ሰርገኛውና የሙሽሮቹ አጃቢዎች በጭቃ በላቆጠው ጠባብ መንገድ ላይ እየተጋፉ ጭፈራውን ያስነኩታል።“ሀይሎጋ ..ሀይሎጋ ሆ.. አይሎጋ…. ኧረ ጎበዝ አህምነው” ይላሉ።እኔም አሻግሬ ውዴን እያየሁ በቀስታ እጓዛለሁ።የጓደኛዬ ሰርግ ነው።በተገኘሁበት ላይ ሁሉ ቀልቃላ የነበርኩት እኔ ያለወትሮዬ ጭር ብያለሁ።ሙሽራው ጓደኛዬና ሙሽሪት ሲያዩኝ ብቻ የሞት ሞቴን ፈገግ እላለሁ።
ውዴን ከሩቅ እያየኋት፤ ሁኔታዋንም እየተመለከትኩ ይበልጥ መብገን ጀምሬያለሁ።እስዋም ሰረቅ አድርጋ ስታየኝ ላለማስፎገር ማዘኔ እንዳታውቅብኝ ሚዜዎች መሀል ገብቼ “ጬሰ.. አቧራው ጬሰ…”ብዬ የሀይሎጋው መሪ መሆን አምሮኝ ነበር።በዚህ ጭቃ ደግሞ የምን አባሯ ብለው እንዳይስቁብኝ ፈራሁ፡፡
ከውዴ ጋር ከተዋወቅን ሶስት አመት ሞልቶን ነበር።በእርግጥ ከተግባባን ሶስተኛ ወራችን ብቻ ነበር።ግራ መጋባት ከጀመርን ደግሞ ሶስተኛ ሳምንታችን ነው። ግራ መጋባታችን አድጎ ከተኳረፍንና ትታኝ ከሄደች ሶስተኛ ቀናችን።ዛሬ ጓደኛዬ ሰርግ ላይ እንደማንተዋወቅ ሁሉ ተራርቀን በግልምጫ እንተያያለን።
ላገባት አስቤ ነበር።ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ “ለምን አታገባም?” ብለው ሲያስጨንቁኝ፤ እኔም ቆሞ መቅረቴ ሲያሳስበኝ ያስቀመጥኩትን መስፈርት ሁሉ ንጄ ነበር ውዴን ፍቅሬን ሰላምን የቀረብኳት።ምን ዋጋ አለው።በዚህ ዘመን ፍቅር የማያበረክት መውደድን የማያቆይ ገጠመኝ በዛ።የዘንድሮ ሰርግና ሰርገኛን ጠላሁት።ምክንያት ውዴን ቀምቶኛላ።ከውዴ ጋር አጋጨኝ፤ ከፍቅሬ ጋር ለየኝ።ብጠላው ምን ያንሰኛል።
የዛሬ አያድርገውና እኔና ውዴ የማያግባቡን ሶስት መሰረታዊ ነገሮች ነበሩ።ሁለቱ እንደምን አንዱን እኔንም አሳምኖ ባንዱ ላይ ተቻችሎ መቆየት ችለን ነበር ሶስተኛው ጉዳይ ግን ልዩነታችንን አስፍቶ አቃረነን።ከባድ ውሳኔ አሳልፈን ነበር።ለመጋባት ቀለል ያለው ጉዳይ ግን ግራ አጋባን።እንዴት መጋባት እንዳለብን ስላልተግባባን ተለያየን።
ውዴ ውድ ነገሮችን አጥብቃ ትወዳለች።ምግብ ቤት ገብተን ከምግብ ዝርዝር እና ዋጋ ማሳያ ሰሌዳ /ሜኑ/ ውስጥ ውድ ምግብ ካልሆነ አታዝም፣ ልብስ ልንሸምት ከወጣን ከልብሶች ውዱን እንጂ አትመርጥም።ይሄን ማድረግዋ አስከፍቶኝ አያውቅም ነበር።ውድ ነገር መምረጧን በምክንያት ወድጄው ነበር ፤እኔንም ውድ ስለሆንኩ ነው የመረጠችኝ ብዬ።ምን ዋጋ አለው ዛሬ አንተ ከሰርጉ የበለጥክ ውድ አይደለህም ብላ መሰለኝ ትታኝ ሄደች፡፡
እስዋን ከመቅረቤ በፊት ሴቶችን ለመቅረብ ብዙ መስፈርት አስቀምጬ ነበር።ነገር ግን ውዴ ቀርባኝ ያስቀመጥኩት መስፈርት ሁሉ ስህተት እንደነበር እንዳምን አድርጋኝም ነበር።ቤት ውስጥ ሴት ሆና ስላገኘኋት ወድጃትም ልንጋባ ወሰነን።ለዚያም መዘጋጀት ጀምረን፡፡ምን ዋጋ አለው? ዛሬ ዝግጅት ማድረግ ካቆምኩ ሶስት ቀን ሞላኝ።ሰርግ ካልደገስን አለች።እኔ ደግሞ ሰርግ ለኛ ጥሩ አለመሆኑን በመጥቀስ ተሟገትኩ።
ሰርግ ጥሩ ያልሆነው ለኔ ብጤ ነው፤ ወሩን ጠብቆ ጠብ የሚል ገቢ መተዳደሪያው ለሆነ።ለደላውማ ሰርግ በየአመቱ ቢደጋግም ፍቅሩ ባይደምቅ ድግሱ መድመቁ አይቀር።ለኔ ግን ሰርግ መሰረግ አይደለም ስሙም ከባድ ነው አልኳት።አብረን መኖር ጀምረን ነበር እኮ።ምን ያደርጋል ሰርግ።በቃ ቤተሰብ ጋር ሽማግሌ መላክና አብሮነታችንን ይፋ ማድረግ ይበቃል አልኳት።እስዋ ግን “በፍፁም ካልደገስን” አለች።በዚህ ተካረርን ለመለያየት በቃን፡፡
በሌለን ገንዘብ ሰርገን ግራ ከምንጋባ ተግባብተን እንጋባ ብያት ነበር።ምትሰማኝ መስሎኝ።ብዙ ጎትጉቼም አሳምኛት ነበር።የሰሞኑ የሰርግ ግርግርና ሰርገኛ መልሶ ሀሳብዋን አስቀየራት እንጂ።ማሳመኛ ምክንያት ደረደርኩ ፤ወይ ፍንክች።ፍቅር እንጂ ሰርግ ጎጆን አያሞቅም ብዬ በአለም ላይ ትልቅ ወጪ ወጥቶባቸው በወራት ውስጥ የፈረሱ ሰርጎችን ታሪክ አወራኋት።አልሰማህም አለችኝ፡፡
ግራ ቢገባኝ የባንክ ደብተሬን አውጥቼ አሳየኋት፤ አላምን አለች።ይሄኔ ተከፋሁ፤ ያን ጊዜ አመረርኩ።እርግጥ እወዳት ነበር።ያስቀመጥኩትን መስፈርት ቀንሼ…ቀንሼ ኧረ እንደውም ትቼ የቀረብኳትና ሚስቴ ትሆነኛለች ያልኳት ውዴ ሰላም ልሂድ ስትል እንድትሄድ ተውኳት፡፡
ውዴን ከመተዋወቄ በፊት ሚስት ስፈልግ እንደ መስፈርት የደረደርኳቸውን ነገሮች ብዛት ዛሬ ሳስብ ይገርመኛል።ያ ሁሉ መስፈርት ውዴን አስትታኝ ነበር።ዛሬ ትታኝ ልትሄድ ስንቱን መስፈርቴን እንድተው አድርጋኝ፤ ወይ ነዶ።ሚስት ለማግባት ካስቀመጥኳቸው መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ብዙ ልጅ ልትወልድልኝ ፍቃደኛ የሆነች ሚስት ማግኘት ነበር።
በወቅቱ መስፈርቴ በብዙ ሴቶች የማይሞከር ሆኖብኝ ተቸግሬም ነበር።ልጅ በጣም እወዳለሁ፤ በጣም ብዙ ልጅ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ።ቢያንስ አንድ ደርዘን ሊኖሩኝ ግድ ይላል ብዬ አስብ ነበር።ከተቻለም ቁጥሩ ከፍ ቢል የኔም ደስታዬ ከፍ ይላል።እንደው ለሚስቴ ካዘንኩኝና ትነሽ ከራራሁ ከአስራ ሁለት አንድ ልቀንስላት እችላለሁ።
ከ11 ግን ፈጽሞ አልቀንስም።በቃ መጨረሻዬ ነው።ከዚያም 12 ወይም 11 እድሎችን በተለያየ አስራ አንድ አቅጣጫ መጠበቅ።ህይወት የምትሰምረው በእድል ነው ብዬ አስብ ነበር።በነገራችን ላይ እድልና እድለኝነት ዛሬ ድረስ አምንበታለሁ።በእስከ ዛሬ ተሞክሮዬ ጥረት እና ትጋት ምንም ስላልፈየዱልኝ በእድል ማመን መጀመሬ ልክ ነበርኩ።
እኔ በእድል በጎ ተፅዕኖ ተፈጥሮብኝ በሱ ማመን ጀምሬያለሁ።እድል ባይኖር ኖሮ አንዳንዱ አንድም ቀን ሳይሰራ የሚቸረው የተትረፈረፈ ሀብትና የተሟላ ኑሮ ባልኖረ፤ ሌላው ደግሞ እድሜውን ሙሉ ሲማስን ኖሮ በወጉ ጠግቦ መብላት ብርቅ ባለሆነበት ነበር።እናም ህይወት እድል ናት ብዬ አምናለሁ።የልጆች ቁጥር ብዙ ሲሆን ብዙ እድል ይገኛል ብዬ ማሰብ ያስጀመረኝም ጉዳይ የበረከተ ነበር።
ውዴን ከማግኘቴ በፊት እኔን ለማግባት ካቀረብኳቸውና ከቀረቡኝ ሴቶች ኡ! “ልወልድልህ የምችለው አንድ ልጅ ብቻ ነው፡፡” ካለችኝ አንሰቶ በከፍተኛ ጉትጎታ ድርድርና ማግባባት “ሰባት ልጅ እወልደልሀለሁ፡፡” ያለችኝም ገጥማኝ ነበር።
ውዴ መጥታ ቁጥሩን በአንድ ከፍ አድርጋ ሰባት እወልድልሀለሁ ያለችኝን አስተወሰችኝ እንጂ።ውዴ በፍቅር በአያያዝዋ ምክንያት መስፈርቴን ሁሉ ትቼ የልጆች ፍላጎቴ ከ12 ሁለትና ሶስት እጥፍ ቀንሼ ሶስት ልጆች ብቻ ቢኖሩኝም አልከፋም አስብላኝ ነበር።ኧረ ብንቆይ ኖሮ ሶስቱም ይቅር ብትለኝ እኔም እሺ ሳልል አይቀርም ነበር፡፡ወድጃት ነበራ፡፡
ይሄው በሰው ሰርግ በአጋጣሚ በርቀት እየተያየን ዋልን።ያን ቀን እየተበሳጨሁና ስለ ውዴ እያሰብኩ እቤቴ ገባሁ።“በቃ ባለመሰረጌ ውዴን ላጣት ነው..ኡፉፉ” የሚገርመው ውዴና እኔን ያገናኘው ሰርግ ጥንዶች ትዳር ከወር በላይ መዝለቅ አልቻለም።ጓደኛዬ ድል ባለ ሰርግ ያገባት ሚስቱን መፍታቱን ሰማሁ።ቶሎ የታሰበችኝ ውዴ ነበረች።
ምነው ሰርግ አብሮ መኖርን ሊያጠነክር የማይችል፤ ፍቅርን ሊጠብቅ የማይችል መሆኑን በዚህ በተረዳች አልኩኝ።አልጋዬ ላይ ተንጋልዬ ስለ ውዴ እያሰብኩ በሬ ተንኳኳ።ለአንድ ወር ከሳምንት የራቀችኝ ውዴ ነበረች።ሳንነጋገር ተቃቀፍን።ከደቂቃዎች በኋላ ተላቀቅንና ቀና ብላ እያየችኝ “ትቼዋለሁ” አለችኝ።ምኑን ስላት “ሰርጉን” ስትለኝ እንደ አዲስ ተቃቀፍን።….አበቃ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም