በበይነ መረቦችና ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ለጥቃት የሚያነሳሱ፣ ግድያንና መፈናቀልን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶች ሲተላለፉ ይስተዋላሉ። በድርጊቱ ተራ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ዜጎችን የሚመሩ የመብት አራማጆች ነን ባዮች ህዝቡን እርስ በርስ በማጋጨት አንዳች “ጥቅም” ለማግኘት ሲዳክሩ ይስተዋላሉ።
እነዚሁ የህብረተሰብ አንቂ ነኝ ባዮች ጭራሽ የበይነ መረቡ አልበቃ ብሏቸው የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥርዓትን ባልተከተለ እና ከፍለው ባሰማሯቸው ጥቂት ሆድ አደሮች በአደባባይ ሲያሰድቡ እና የጥላቻ መርዝ ሲረጩ ነው የሚውሉት።
ይህ ብቻ አይደለም የአንዳንድ የመንግሥት ሃላፊዎችም ንግግር ከአውድ ውጭ እየተወሰደ በተፈጠረው መከፋፈል ላይ ቤንዚን በእሳት ላይ እንደ ማርከፍከፍ ሆኖ የጥላቻ መፈራረቅና መቀጣጠል ምክንያት ሆኗል። ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልሶች በሙሉ ጥላቻንና ጥቃትን ምላሽ ያደረጉና ሃይ ባይ ያጡ መልዕክቶች ለፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት እየሆኑ ነው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ግድያ፣ ጦርነት፣ ዘር ማጥፋት እንደተለመደ ነገር ተደርጎ መቀስቀሱ ቀጥሏል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቷ ውስጥ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ተፈናቅለዋል፤ በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ እንዲሁም ለብዙዎች በስጋት ውስጥ ለመኖር ምክንያት እየሆነ ይገኛል።
የተለያዩ ሰብአዊ መብት ድርጅቶችና እንዲሁም የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጥናት እንደሚያሳየው ለዚህ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የጥላቻ ንግግር ነው። ይሄንን ድርጊት ለመከላከልና ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ደግሞ “የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን” ለመከላከል አዋጅ ወጥቷል።
ይሁን እንጂ የዚህ ጠንካራ አዋጅ ብርቱነቱ ወረቀት ላይ ብቻ ሆነ። በሰው ደም እና ሞት የሚነግዱ “እነ ነውር ክብሩን” አደብ ለማስያዝ “የወረቀት አንበሳ” የሆነው ሕግ በተግባር በማዋል ጡንቻው በአደባባይ ሊታይ ይገባል።
ግለሰቦች የሚሰሩት ወንጀል ችላ በማለት ሀገሪቱ ከአለችበት ሁኔታ ጋር በማያያዝ “ ለአንድነት፣ ለመቻቻል ለአገራዊ መግባባት” እየተባለ ነውራቸውና የሚሰሩት ወንጀል ዝም እየተባለ አያሌ ንፁሃን ዜጎች እያለቁ ነው። ታዲያ በነፃነት እና በመፋነን መካከል ያለው ልዩነት ያልገባውን ግለሰብ ትምህርት ለመስጠት የሕግ ልጓም ሊበጅላቸው ይገባል።
ከዚህ በፊት የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሞግቱት ጋዜጠኞችና የመብት አራማጆች ነፃነቱ የሚጠይቀውን ሃላፊነትና ጨዋነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ይናገራሉ። “አፍ ያመጣው ነገር ሁሉ መጽሐፍ ተገቢ አይደለም” ይላሉ። አንድ ሰው ሲናገርም ሆነ ሲጽፍ ተጠያቂነት እንዳለው ሊነገር ይገባል። በማህበረሰብ ውስጥ ዋና ሥራ ዋነኛው ነገር ህዝብን ማቀራረብ ስለሆነ መከባበርና መቻቻል ነው። ይህ ባህል ከሆነ ደግሞ ከሕግ ይልቅ ባህል አጽንኦት ቢሰጠው ጥሩ ነው ብለው መከራከሪያ ሀሳባቸውን ይገልፃሉ። ጨዋነት የሚፈጠረው ሕግ በማውጣት በመተግበር ሳይሆን መከባበርና መቻቻልን ባህል በማድረግ ነው ይህ ከሆነ ሕግ ማውጣት ያን ያክል አስፈላጊ አለመሆኑን ያስረዳሉ።
ይህ ምሁራኖች ያነሱት ሃሳብ እውነት ሆኖ ሳለ ሕጉ በተግባር ይዋል እያልኩ የምሞግተው እኮ ሌሎች ማህበራዊ ተቋማት ስለከሸፉ ነው። ይልቅ ሕጉን በተግባር እያዋሉ የጥላቻ ንግግርንም ሆነ ሃሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት እየተከላከሉ በተያያዘ ደግሞ ማህበረሰቡ ያሉትን መልካም የጋራ እሴቶች ማዳበርና ተገቢ ይመስለኛል። ነገር ግን ጉዳዩ ከዚህ የዘለለ ስለሆነ እና እነዚህ ግለሰቦች በአገኙት አጋጣሚ የሚረጡት መርዝ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ስለሆነ የሕግ ተጠያቂነትን ማስፈን አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።
ምንም እንኳ ዲሞክራሲ ሂደት ቢሆንም ሂደቱም በአንድ ምሽት እንደማይመጣ መታወቅ አለበት። በመሆኑም የዲሞክራሲ ሂደት ለማስቀጠል የጥላቻ ንግግር ልክ እንዲኖረው ሕጉ ጥርስ ሊያወጣ ይገባል። የሚያስማማና ሁሉም የእኔ ነው የሚለውና ተቀባይነት ያለው ሕግ የወጣ ሲሆን ይኸው ሕግ በተግባር ሊውል እንደሚገባ ሊሰመርበት ይገባል። ይህ ካልሆነ እነዚህ የሞት ነጋዴዎች “ያልተፈጠረውን ተፈጠረ” ያልሆነውን ሆነ፤ “እገሌ እንዲህ ነውና እንዲያ ነው” በማለት አገሪቱን እና ህዝቡን ለአላስፈላጊ ጥፋት ይዳርጉታል።
ሕጉን በተግባር በሚል የሚገኘውን የሰላም አየር እያጣጣሙ ደግሞ ጎን ለጎን ይመለከተኛል የሚል የትኛውም ተቋም ሆነ ግለሰብ ሁሉንም ነገር ለመንግሥት መተው ሳይሆን የሲቪል ማህበራቱ፣ጦማርያን፣ ጋዜጠኞችና የሕግ ባለሙያዎች በማወያየት የጋራ ማድረግ ተገቢ ነው። ህጉ ይተግበር ሲባል ደግሞ ይህንን ክፍተት መንግሥት እንደመጨቆኛ መሣሪያ እንዳይጠቀምበት መከታተል ሌላኛው ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
በአጠቃላይ ሁሉም ዜጋ በሰላም ወጣቶ የመግባት ነፃነት እንዲኖረው፤ የንፁሃን ደም በከንቱ ከመፍሰስ ለመታደግ፤ መፈናቀልን ለማስቆም፤ ህጉ ጥርስ ሊያወጣ ይገባል በሚል አሳስባለሁ። ከባድ ዋጋ እንደ አገርም ሆነ እንደ ግል ከመክፈላችን በፊት ከወዲህ አንድ ሊባል ይገባል። የሌለውን ያልረቀቀውን ሕግ ሳይሆን በተግባር ያለውን የጸደቀውን ሕግ እንኳን በተግባር ብናውል የሚማረው በሰላም ተምሮ የሚሰራው በሰላም ሰርቶ በደህነት ወጥቶ ይገባል። ስለዚህም በወረቀት ላይ ያለውን ህግ በተግባር በዋል አገርን ዜጋንም ማዳን ይገባል። ሰላም
የልቤ ደርሶ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2013