በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ መልዕክት ሲበዛ ጠንካራ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ጀምሮ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከእያንዳንዱ አንደበት የሚተላለፈው መልዕክት በአብዛኛው የሚያጠነጥነው ‹‹ይቻላል፤ እንገነባዋለን፤ለግድቡ የተቻለንን ሁሉ እናዋጣለን፤ እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን፤ ብርሃኑንም እናያለን›› የሚሉና ህይወት ያላቸው ስለመሆናቸው የእያንዳንዱ ሰው የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ከዚህም አለፍ ሲል ሁላችንም በህዳሴ ግድባችን የመጣን የትኛውንም አካል መታገስ እንደማይቻለን በያገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ከመግለጽ ተቆጥበን አናውቅም። በተለይ የውጭ ተጽዕኖ አለ ከተባለማ ‹‹ምን ቆርጧቸው ነው ነገር ነገር የሚላቸው!? አልበዛም ! ኢትዮጵያውያን መሆናችንን ዘነጉት እንዴ!›› ማለታችንም አይቀርም። ለዚህ አባባላችን በዋነኝነት በምክንያትነት የምናስቀምጠው ነገር የመጀመሪያ ከገዛ አገራችን በሚፈልቀው ውሃ ሌሎች የተፋሰሱ አገራት ሳንጎዳ መጠቀም መቻላችን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የትኛውም አገር ከግድባችን ጋር ተያይዞ ቤሳቤስቲን አለመስጠታቸውን ጠቅቀን በማወቃችንም ጭምር ነው። ከዚህም የተነሳ በህዳሴ ግድባችን የመጣን የትኛውንም ተግዳሮት በአይናችን ብሌን የመጣን ያህል ስለምንቆጥረው እስከህይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን የሚሉ መልዕክቶችም ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንደበት ሲደመጥ መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው።
ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያ አንደበት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ከልብ የሚነገሩ ቃላት በተግባር ታጅበው ዛሬ እነሆ አስረኛ ዓመት ላይ እንገኛለን። ግድባችን እውን ሆነ ከዲዛይን ወደ ሚጨበጥ ከፍ ብሎ ተናፋቂው ብርሃን ሊፈነጥቅ ከጫፍ ደርሷል። ብርሃን ከገንዘብ ጋር ሲደመር ደግሞ ለኢትዮጵያ ጉዳይ መሙላት ትልቁን ስፍራ ይይዛል። ይህ እንዳይሆን በዙሪያችን እንደጦስ ዶሮ የሚዞር የእድገታችንና የልማታችን ጸር የሆነው የትኛውም ተጽዕኖ ግን በኢትዮጵያውያን አንድነትና መተሳሰብ ሊመከት የግድ ይላል።
የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የላብ ፊርማ ያረፈበት ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሞልቶ የኢትዮጵያውያኑን ላብ እንዳይመልስ መልማታችን የሚያስፈራቸውና እንደውስጥ እግር እሳት የሚያንገበግባቸው አካላት ጉዳያችን እንዳይሞላ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በብዙ ድካምም ይማስናሉ። አፍ አውጥተውም የኢትዮጵያ እድገት እንደሚያሰጋቸው ይናገራሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ልታድግ ብሎም በልማት ልትመነደግ ጊዜው አሁን ነው። በኢትዮጵያ ማደግ የፍርሃት ቆፈን ይዟቸው ቢያንቀጠቅጣቸውም የኢትዮጵያ እድገት ሽቅብ እንጂ ከዚህ በኋላ ቁልቁል እንዳልሆነ ቢገባቸው መልካም ነው።
ኢትዮጵያ አገራችን ብዙ አቅዳለች፤ በብዙም እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ጉዳዬ ነው ብላ የያዘቻቸው አንኳር አንኳር ነገሮች መስመር እየያዙላት ነው። አንዳንዶች እንደሚያሟርቱት በአጭር የምትቀር አገር ሳትሆን ታላቂቱ አገር ታላቅነቷን በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር እያረጋገጠች በመጓዝ ላይ ትገኛለች። ዋና ግቧም ራሷን በአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንደመሆኑ ይህ ጉዳይዋ ይሞላ ዘንድ የዜጎቿ መግባባትና መተባበር የግድ ይላል።
የህዳሴ ግድቡ በማን አለብኝነት የሚገነባ ግድብ ሳይሆን የሌሎችንም የተፋሰሱ አገሮች በማይጎዳ ሁኔታ እየተገነባ ያለ ግድብ ስለመሆኑ ኢትዮጵያ በየአጋጣሚው ሁሉ ከመግለጽ ተቆጥባ አታውቅም። ይህን ጉዳይ ለማስረዳትም ታብያም አታውቅም። ግድቡን ለመገንባት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስና የመጀመሪያውን 4 ነጥብ 9 ሜትር ኪዩብ ውሃ ለመሙላት በዘፈቀደ እንዳልተጓዘች ሁሉ በቀጣይም በመጪው ክረምት ላይ ሁለተኛውን ዙር ውሃ ለመሞላት የማንንም ፈቃድ መጠየቅ አይጠበቅባትም። ምክንያቱም እየገነባች ያለው ውሃ ይዞ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ነው። ይህ ደግሞ ቅጠል ተሸክመው በጭስ የሚታጠኑ እናቶቻችን በዘላቂነት ከጭስና ከእንግልት የሚገላግል ነው። ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ፍትሀዊ ተጠቃሚ እንሆን መለቷ የሚያስመሰግናት እንጂ በጥርጣሬ የሚያሳያት አይደለም።
ኢትዮጵያ እቅዷ መና አይቀርም፤ እንደቀደመው የቅኝ ግዛት ውል ተጠፍራ ዛሬ ህዝቧን አታስርብም። ከገዛ ምድሯ በሚመነጨውና ለተፋሰሱ አገራት 86 በመቶ አበርክቶ ባለው ውሃዋ የመጠቀም መብቷን ከማንም ጠይቃ መውሰድ አይጠበቅባትም። ከዚህ ቀደም ለበርካታ ዓመታት ግብፅና ሱዳን ያለ ተቀናቃኝ ባፈጀና ባረጀ ህግ አስረው ዛሬም እንደትናንቱ ሊያሰናክሉን አይችሉም።
እኛ እንደሌሎቹ አገራት የባህር በር የለንም፤ ወይም ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን እንደፈለግነው ከከርሰምድራችን የምንቀዳው ነዳጅ በተፈለገው ሁኔታ አልተመቻቸልንም። ስለዚህም ለልማታችን ቁልፍ ነው ያለነውን የህዳሴ ግድባችንን አጠናቀን መጠቀም የአማራጭ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ከምድራችን በሚፈልቀው ውሃ የታችኛዎቹን ተፋሰስ አገራት ሳንጎዳ የመጠቀም መብታችንን ማንም ሊነፍገን ባለመቻሉም ነው የህዳሴ ግድቡ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኪስና መቀነት ተፈትቶ በመገንባቱ አሁን የሚገኝበት ደረጃ ላይ መድረስ የቻለው።
ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ የምታደርገው ጉዞ ቀላል አይደለም። ማንኛውም የምታከናውናቸው ተግባራት ብዙዎችን የማይጎዳ እንደሆነ ቢታወቅም የሚያስከፋቸው ብዙ ናቸው ብላ ግን እጇን አጣጥፋ አትቀመጥም። ተወደደም ተጠላ የኢትዮጵያ የልማቷና የእድገቷ መሰረት በሆነው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ መቀለድ አይዳዳትም፤ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን ግድቧን ሞልታ ለህዝቧ ብርሃን ትፈነጥቃለች እንጂ ህዝቧና መንግስቷ በብዙ ዋጋ ከፍለው የገነቡትን የህዳሴ ግድብ እንደሃውልት ተገትራ ለማየት አሊያም ለማስጎብኘት አይደለም የገነባችው።
እርግጥ ነው አንዳንድ ህልመኞች ከጉዞዋ ሊያናጥቧት ደፋ ቀና ማለታቸው አልቀረም። ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ ህግን ለማስከበር ደፋ ቀና እያለች ባለችበት ወቅት ሱዳን ያልተገባትን ለመጠየቅ አላመነታችም። የመሬት ይገባኛልን ጥያቄ ስታነሳ ግን የተላለፈችው በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ዘንግታለች። ኢትዮጵያ ጉዳዩ እስኪሞላ የምትተኛው በአንድ አይኗ ብቻ እንደሆነ አልተረዳችም።
በቅርቡ ስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ ጥቂት ሳምንታት ቀርተውናል። ይህም በሰከነ መንፈስ ስለመጓዙ ብዙዎቹን ባያስደስታቸውም ኢትዮጵያ ግን የያዘችውን እቅድ ለማሳካት ከጫፍ ላይ ደርሳለች። ግድቡን ያኔ ከአስር ዓመት በፊት ስንጀምርም ሆነ አሁን ለማጠናቀቅ ጫፍ ስንደርስም የማንንም የውጭ ድጋፍ አልተመኘንም። በራሳችን አንጡራ ላብ ለብዙዎች ጥቅም የሆነን ታላቅ ግድብ እውን አድርገናል፤ የቀረው ነገር ቢኖር የተመኘነውን ብርሃን መፈንጠቅ ሲሆን፣ እሱም ሊሆን 11ኛው ሰዓት ደርሷል ።
ሥራው ብዙ ዋጋ ቢያስከፍለንም፤ የውጭ ኃይል በተለይም የምዕራባውያኑ ተጽዕኖ ቢያይልም፤ በተለያየ አቅጣጫ የጠላት ድንፋታ ቢበረታብንም፤ ጥቂት የማይባሉ ኃይሎች ህልውናችንን ቢፈታተኑትም፤ የመልማታችን አጀንዳ ቢመራቸውም፤ በእሳት እንደተፈተነ ወርቅ ማብራታችን የግድ ነው። ግድባችንም ሆነ ጉዳያችን መሙላቱ ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ወደፊት እንጂ የኋልዮሽ ጉዞ አይሞክራትም። የእናት ኢትዮጵያ ጉዳይሽ እንዲሞላና ዕቅድሽ እንዲሳካ ሁላችንም ሁለንተናዊ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
ቅድስት ሰለሞን
አዲስ ዘመን ግንቦት 14/2013