በተአምራት ድነዋል
በትግሬ ጠ/ግዛት በመቀሌ ከተማ ሚያዝያ ፲/፶፩ ዓ.ም ከሌሊቱ ፫ ሰዓት ሲሆን የግራዝማች ገዛኸኝ ፎቅ አግዳሚው ተሸካሚ ተሰብሮ ሲፈርስ በፎቁ ላይ ፭ ወንዶችና ፬ ሴቶች አንድ ጥጃ ስለነበሩ፤ እነዚህ ወደ ምድር ቤት ወርደው የፎቁ ወለል አፈርና ማዕዘን ተደንብቶባቸው ሳለ አንዲት ሴት በግድግዳው ጥግ ተንጠላጥለው ጩኸት ስላሰሙ ጎረቤቶች ረድተው የተጠቀሱትን ሰዎች የተጫናቸውን ማእዘንና አፈር አንስተው አውጥተዋቸዋል።
ከ፱ጠኙ ሰዎች ግርማይ ገዛኸኝ የተባለው ከራሱ ላይ በ፫ ቦታ ሲቆስል ሌሎቹ ድነዋል፤ በቤቱ ውስጥ ፳ ኩንታል የሚሆን ከያይነቱ እህል ስለነበረ ከአፈሩ ጋር ተደባልቆ ተበላሽቱዋል ሲሉ የመቀሌ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሻምበል ምኒልክ ኋ/ማርያም ባስተላለፉልን ጽሑፍ ተረጋግጧል።
እግዚአብሔር በቸርነቱ ባይመለከታቸው ኖሮ ያን ያህል አፈርና ድንጋይ ማዕዘን ተጭኖአቸው ወዲያው ያልቁ ነበር። ያምላክ ቸርነት ወሰን የለውምና አንድም ሰው ሳይሞት መዳናቸው ተአምር ነው።
የትግሬ ጠ/ግ/ አዣንስ
ሚያዚያ 30 ቀን 1951
ሌባ አዳኙ ሌባ ሆኖ ተገኘ
በደብረማርቆስ አውራጃ የጐጃም ወረዳ ግዛት ውስጥ ሌባ አዳኝ (ነጭ ለባሽ ) ገላዬ ካሣ የተባለው የተሰጠውን አደራ በመዘንጋት የሰላማዊ ሕዝብን ሀብትና ንብረት በመስረቅ በመዝረፍ ሕዝብን በድሏል ሲባል ሲወራበት ከቆየ በኋላ፤ ሐሰትና ቅጥፈት የኋላ የኋላ መገለጣቸው አይቀርምና የመጨረሻው ጊዜ አቶ በላይ ደጉን ግምቱ አራት መቶ የሆነ ሀብት በመስረቅ ግላዊ ወንጀል ሠርቱዋል ተብሎ ስለተከሰሰና የሠራውም የስርቆትና የዘረፋ ወንጀል እጅግ የበዛ በመሆኑ በፖሊስ በመከታተል ሁኔታው ተጣርቶ ደብረ ማርቆስ አስቻለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሠራውም የስርቆት ወንጀል ተመስክሮበት ስለወንጀሉ ፭ ዓመት ተፈርዶበት እወህኒ ቤት ገብቷል። ስለዘረፈውና ስለሰረቀው ገንዘብ ግን በፍትሐ ብሔር ተከሶ እንዲከፍል ተደርጉዋል።
ይህ ሌባ አዳኝ የሚባል ስም የተሰጠው የመንግሥቱ ሌቦችን ወስላቶችን፤ ነፍሰገዳዮችን ጭምር እየተከታተለ በመያዝና ለበላይ ባለሥልጣን አቅርቦ አስፈላጊውን ቅጣት በማስወሰን የሕዝቡን ችግር እንዲያቃልል የተሰጠውን ሥልጣን ክዶ፤ አይሰማብኝም፤ አይገለጽብኝም በማለት በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ይህን የስርቆትና የዘረፋ ወንጀል ሠርቶ መገኘቱ፤ የወስላቶች መንፈስ የተቆራኘው የማስተዋል ችሎታ የሌለው መሆኑን ከመረዳቱም ይልቅ፤ እሱን የመሰለ የሱን ውስልትና ተግባር እየተከተለ እንደዚሁ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ወንጀል ሲፈጽም ስለተገኘ፤ ፍሬው ብርሃኔ ስለተባለውም ሌባ አዳኝ ተከሶ የሠራው ወንጀል የተጨበጠ በመሆኑ፤ ውሳኔ ባልተሰጠ ጊዜ እሥር ቤት እንዲቆይና ወደፊት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሚወስንበትን ፍርድ እንዲጠብቅ ተወስኖዋል።
ስለዚህ ወደፊትም ቢሆን ፖሊሶች በበለጠ መከታተልና ይህን የመሰለውን እምነት አጉዳይ ወንጀለኛ በመመርመር ማግኘት የሚያስመሰግናቸው ነው።
የማነ በየነ የጐጃም ጠ/ግዛት አዣንስ ረዳት ተምሮ መመለስ
የመካኒክ ትምህርት እንዲማሩ ወደ ውጪ ሀገር ተልከው የነበሩት አቶ ታሪኩ ማህተመ ስላሴ፣ የእርሻ ሚኒስቴር ባልደረባ፣ ከጀርመን ሀገር ሰርጀን ሜጄር ሰይፉ ዲን ሲራጅና የአስር አለቃ ግርማ ሀብቴ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ትምህርት ቤት ባልደረቦች ከአሜሪካ አገር የተላኩበትን ትምህርት እስከ ተወሰነላቸው ጊዜ ድረስ ሲማሩ ቆይተው ግንቦት ፭ ቀን ፩፱፶፩ አም ከእኩለ ቀን በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አኤሮፕላን አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
አቶ በጋሻው አበበና አቶ ተሻለ አበበ፣ በእርሻ ሚኒስቴር ባልደረቦች ለአራት ወር ያህል የአንበገጣ መከላከያ ትምህርት ለመማር ወደ እንግሊዝ ሊቪያና ሱዳን ሄደው ስለነበር፤ ዛሬ ግንቦት አምስት ቀን ከእኩለ ቀን በፊት አራት ሰአት ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ አኤሮፕለን አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
ግንቦት 6 ቀን 1951
አምሯል
ዘንድሮ ወሎ ብላጊ በጣም በመያዙ ህዝቡ በጣም ተደስቷል። አሁን ደግሞ በዚህ በግንቦት ወር ቆላ ደጋውን እያስማማ በጸሀይ ጣልቃ በመግባት ስለሚዘንብ በደጋው ግንቦቴ በቆላው ማሽላ በየአይነቱ በመዝራት ላይ ይገኛል።
የወሎ ጠቅላይ ግዛት አዣንስ።
ግንቦት 15 ቀን 1951
ደብረ ብርሃን
የንፋስ አደጋ
ግንቦት ፩፭ ቀን ፶፩ አም ከጠዋቱ ፭ ሰአት በሚሆንበት ጊዜ ከባድ የንፋስ አደጋ ተነስቶ በከተማው መሀል የሚገኘውን የወረና ግዛት ጽኅፈት ቤት ና አቶ ይበርታ ጻድቄ የተባሉትን ሰው ሁለት ደጃፍ መኖሪያ ቤት የጣሪያውን ቆርቆሮ ገነጣጥሎ ጥሎታል። ይህም ሲሆን በሰው ላይ አንዳችም አደጋ አልደረሰም ሲል የአውራጃው ግዛት አዣንስ በላከው ወሬ ገልጸዋል።
ግንቦት 15 1951