እሁድ ነው፤ የእረፍት ቀን:: እረፍት ለሀና ቅንጦት ነው:: ለእርሷ ዛሬን እቤት እንድትውል ህይወትዋ አልፈቀደላትም:: የልጆችዋን ቁርስ አሰናድታ ሲነሱ ማግኘት የሚችሉበት ቦታ ላይ አኑራ እየተጣደፈች ከቤት ወጣች:: ወደ ስራዋ ፈጥና መድረስ አለባት:: ማታ ወደ ቤት ስትመለስ ባዶ እጅዋን ከሆነ ቤትዋ ፆሙን ያድራል:: ከሩጫ ባልተናነሰ እርምጃ የስራ ቦታዋ ደርሳ አፍልታ የምትሸጠውን ቡና ለሚጠባበቁ ደንበኞችዋ ለማድረስ ወደፊት ትጣደፋለች::
ከመቅፅበት እየሄደችበት ባለው መንገድ ላይ የሰዎች ጩኸት አካባቢውን አናጋው:: የተፈጠረውን የተመለከቱ ሁሉ ራሳቸውን ይዘው ኡኡታቸውን አቀለጡት:: አንድ የሞተር ብስክሌት ሀና በምትጓዝበት መንገድ ላይ ከፍጥነት በላይ ተንደርድሮ ዘግናኝ በሆነ መልኩ እላይዋ ላይ ወጥቶ እስከነ አሽከርካሪው ተበታተነ:: ሰዎች አደጋው ወደ ደረሰባቸው ሰዎች ቀርበው የተቻላቸውን ማድረግ ጀመሩ::
ሀና ታታሪ መሆንዋን የሚያውቋት ሁሉ የሚመሰክሩላት ወጣት ናት:: ልጆችዋ እንዳይጎልባቸው አቅምዋ የፈቀደውን ሁሉ ታደርጋለች:: “በህይወት መኖሬን የማረጋግጠው ልጆቼን ሳይ ነው::” የሚለው የዘወትር ንግግርዋ ለልጆችዋ ላላት ጥልቅ ፍቅር ማስረጃ ነው:: ሁለት ልጆችዋ አንድ ቀን እንዳይከፉባት እስዋ አስር ዓመት ብታዝን ትመርጣለች:: ምርጥ እናትና ጥሩ ሚስት ናት:: በስራ ብዙ ጊዜዋን አሳልፋ እረፍት የምትለውን ጊዜዋን ለቤተሰብዋ የምታውል ድንቅ ሴት::ብዙ ጊዜ “ባልና ሚስት ከአንድ ምንጭ ይቀዳሉ::”
ተብሎ በብዙዎች የሚነገረው አባባል እዚህ ቤት ላይ ይፋለሳል:: ሀናና ባለቤትዋ እጅጉን የተራራቀ ባህሪ ያላቸው ናቸው:: ሀናና ባለቤትዋ ሳህሉ እንደ ተቃራኒ ፓርቲዎች ሰፊ የሆነ ልዩነት የሚታይባቸው በበዙ ነገር የማይግባቡ ናቸው:: ሁኔታቸውን የተመለከተ “እንደው በምን ሁኔታ ተግባብተው ትዳር መሰረቱ ኧረ እንዴትስ ተቀራረቡ? እንዴትስ ነው የሚኖሩት” ማለቱ አይቀርም::
በአብሮነት ኑሮዋቸው ውስጥ በርካታ ጊዜ ቢጣሉም፤ በሃና ትዕግስትና በእሱ ግዴለሽነት ዛሬም ድረስ አብረው ዘልቀዋል:: ልጆቻቸው ደግሞ እንዳይለያዩ አድርገው ያስተሳሰሩዋቸው ስጦታዎቻቸው፤ እንዳይለያዩ ሰበብ የሆንዋቸው መጋመጃዎች ናቸው:: ሃና የመጀመሪያ ልጅዋን ትዕግስት ብላ የሰየመቻት በምክንያት ነው:: ቤትዋን አቅንታ ለማዝለቅ ታጋሽ መሆን እንዳለባት ለራስዋ ለመንገር::
ከመጀመሪያ ሁለተኛ ልጅዋን በፅናት አለችው:: ለጎጆዋ መፅናትን በመመኘት:: እርግጥ ጎጆዋ በአባወራው ደጀንነት የጠነከረ ባይሆንም በልጆችዋ ፍቅርና በእስዋ ጥረት ዛሬ ድረስ ቆይቷል:: ነገን ተስፋ አድርጋ ዛሬን የምትተጋ ነገን አልማ ዛሬ በብርታት የምትታትር ትጉህ ናት::ከእሷ ተቃራኒ የሆነው ባለቤትዋን ለማረቅና ለማስተካከል ብዙ ጥራለች፤ አልተሳካላትም እንጂ:: ትንሽ ሰርቶ ብዙ የሚያርፍ፣ ትንሽ ወዶ ብዙ ፍቅርን ከሌላ የሚጠብቅ አይነት ሰው:: ሃና ግን የቤትዋንና የራስዋን ህይወት ለመለወጥ የምትተጋ ጠንካራ ሴት ናት ባለቤቱ::
በእርግጥ ሳህሉ በስራው ስኬታማ የሚባል አይደለም፤ ሱሰኝነቱ የፀናበት ግን ከሶስት ዓመት በፊት ይሰራበት ከነበረው መስሪያ ቤት በሥነምግባር ብልሹነት ምክንያት ከተባረረ በኋላ ነው:: ከስራው ለመባረር ያበቃው ጉዳይም በቸልተኝነቱ በሰራው ትልቅ የሂሳብ ስህተት ነው:: በእርግጥ ሆን ብሎ ያደረገው አልነበረም:: በሌሎች ግን አለመታመኑ ይቆጨዋል:: የሂሳብ ስህተቱ ሆን ብሎ ያደረገው የመሰላቸው የበዙ ባልደረቦቹ ነበሩ:: ምክንያቱም ያለበትን ሱስ በደንብ ያውቁታልና:: ባያደርገውም ሱሰኛ መሆኑ አስጠርጥሮታል:: ባያጭበረብርም ስህተቱ ግን ከቅጣት አላዳነውም::
በወቅቱ ከስራ መባረሩ ይበልጥ ተስፋ አስቆርጦት መዋያና ማደሪያው መሸታ ቤት ሆኖ ነበር:: ያ ነበር ባለቤቱ የተፈተነችው:: ከገባበት ድባቴ ለማላቀቅ ጣረች፤ ከተዘፈቀበት የሱስ አበላ ለማውጣት የተቻላትን አደረገች:: ነገር ግን አልቻለችም:: የባንክ ደብተሩ ላይ ያለውን ብር ሲያልቅ እቤት መዋል ጀመረ:: ውሎ ሲያድር ከባለቤቱ ገንዘብ ይጠይቅ ጀመር:: በፍቅር ቀርባ የሚፈልገውን እየሰጠች ልታርቀው ሞከረች ፤ እሱ ግን ባሰበት ፤ ይብስ ብሎ በማስገደድ ስትደክም ውላ ያገኘችውን የቀን ገቢዋን ይነጥቃት ጀመር::
ይሄኔ ቤታቸው ተናጋ፤ በዚህ ጊዜ ፍቅር ነጠፈ:: አስታራቂ ሽማግሌ ተመላለሰ:: አልቅሳ ችግርዋን አወራች፤ አጎንብሳ እንዲገሩላት ለመነች:: በዚህም መመለስ አልቻለም:: ተስፋ ወደመቁረጡ ተቃረበች:: መለየትንም ደጋግማ አሰበች:: የምትወዳቸው ልጆችዋ አሳዘንዋት፤ የምትሳሳላቸው ልጆችዋን አባት አልባ ማድረግ ከበዳት:: እናም የመቻል ጥግ ላይ እስክትደርስ መቻልን ቻለች:: ለልጆችዋ ስትል ሁሉን አደረገች:: ለቤትዋ ስትል አንገትዋን ሰበረች:: ልጆችዋን ለማቅናት በችግር ብዛት ጎበጠች:: ለቤትዋ ጉልበት እስዋ ደከመች::
ዛሬም በእረፍት ቀን ወደ ድካምዋ እያቀናች ነው:: እቤትዋ ስላለው ሁሉ እያሰበች፤ ስለልጆችዋ እየተጨነቀች፤ ስለ ባልዋ ብዙ እያውጠነጠነች በመጓዝ ላይ ናት:: ነገር ግን ጉዞዋ ተገታ:: መንገድዋ እንዳይቀጥል ሆኖ ተቋረጠ:: እሩቅ አስባ ባጠረ ጉዞ ከመንገድዋ ክፉ ገጠመኝ ገታት:: ሁኔታው እዚያ ቦታ ለነበረው ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ነበር:: ሰዎች አፋፍሰው ወደ ህክምና ለማድረስ ሞከሩ፤ ሀኪም ከማግኘትዋ በፊት ግን እስትንፋስዋ ተቋረጠ::
የአካባቢው ነዋሪዎች ባለቤትዋ ስለሆነው ከእንቅልፉ ቀስቅሰው ነገሩት:: ያልጠበቀውን መርዶ አረዱት:: ጉልበቱ ተብረከረከ:: ሁሉ ነገር ጨለመበት:: ለአንድም ቀን አስቦላት ለማያውቀው ሚስቱ ለቀናት አነባ:: ለዓመታት ሲበድላት ለነበረችው ሚስቱ ልቡ በፀፀት አደማ:: በኀዘን የተኮማተረው ልቡ ራሱንና ሱሱን አስተወው:: ለወራት ራሱን እንደ መሳት አደረገው:: ወደራሱ ሲመለስ አዲስ ሰው ሆነ:: ልጆቹን እንዳባት አይቶዋቸው አያውቅም:: ዛሬ ግን እናትም አባት የመሆን ግዴታ እንዳለበት ተረዳ:: ስለልጆቹ ብዙ ሊሆን፤ እነሱን ተንከባክቦ ለፍሬ አብቅቶ ከበደላት ሚስቱ ሙት መንፈስ ጋር መታረቅን አሰበ:: በመታደስ ሂደት ውስጥ ወራት አለፉ::
የሳህሉን ለውጥ የተመለከቱ ተደነቁ:: የእሱ ሁኔታ መለወጥ ያስገረማቸው የሚስቱ አለመኖር አስቆጫቸው:: የእሱ አዲስ ሰው መሆን ለልጆቹ ህይወት ዳግም መታደስ ምክንያት ሆነ:: በሚስቱ ቢያረፍድም ለልጆቹ ቀድሞ ደርሶ ሊታደጋቸው ሃላፊነቱን ያለ ስስት መወጣት ጀመረ:: በሚስቱ አርፍዶ ለአብራኳ ክፋዮች ለመካስ የተጓደለ ህይወትን እንደአዲስ መምራት ቀጠለ:: …ተፈፀመ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2013