አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ኢትዮጵያና ጣሊያን በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምን ለማምጣት በጋራ እንደሚሰሩና፣በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ለሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ለሚገኙት የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ትናንት በቤተመንግስት ባደረጉላቸው የእራት ግብዣ ላይ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣በንግድ፣ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ በማጠናከር፣በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ለማጠናከር ከጣሊያን ጋር እንደምትሰራና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውንም ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ-ጣሊያን የግንኙነት ምዕራፍ የረጅም ጊዜ ታሪክ አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉት ውይይትም የቆየ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚረዳ መሆኑንና ባደረጉት ውይይት መደሰታቸውንም ተናግረዋል፡፡በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ መኖሩን በመጠቆም የጣሊያን ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ታሪካዊ ስምምነት ባደረገች ወቅት ጉብኝታቸው የመጀመሪያ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና በሌሎችም የጋራ ጥረት በሀገሪቷ የመጣውንም ለውጥ አድንቀዋል፡፡ሀገራቸው ለውጡን በመደገፍ አጋር እንደምትሆን ተናግረዋል፡፡የጣሊያን የንግድ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡ ጣሊያን ኢንቨስት ከምታደርግባቸው አምስት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡
የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ሲገቡ ለክብራቸው መድፍ ተተኩሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ በ2019 ጣሊያንን እንዲጐበኙ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋብዘዋቸዋል።