አዲስ አበባ፡- የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአደጋ ስጋት ቅነሳን ከአገሪቱ ብሄራዊ የልማት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር የሚያስችል አካታች የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂዎችን የያዘ መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቀን «አደጋ የህይወት ዋጋ ያስከፍላል» በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለዘጠነኛ ጊዜ ትናንት ታስቦ ውሏል፡፡
የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ መመሪያው ትናንት በሂልተን ሆቴል ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት፤ መመሪያው የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ አገሪቱ በተደጋጋሚ የሚያጋጥማትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ከመከላከል ባሻገር የድጋፍ ሥራዎችን ከልማት ሥራዎች ጋር በማስተሳሰር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ነው፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ አገሪቱ በተለይ በድርቅ ምክንያት ሊከሰት የሚችልን የኢኮኖሚ ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል አቅም በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶችን ማሳየት የቻለች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተስተዋሉ ባሉ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት እየደረሰ ያለው የዜጎች መፈናቀልና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል አሁን እንደ ድርቅ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመቋቋም የሚያስችል አቅምም በዘላቂነት መፍጠር አልቻለችም፡፡
«ከ30ዓመት በላይ ስንረዳ ቆይተናል፤ እርዳታ ለህመም ማስታገሻ ያገለግላል እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም» ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የአገሪቱ የልማት እቅዶችና ስትራቴጂዎች በአደጋ ምክንያት ሊደርስ የሚችልን ውድመትና ጥፋት አደጋ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መተንበይና መከላከል በሚያስችል መልኩ መተግበርን የሚጠይቅ መሆኑን አብራ ርተዋል፡፡ ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት መመሪያው መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩልም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቱ ክልሎች ከግጭት ጋር ተያይዞ ከሚኖሩበት አካባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች ጊዜያዊ የሰብዓዊ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቀን ከሌሊት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው የመመለሱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለአብነት ያህልም ከሰሞኑ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ከ28ሺ በላይ ዜጎችን ወደመጡበት የመመለስና መልሶ የማቋቋም ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁንና የኮሚሽኑ ዋነኛ ሚና አደጋ ከተከሰተ በኋላ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ እንደመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣቱ ላይ የሁሉም ጥረት ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይም የግጭቶች መንስኤዎችን በመለየት ከምንጫቸው የማድረቁ ተግባር በወሳኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ፕሮግራም መሪ ሚስተር ሪቻርድ ስፔንሰር በበኩላቸው እንዳመለከቱት፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ የሆኑ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 80 በመቶ የሚሆኑት በተፈጥሮ አደጋ በተከሰተ ድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል፡፡ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ እ.ኤ.አ በ2011 እስከ2012 ዓ.ም ብቻ 13 ሚሊዮን ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለድርቅ ተጋላጭ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሰው ሰራሽ በሆኑ አደጋዎች በተለይም በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት በየዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የቀጣናው ነዋሪዎች ለሞትና ለስደት መዳረጋቸውን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያም ከእነዚህ አገራት አንደኛዋ መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃርም የአገሪቱ መንግሥት ችግሩን ለመከላከልና ከተከሰተ በኋላም ለዜጎች አፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መመሪያውን ማዘጋጀቱም የዚሁ ጥረቱ አንዱ አካል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
መመሪያው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ካስቀመጠው አቅጣጫ አንፃር ከፖሊሲና ስትራቴጂዎች አንፃር የተቃኘ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያግዝ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ ባንኩ ለመመሪያው ተግባራዊነት የበኩሉን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ «በተለይም በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ እየጨመረ ያለውን የሰዎች ፍልሰት በዚህ ምክንያት የሚመጣውን አደጋ በመቆጣጠር በኩል ጠንካራ ድጋፍ በማድረግ አጋርነቱን ያሳያል» በማለት ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ እያጋጠማት ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው በተለይም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በማውጣት ተግባራዊ ማድረጉ ችግሩ የከፋ እንዳይሆን ብሎም እንዳይባባስ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡ የዓለም ባንክ የአገሪቱ መንግሥት በሚያደርጋቸው ሥራዎች ላይ የበኩሉን ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የኮሚሽኑ መረጃ እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ በማርች 2015 በጃፓን ሴንዳይ ከተማ በተካሄደው ሦስተኛው የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጉባዔ ላይ ከምዕተ ዓመቱ ዘላቂ የልማት ግቦችና ከፓሪስ የአካባቢ አየር ንብረት ጥበቃ ስምምነት ጋር በተጣጣመ መልኩ አገራት አካታች የአደጋ ስጋት ቅነሳ መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ነው እንዲዘጋጅ የተደረገው፡፡
ማህሌት አብዱል