በተለያዩ የውጪ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ በሲቪል ምህንድስና ባለሙያነት ተቀጥረው ሰርተዋል:: በሰሩባቸው በነዚህ ድርጅቶች ውስጥም በሲቪል ምህንድስናው ዘርፍ በቂ ልምድና አውቀት አግኝተዋል:: ይህንኑ ልምድና እውቀታቸውን ተጠቅመውም የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን የሚያስመጣ የራሳቸውን ኩባንያ ለማቋቋም በቅተዋል:: ከአስመጪነቱ ጎን ለጎንም ወደ ላኪነቱ ጎራ በመሰለፍ የቅባት እህሎችን ወደ ውጪ መላክ ችለዋል::
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከውጪ የሚያስገቧቸውን የኮንስትራክሽን ማሽነሪ እቃዎችን በሀገር ውስጥ በማምረትና በመገጣጠም በተመጣጣኝ ዋጋ ለሀገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ህልም ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ:: እኚህ በትብብር መስራትን መርሃቸው ያደረጉና ባለሙያዎችን አሰባስበው ለውጤት እየተጉ ያሉ ነጋዴ የ‹‹ማስ አፍሮ ዩ ትሬዲንግ›› ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መታፈሪያ ወንድአፍራሽ ናቸው።
አቶ መታፈሪያ ትውልድና እድገታቸው ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ ነው:: የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሸዋሮቢት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት በማምጣታቸውም በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ተመድበው ትምህርታውን በሲቪል ምህንድስና ከተከታተሉ በኋላ በ1995 ዓ.ም በዲግሪ ተመርቀዋል::
በተመረቁበት የሲቪል ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ መጀመሪያ ግራጋዶስ በተሰኘ የጃፓን የመንገድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ለአራት ዓመታት አገልግለዋል:: በመቀጠልም በሌላ የህንድ የመንገድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ገብተው በሙያቸው ሰርተዋል:: በሌሎችም የውጪ ሀገራትና የሀገር ውስጥ የግል የመንገድ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው በሙያቸው እስከ 2009 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ አገልግለዋል:: በትርፍ ጊዚያቸውም የማማከር ስራዎችንም ሰርተዋል::
ከበፊት ጀምሮ የራሳቸውን ቢዝነስ የመጀመርና ኢንቨስተር የመሆን ሃሳብ የነበራቸው አቶ መታፈሪያ፤ ተቀጥሮ የመስራቱን ነገር እርግፍ አድርገው ትተው ቢዝነሳቸውን ለመጀመር ቢንደረደሩም በጊዜው የነበረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ለዚህ የሚጋብዝ አልነበረም:: ይሁን እንጂ በሂደት ተስፋ እያዩ በመምጣታቸው የራሳቸውን ኩባንያ ማቋቋም እንዳለባቸው ከውሳኔ ላይ ደረሱ:: አሜሪካና ቻይና በመሄድ ለአንድ አመት ጥናት ሲያደርጉ ከቆዩ በኋላ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ጭምር በማሳተፍ የንግድ ፍቃድ አውጥተው ‹‹ማስ አፍሮ ዩ›› የተሰኘና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከውጪ ሀገር የሚያስመጣ ኩባንያ በ2010 ዓ.ም መሠረቱ::
ኩባንያውን ሲመሰርቱ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ ዋነኛ አላማቸው አድርገው የተነሱት አቶ መታፈሪያ፤ በቅድሚያ ቢሮ በማደራጀት የድንጋይ መፍለጫ፣ ስካቫተር፣ ሎደር፣ ግሬደር፣ ቡልዶዘርና ሌሎችንም የኮንስራክሽን ማሽነሪ እቃዎችን ከውጪ ሀገር አምጥተው በሀገር ውስጥ ማከፋፈል ጀመሩ:: ሆኖም ማሽነሪዎቹን ከውጪ ሀገር አስመጥቶ በሀገር ውስጥ ማከፋፈሉን እምብዛም አርኪ ሆኖ ስላላገኙት ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ጋር ስምምነት በማድረግ የቅባት እህሎችን ወደውጪ ሀገራት መላክ ቀጠሉ::
ከወለጋና ሁመራ አካባቢዎች ሰሊጥ፣ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን ወደ ቻይናና ኢንዶኔዥያ መላክ ቻሉ:: በተለይ እነዚህን የቅባትና የጥራጥሬ እህሎች ወደ ቻይና ሲልኩ በምላሹ ሌሎች እቃዎችን ከቻይና መግዛት አስቻላቸው::
ለዚህ ስራ አዲስ በመሆናቸው፣ የተከማቸ ካፒታልም ስላልነበራቸውና በቂ ብድርም ባለማግኘታቸው የአስመጪነትና ላኪነት ስራው እንዳሰቡት ሊሄድላቸው አልቻለም:: አብዛኛዎቹ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችም በብዛት የሚገኙት በወለጋ፣ ሁመራና ጎጃም አካባቢ ብቻ በመሆኑና በነዚሁ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የፀጥታ ችግር በመኖሩ ምርቱን እንደልብ ወደውጪ ሀገር መላክ ተሳናቸው::
ከዚህ ችግር በመነሳትም ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ሙሉ ትኩረታቸውን ቢሮና ሠራተኛ ማደራጀት፣ የፋብሪካ ቦታ መውሰድ፣ ግንባታ ማካሄድ፣ በቂ የሆነ ባለሙያ መመደብ፣ ቀደም ሲል የነበሩ የውጪ ሀገር ደንበኞችን ማቆየትና እንዲታገሱ የማድረግ ስራ ላይ አደረጉ:: ኩባንያው አብዛኛዎቹን ስራዎች የሚያከናውነው በኪራይ ከመሆኑ አኳያም ከኪራይ የሚላቀቅበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየሰሩ ይገኛሉ::
በ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር መነሻ ካፒታልና በአምስት ሠራተኞች ሥራውን የጀመረው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 22 ሚሊዮን ብር ደሰርሷል:: አርባ ለሚሆኑ ዜጎችም ቋሚና ጊዚያዊ የስራ እድል ፈጥሯል:: በመንግስት በኩል ድጋፍ ከተገኘ በተለይ ደግሞ በንግድ ባንክ በኩል የገንዘብ ብድር ከተመቻቸ ኩባንያውን ከዚህ በላይ በማሳደግ ለበርካታ ዜጎች የስራ አድል ለመፍጠር ግብ አስቀምጧል::
የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከውጪ ሀገር ከማስመጣት ይልቅ በሀገር ውስጥ ለማምረትና ለመገጣጠም የሚያስችላቸውን ፋብሪካ የማቋቋም ትልቅ ሕልም ያላቸው አቶ መታፈሪያ፤ ይህንኑ ሕልም እውን ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ህንፃ ገንብተው በማጠናቀቅ የማደራጀት ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ:: ለዚህም አብረዋቸው ከሚሰሩ በርካታ ኩባንያዎች ጋር ንግግር አካሂደዋል:: በቂ ሙያተኛ ካገኙም የማሽነሪ መገጣጠሙን ስራ ወደሀገራቸው የማሸጋገር ፍላጎቱ አላቸው::
ቀደም ሲል ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገቡት የነበረው ትላልቅ የኮንስትራክሽን ማሸን ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪና ጊዜ የሚፈጅ ከመሆኑ አኳያም በቅድሚያ ተፈታቶ ወደሀገር ውስጥ የሚገባበትንና በሀገር ውስጥ የሚገጣጠምበትን ሁኔታ ለመፍጠርም አቅደዋል:: ከውጪ ሀገር የኮንስትራክሸን ማሽነሪ አምራች ድርጅቶች ጋር በመሆን ማሽኑ በጋራ በሀገር ውስጥ የሚመረትበትን ሁኔት ለመፍጠርም ሃሳቡ አላቸው::
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ኩባንያቸው ከኮንስትራክሽን ማሽነሪ ንግድ በተጨማሪ ማሽኖችን ወደመገጣጠምና ማምረት ስራ የመሸጋገር እቅድ ይዟል:: ወደ ምግብ ማቀነባበሪያ የሥራ ዘርፍ በመግባትም በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት የመሙላት ፍላጎትም አለው:: በዚሁ ዘርፍ ከመንግስትና ከባለሃብቶች ጋር ተደጋግፎ የመስራት ሃሳብም ነድፏል:: ከቅባት እህሎች በተጨማሪ ቡናን በማቀነባበር ወደ ውጪ ሀገር የመላክና በማዕድን ንግድ ውስጥም የመግባት ሰፊ እቅድ አለው::
በዚህ አጋጣሚም ኩባንያው ሰዎች በማዕድን ማውጣትና ንግድ ስራ ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መንግስት በረጅም ጊዜ የሚመለስ ብድር ማመቻቸት እንደሚገባውና በማዕድን ማውጫ አካባቢዎች ላይ በቂ ደህንነት እንዲኖር የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ይጠቁማል::
በአስመጪነትና ላኪነት ቢዝነስ ውስጥ አራት ዓመታትን ያሳለፉት አቶ መታፈሪያ፤ ወደ ውጪ ሀገራት የቅባትና የጥራጥሬ እህሎችን ሲልኩ የዋጋ ንረት ችግር እንደሚያጋጥማቸውና በግላቸው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ማነቆ እንደሆነባቸው ይናገራሉ:: በዚህ ረገድም በተለይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ጠንከር ያለ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ:: መንግስትም አንዳንዴ ጣልቃ ገብቶ ዋጋውን ማረጋጋት እንደሚጠበቅበት ያመለክታሉ:: ይህ ከሆነ የውጪ ምንዛሬ እጥረት እንደማያጋጥምና ሁሉም ላኪዎች እኩል ተጠቃሚ የመሆን እድል እንዳላቸው ያስረዳሉ::
በሌላ በኩል ደግሞ አቶ መታፈሪያ የኮንስትራክሽን እቃዎችን ወደሀገር ውስጥ ሲያስገቡ በባንክ በኩል የውጪ ምንዛሬ እንደማያገኙም ገልፀው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት በቂ የውጪ ምንዛሬ እንዲኖር በጥቁር ገበያ በኩል የሚንቀሳቀሰውን ዶላር ማስቆም እንዳለበት ያመለክታሉ:: አስመጪዎችም ገንዘባቸው ከባንክ ውጪ እንዳይሰራ ቢደረግ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደሚቻል ያስረዳሉ:: ሰዎች የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከሀገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲገዙ መበረታታት እንዳለበትም ይጠቅሳሉ:: ከተቻለም የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ጨምሮ ሌሎች እቃዎች በሀገር ውስጥ የሚመረቱበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ይጠቁማሉ::
‹‹በአስመጪና ላኪነት ስራ ዘርፍ ውጤት ለማምጣት ብዙ ይቀረኛል›› የሚሉት አቶ መታፈሪያ፤ ስራው በራሱ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድርና የአእምሮ እረፍት የማይሰጥ በመሆኑ እንዲህ በቀላሉ ውጤት የሚመጣበት እንዳልሆነ ይናገራሉ:: ለስራው በሚደረገው ትጋት ልክ በመንግስት በኩል የሚደረገው ማበረታቻም ዝቅተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ:: ስራውን ዳር ለማድረስ ግን በእልህና በትጋት እየሰሩ እንደሚገኙ ይገልፃሉ::
የአስመጪነትና ላኪነት ስራው ይቀራል እንጂ የኮንስትራክሽን ማሽኖችን የመገጣጠምና የማምረት ስራው ግን የማይቀር መሆኑንም ተናግረው፤ ይህም በቀጣይ ሀገሪቱ ለኮንስትራክሽን ማሽኖች የምታወጣውን የውጪ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይገልፃሉ:: ለዚህም መንግስት በውጪ ሀገር የሚመረቱ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚጥሩ ባለሙያዎችን መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባው ያሳስባሉ:: ፖለቲካና ቢዝነስ መለያየት እንዳለባቸውም ይገልፃሉ::
በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችም የኮንስትራክሽን ማሸነሪዎችንና ሌሎችንም እቃዎች ከውጪ ሀገራት አስመጥተው በሀገር ውስጥ ከማከፋፈል ይልቅ ማሽነሪዎቹ እዚሁ የሚገጣጠሙበት አሊያም ደግሞ የሚመረቱበትን መንገድ ቀይሰው ቢንቀሳቀሱ ከራሳቸው አልፍው ሀገራቸውንም ጭምር መጥቀም እንደሚችሉም ያስረዳሉ:: ከውጪ ሀገራት እነዚህን እቃዎች የሚያስመጡ ኩባንያዎችም እቃዎቹን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው ያሳስባሉ:: ባለሀብቶችም ትርፋ ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን ስራን አስፍቶ የመስራት ልምድ ማዳበር እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ::
መንግስትም ህዝቡን ወደ መሀል ከተማ ብቻ መሰብሰብ እንደሌለበትና ከዚህ ይልቅ ሰዎች በየአካባቢያቸው የስራ እድል ተፈጥሮላቸው የሚሰሩበትን ስልት መቀየስ እንዳለበት ያመለክታሉ:: በመላው ሀገሪቱ ሁሉ ቢዝነስ እንዳለ ለህብረተሰቡ በማስተማር ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚቻል መገንዘብ እንዳለበትም ይገልጻሉ።
በቀጣይ ሌሎችም በአስመጪና ላኪነት የስራ ዘርፍ ብሎም በሌሎች የቢዝነስ መስኮች በመሳተፍ ሰርተው ውጤታማ መሆን ለሚፈልጉ ሁሉ ውስን አቅም ቢኖራቸው እውቀቱ እስካላቸው ድረስ በጋራ ተደራጅተው የፈለጉትን ቢዝነስ መስራት እንደሚችሉ ይመክራሉ። ሰዎች በተደራጁ ቁጥር የገንዘብ አቅማቸውም የዚያኑ ያህል ስለሚጎለብት ውጤት ለማምጣት ብዙም እንደማይቸገሩ ይጠቁማሉ:: ስራቸውን በትብብርና በፍፁም ቀናነት የሚያከናውኑም ከሆነ ከሚያገኙት ትርፍ እኩል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ይጠቅሳሉ:: የሚያቋቁሙት ትልቅ ኩባንያ ከራሳቸው አልፎ ለልጆቻቸው ብሎም ለሀገር የሚተርፍ ሀብት እንዲሆን በጋራ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2013