‹ቁልፍ ተራ፣ ሸራ ተራ፣ ምናለሽ ተራ፣ ጭድ ተራ፣ ጠርሙስ ተራ፣››… ስንቱ ይጠራል፤ ይደረደራል። የመርካቶ ገበያ ቦታዎች ተራ ተዘርዝሮ አያልቅም። በዚህ ታላቅ በአፍሪካ ታዋቂ በሆነው መርካቶ ገበያ ምዕራብ ሆቴልን ተጎራብተው ከሚገኙት የገበያ ስፍራዎች ሁሉ እውቅናው ከፍ ያለው ‹‹ምናለሽ ተራ ›› ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ። ምን አለሽ ተራን ልጅ አዋቂው፤ ምሁር መሀይሙ ሳይቀር አሳምሮ ያውቀዋል፤ ይገበያይበታል። ሌላው ቀርቶ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል የመጡና አንዳች ነገር አጥተው የተቸገሩ የውጪ ሀገር ዜጎች ሳይቀሩ ምንአለሽ ምንም እንደማታጣ ተማምነው ጎራ ብለው ያሰቡትን ይሞላሉ።
ማንኛውንም አሮጌ ዕቃዎች፣ ተፈላጊ እና በገበያ የማይገኙ ብሎንጅ ጨምሮ ቁሳቁሶችን በጉያዋ አቅፋለች። የተለያዩ ኬብሎች፣ ብረት ድስቶች ፣ ጠርሙሶች፣ ሰዓት፣ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና ሌሎች መለዋወጫዎች፣ ካልሲንና እዚህ ቦታ ሊገኝ አይችልም ተብሎ የሚገመትን የውስጥ ሱሪን ጨምሮ ልባሽ ልብሶች፣ ጫማዎች የፈለጉትን ሁሉ ምናለሽ ተራ ማግኘት ይቻላል። ምን አለሽ ተራ ምንም የሌለ ነገር የለም። በዓለም ተፈልጎ የታጣ መርካቶ ምን አለሽ ተራ ውስጥ ይገኛል ቢባል ውሸታም ያሰኝ ይሆን?።
በዚሁ የገበያ ቦታ አግኝተን ያነጋገርነውና በአሮጌ ልብስ ሽያጭ የተሰማራው ወጣት ተስፋዬ ሙሉቀን በምን አለሽ ተራ ሁሉም ነገር ለመገኘቱ ምክንያት የሆነውን በኩራት ሲገልፅ ‹‹ዕድሜ ለቁራሌው›› ብሎናል። ወጣቱ እንዳለው ቁራሌው ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሰበሰበውን የሚያራግፈው በምን አለሽ ተራ ነው። ቁራሌው ብቻ ሳይሆን ቡትት ለብሰው የአእምሮ ችግር ያለባቸው እስኪመስሉን በየጎዳናው ሀይላንድና ያገኙትን ፕላስቲክ ሁሉ እየሰበሰቡ በሰፊና ትልቅ ማዳበሪያ ሲከቱ የምናስተውላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎችም ሲሰበስቡ የዋሉትን የሚያስረክቡት ለምናለሽ ተራ ነጋዴዎች ነው።
እሱም አንድ እግር ካልሲና የውስጥ ሱሪ ጨምሮ የተለያዩ አሮጌ ልባሾችና ጫማዎችን የሚረከበውም ከሁለቱ አቅራቢዎቹ ነው። ከነዚህ ውጪ ማንኛውም ሰው ከጥቃቅን ብሎኖች ጀምሮ ያመጣውን አሮጌ ዕቃ ይገዛል።
ወደ ምናለሽ ተራ መግቢያ ላይ ‹‹ምንድነው የያዝሽው? የሚሸጥ ነው የሚሰራ ? ›› በሚል ጥያቄ ልቤን ሲያወልቁኝ የነበሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ትዝ አሉኝ። እኔ አልገባኝም እንጂ ያንጠለጠልኩትን ላስቲክ አይተው የሚሸጥ ነው የሚሰራ ? በማለት እየጠየቁኝ ነበር። ለማንኛውም ከወጣቱ እንደተረዳሁት ከሆነ ለጥያቄው ምን አገባህ ወይም ምን አገባሽ የሚል ምላሽ መስጠት ‹‹ፋራ›› ያሰኛል ። ምልልሱ ከበዛም ፀብና ዱላ ሊያስከትል፣ መተናነቁ ከቀጠለ ደግሞ የያዘውን ዕቃ እስከመነጠቅ የሚደርስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በመሆኑም ወደ ምናለሽ ተራ የገበያ ቦታ ሲመጣ ትዕግስትና ጨዋነት ወሳኝ ነው።
ወጣት ተስፋዬ የገበያውን ሁኔታ ሲገልጽልን ‹‹እግዚአብሄር ይመስገን ጥሩ ነው›› ብሎናል። ‹‹ልባሽ ፓንትና ካልሲውም ይሄዳል። እንደ አቅሙ የሚገለገልበት የሕብረተሰብ ክፍል አለ። በተለይ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ አንድ እግር ካልሲ እንዲሁም ጫማ ጠፍቶባቸው በመጡ ሰዎች ተመሳሳዩ እጅግ ተፈላጊና ከምናለሽ ተራ ውጪ የማይገኝ በመሆኑ ከአዲሱ ጫማና ካልሲ ባልተናነሰ ዋጋ ይሄዳሉ።›› ሲል ነው ያጫወተኝ። እሱ በስራው ደስተኛ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ሰርቶ ባገኘው ገንዘብ እናትና አባቱን ጨምሮ ስድስት እህትና ወንድሞቹን ማስተዳደር ስላስቻለው ነው።
ወይዘሮ ዙልፋ ሙብአረክ ሌላዋ የምናለሽ ተራ ነጋዴ ናቸው። በምን አለሽ ተራ መዋል ከጀመሩ 35ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል። ብረት ድስት፣ ጭልፋና ሌሎች አሮጌ ዕቃዎችን በሙሉ ለገበያ ያቀርባሉ። ዕቃዎቹ የሚቀርቡት ዝም ብለው ሳይሆን ታጥበውና ተጨማሪ እሴት ታክሎባቸው ነው። ሰባት ልጆቻቸውን የሚያስተዳድሩትም ከዚሁ በሚያገኙት ገቢ ነው። በደርግ ጊዜ ስኳርና ጨውን ጨምሮ ሌሎች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከህብረት ሱቅ በማውጣት እየሸጡ ገቢያቸውን ይደጉሙ ነበር። ከዚያ በኋላም አሮጌ ቁሳቁሶችን ገዝተው አጥበውና አሳምረው በመሸጥ ነጋዴ የሚለውንም መጠሪያ አግኝተዋል።
በአሮጌ ገመድ ንግድ ሥራ የተሰማሩት ደግሞ አቶ አሸናፊ ኃይሌ ይባላሉ። 2 ነጥብ 5፣ ሦስት በአራት፣ ሁለት በአራት የሚባሉ ገመዶች (ኬብሎችን) በተለይም የአምፖል ነጭ ገመድ ሲሸጡ አስተውለናል። ‹‹አሁን ላይ ማናቸውም ለምናለሽ ተራ ለገበያ የሚቀርቡ ዕቃዎች ዋጋ በመቶ እጥፍ ጨምሯል። በተለይ ኬብል በባለሀብቶች በመያዙና ሊለቀቅ ባለመቻሉ እጅግ ውድ ነው። ድሮ 20 እና 30 ብር ይሸጥ የነበረው ዛሬ ከመቶ ብር በላይ ነው የሚገዛው። አቅርቦት ካለመኖሩም በላይ በኮቪድ ምክንያት ገበያው ተቀዛቅዟል።›› ይላሉ። አሁን ላይ እየሸጡ ያሉት ቀደም ብሎ ገዝተው ያከማቹትን ነው። በምን አለሽ ተራ ምን ጠፍቶ ያሰቡት፣ የጠየቁት ሁሉ ይገኛል፤ ይቸበቸባል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 29/2013