንና ማህበሩ ከባህላዊ ወርቅ አምራች ወደ ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራችነት ደረጃ ሽግግር አላደረገም። ከዚህ አኳያም ማህበሩ ወርቅን በተሻለ መንገድ አምርቶ አባላቱንም ሆነ መንግሥትን ተጠቃሚ እንዲያደርግ በመንግሥት በኩል የማሽነሪ ድጋፍ ይፈልጋል።
ማህበሩ በየዓመቱ ሃያ ኪሎግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርብ ሲሆን ምርቱን በዘመናዊና በማሽን በተደገፈ መልኩ ቢያመርት ከዚህም በላይ መጠን ያለው ወርቅ ማቅረብ ይችላል። ወርቅ የሚመረትበት አካባቢ ባንክ አለመኖሩም ምርቱን ለመገበያየት ተጨማሪ እንቅፋት ፈጥሮበታል። ሆኖም በአካባቢው ባንክ ቢኖር የቁጠባ ባህል እንዲዳብር ከማድረጉም በዘለለ የወርቅ ግብይቱን ያሳልጣል።
በቀጣይም ማህበሩ በመንግሥት ተደግፎ አሁን ላይ አባላቱ የሚያባክኑትን ጉልበት በማስቀረት ወደ ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ማህበር ደረጃ የመግባት እቅድ አለው። ይህንኑ እቅዱን ለማሳካትም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዞን ሸርቆሌ ወረዳ የገያፅ ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሽራ አስኪያጅ አቶ አህመድ መሀመድ እንደሚሉት በመጀመሪያ በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀትና አስር አባላትን በመያዝ ወርቅ የማምረት ሥራው ተጀምሯል። በአሁኑ ጊዜ ግን በልዩ አነስተኛ ደረጃ ወርቅን በባህላዊ መንገድ እያመረተ ይገኛል። ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ማህበሩ ከባህላዊ የወርቅ አመራረት ስርዓት አልወጣም።
በወርቅ ማዕድን ላይ በቂ ጥናት ባለመካሄዱ ማህበሩ እስካሁን ድረስ በባህላዊ መንገድ ወርቅ ማምረቱን አልተወም። ሆኖም የወርቅ አመራረት ሂደቱ በጥናት ላይ የተመሰረተና በዘመናዊ መልኩ የሚከናወን ቢሆን ማህበሩ አሁን እያመረተው ካለው ወርቅ በላይ ማምረት ይችላል። ለብሄራዊ ባንክ የሚያስገባው የወርቅ መጠንም ከፍ ይላል፤ የውጭ ምንዛሪንም ያሳድጋል።
በዚህ ዓመት በአስር ወራት ብቻ ማህበሩ ስድስት ኪሎ ያህል ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይ ከዚህም በላይ አምርቶ ማቅረብ እንዲቻል በመንግሥት በኩል ሞያዊና የማሽነሪ ድጋፍ ይፈልጋል። በተለይ ደግሞ ማህበሩ ከልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች ደረጃ ወደቀጣዩ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር የመንግሥት ድጋፍ ወሳኝ ነው። በአካባቢው የመንገድና የውሃ ችግር በመኖሩም ተመሳሳይ መፍትሄ በመንግሥት በኩል ይፈልጋል።
ለጊዜው የማህበሩ አባላት ቁጥር አስር ቢሆንም በቀጣይ ግን ማህበሩ የአባላቱን ቁጥር ወደ መቶ የማሳደግ እቅድ አለው። የመንግሥትን ድጋፍ ባያገኝ እንኳን ማህበሩ ዘመናዊ መሳሪያዎችን ከባለሃብቶች በመከራየት በዘመናዊ መልኩ ወርቅ የማምረቱን ሥራ ይቀጥላል። አቅሙን ማጎልበት ከቻለም ማሽኖቹን በራሱ የመግዛት እቅድ እንዳለው ይናገራሉ።
የመአድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሰሞኑን ለባህላዊ ወርቅ አምራቾች የእውቅናና ሽልማት ፕሮግራም በሸራተን አዲስ ሆቴል ማዘጋጀቱ ይታወሳል። በዚህ ወቅት የመአድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ባህላዊ የወርቅ አመራረት ሂደቱ በቴክኖሎጂ በተደገፈና በዘመናዊ መልኩ እንዲከናወን በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም