አዲስ ዘመን ድሮ ግንቦት 1
በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ19 46 እና19 47 እንዲሁም በ19 60 የታተሙ የአዲስ ዘመን ጋዜጦች ይዘዋቸው ከወጡ ዘገባዎች መካከል ተናባቢ ናቸው ብለን ያስብናቸውንና በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎችንና ወጣ ያሉ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል።
የመሬት ጉዞ
በ፲፱፻፵፮ ዓ.ም በጥቅምት ወር በመጀመሪያው ላይ ከወረይሉ ምክትል ወረዳ ክሬ ወደ ሚባለው መሬቱ ከነአዝመራው ከነሰብሉ ጋር አንድነት ተንሸራቶ ወርዶ በቶ በሚባለው ወንዝ ላይ ተዘረጋ።
ያዝመራው ባቤቶች መሬት ከሔደበት ሔደው አዝመራውን ለመሰብሰብ በላዩ ላይ የተሰባሰቡትን ገበሬዎቻቸውን፤ በብዛት አሰማርተዋል። ከዚሁ መሬት ላይ የሚታየው አዝመራ ፤ገብስ፣ ጤፍና ኑግ ነው፤ከዚህም በቀር በብዙ የሚቆጠር የእህል ክምር በላዩ ላይ ይታያል። ውድማውን ከዚያው በማዘጋጀት ላይ ናቸው። በእነዚህ በሁለቱ ምክትል ወረዳዎች መካከል በቶ የሚባል ትልቅ ወንዝ አለ። ተነስቶ ሔዶ ወዲያ ማዶ ካለው ገደል ጋር ገጥሞ በጅረት የሚጓዘውን ውሃ ስለዘጋው፤ የተከተረው የባህር ግምት ቁመቱ ከ፩ ኪሎ ሜትር በላይ ይሆናል፤ በጎን ስፋት እስከ ሦስት መቶ ሜትር ሳይጠጋ አይቀርም።
የሔደው መሬት ቁመቱ በግምት አምስት መቶ ሜትር ይጠጋል። በጎን ስፋት አራት መቶ ሜትር ይደርሳል። የሄደውም መሬት ከደቡብ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ነው። ውሃው ግን አስራ ሁለት ቀን ያህል ከተከተረ በኋላ በላዩ ላይ ሳይፈስ እንደተንደረበበ በደቡብ በኩል በገደሉና በደንጋዩ መካከል እየሸረሸረ እንደሚፈላ ምንጭ እየሆነ በየጫካውና በየዳገቱ ላይ ሲወርድ ይታያል። ባካባቢው የሚገኘው ሕዝብ ጠበል ፈለቀ በማለት አስፋፍቶ ያወራል። የኔን አስተያየት የባህሩ ስሜት ነው በማለት አሳርፌዋለሁ። ለሕዝቡ እንግዳ ታሪክ ሆኖበት ጉድ እናያለን በማለት ከየአውራጃው የሚመጣ እግረኛና ፈረሰኛ የሚደርገው እሽቅድድምና የሕዝብ ብዛት ግምቱ ከመጠን በላይ ነው።
በየነ አቻሜ
(ታኅሳስ 17 ቀን 19 46 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን )
በዝናም ምክንያት ተራራ ተንዶ
ሰዎችና ከብቶች ሞቱ
በዚህ ጠ.ግዛት በከንባታ አውራጃ በዴንሣ ጥምባሮ ም.ወረዳ ግዛት በአቶ ጽደቀ ጋረዴ ባላባትነት ውስጥ በነሐሴ 24 /46 ዓ.ም ለ25 አጥቢያ ሌሊቱን በዘነመው ኃይለኛ ዝናም ጦና ሸለቆ የተባለው ተራራ ተንዶ ፤ከዚሁ ጋራ ሥር የሚኖሩ የቤቱ ጌታ አንቃሞ ፣ ፪ኛ ሚስቱ በቦሬ በዶሬን ፣፫ኛ ልጁን ሸክሜ አንቃሞ የሚባሉትን ሰዎችና ከበረት የነበሩት ፲፩ የቀንድ ከብቶች ፣ሁለት ባዝራ ፈረሶች፣ ፭ በጎች በናዳው የጋራ አደጋ ሲሞቱ ፤አንድ ዶሮና አንድ ባዝራ ፈረስ ከዚሁ አደጋ ድነው ታይተዋል። ከተናደውም ጋራ ሥር አንድ ምንጭ ፈንድቶ መታየቱን ያውቁት ዘንድ እገልጽልዎታለሁ።
ማኅተም የአርሲ ጠ.ግዛት ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት።
ፊርማ ሻለቃ አበበ ወልደሥላሴ የአርሲ ጠ.ግዛት ፖሊስ ም.ዋና አዛዥ
(ጥቅምት 13 ቀን19 47 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን )
በእንቀሎ ተራራ ላይ እሳተ ገሞራ ፈነዳ
አሩሲ ኢዜአ፤ በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ በለሐቢሎ ወረዳ ከሚገኘው የእንቅሎ ተራራ ውስጥ በስተደቡብ በኩል እሳተ ገሞራ ስለፈነዳ አያሌ የሆነ ፍል ውሀ ከተራራው ወጥቶ የስምጥ ሸለቆን በጎርፍ አጥለቀለቀው።
ከሥፍራው ዘግይቶ የደረሰን ወሬ እንደሚያስረዳው ከተራራው ውስጥ የፈነዳው እሳተ ገሞራ ሚያዝያ ፪ ቀን ፲፱፻፷ ዓ.ም ሲሆን ፤ በዚሁ እሳተ ገሞራ ምክንያት ተራራው ሲሰነጠቅ ኃይለኛ የሆነ ድምጽ በመሰማቱና መሬት በመንቀጥቀጡ በአካባቢው በሚኖረው ሕዝብ ዘንድ ታላቅ ፍርሃት አሳድሮ ነበር። በዚሁ በፈነዳው እሳተ ገሞራ ከተሰነጠቀው ተራራ መካከል የወጣው ፍል ውሀ ጎርፍ ሸለቆውን በመከተል አካባቢው የሚገኘውን የጦናን ሸለቆ አጥልቆት ነበረ። ይኸው የፍል ውሀ ጎርፍ ደን ሆኖ የኖረውን እንጨት እየነቃቀለና ትልልቅ የአለት ድንጋዮችን እያንከባለለ ወደ ዋቢ ወንዝ ወስዶ ተቀላቅሏል። እንዲሁም በዚሁ ዕለት ወደ ዕለት ተግባሩ ይሰማራ የነበረው የአካባቢው ሕዝብ በጎርፉ ምክንያት ለመሸጋገር ሳይችል መቅረቱ ይነገራል።
ይሁንና ይኸው ተራራ በፈነዳ ጊዜ በሰውና በእንስሳት ያደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ባላንባራስ ወልደ አማኤል አብን ገልጠዋል።
(ሚያዝያ 24 ቀን 19 60 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያምወንድሙ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2013