ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራች አገር ናት። ወራሪ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር በመዳፋቸው ስር ሊያስገቧት አስበው ብዙ ሞክረዋል። መሰል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ካደረጉት ወራሪዎች መካከል አውሮፓዊቷ ኢጣሊያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።
እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም፣ ዓድዋ፣ የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት/ጦር በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ።
ጣሊያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከአድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪቃን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃንኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉስ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና ‹‹የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ›› በሚል ቅዠትና የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች። በመጨረሻም ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የሽንፈት ካባ በድል ለማካካስ በማሰብ በፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሊኒና ግበረ አበሮቹ እየተመራች በኢትዮጵያ ላይ አሰቃቂ ወረራ ፈጸመች። ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም አዲስ አበባን በመቆጣጠር፣ ለአምስት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዢዋ ለማድረግ ጥረት አድርጋለች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ታዲያ ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ እንድትቆይ ለአገራቸው ሉዓላዊነት የተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች የከፈሉት መስዋትነት ፈጽሞ የሚዘነጋ አይደለም። ዛሬ፣ ዕለተ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም፣ የኢትዮጵያውያን አርበኞች ድል 80ኛ ዓመት መታሰቢያ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ዓመታት ከከፈሏቸው እጅግ አስደናቂ መስዋዕትነቶችና ካስመዘገቧቸው በርካታ አንጸባራቂ ድሎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ እንመለከታለን።
መራራዎቹ መስዋዕትነቶች እና አንፀባራቂዎቹ ድሎች
ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ላይ የተቀዳጀችው ድል በቀላሉ የተገኘ አልነበረም። እጅግ ብዙ መራራ መስዋዕትነቶች ተከፍለውበታል። እነዚህ መስዋዕትነቶች እንኳንስ ለማየት ይቅርና ለመስማትና ታሪካቸውንም ለማንበብ ጭምር የሚዘገንኑ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ተጠቃሽ ነው። የኢጣሊያ ንጉሳዊ ቤተሰብ አባል ልደትን ምክንያት በማድረግ ‹‹ለነዳያን እርዳታ እሰጣለሁ›› ብሎ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥት የጠራቸው ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ፤ ለኢትዮጵያውያን የሰጣቸው ምጽዋት ሳይሆን አሰቃቂ ሞትን ነበር። አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ወጣቶች ከሌሎች ተባባሪዎቻቸው ጋር በመሆን በግራዚያኒ ላይ በፈፀሙት የግድያ ሙከራ ምክንያት ከ30ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ለአስከፊ ጭፍጨፋ ተዳርገዋል። ከዚህ ቁጥር የሚበልጡ ደግሞ ለአስከፊ ድብደባ፣ እስራት፣ ስቃይና ስደት ተዳርገዋል። በግንቦት ወር 1929 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትና ምዕመናን ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋም የሚዘነጋ አይደለም።
ሚያዚያ 3 ቀን 1931 ዓ.ም ከአምስት ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን አርበኞች መንዝ ውስጥ ‹‹አመፀኛ ዋሻ›› በተባለ ስፍራ በፋሺስት ኢጣሊያ የመርዝ ጭስ ታፍነው የተገደሉበት ለአገር ነፃነትና ክብር የተከፈለው መስዋዕትነትም ሌላው ማሳያ ነው።
ወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደ ርሰውን ግፍ ሲመለከቱ ልባቸው በከፍተኛ የሃዘን ጦር ተወግቶ ከአርበኞች ጋር በመሰለፍ አርበኞችን ሲያበረታቱና ሕዝቡም ለፋሺስት አስተዳደር ተገዢ እንዳይሆን ሲቀሰቅሱ የነበሩት ታላቁ የሐይማኖት አባት አቡነ ጴጥሮስ የተቀበሉት መከራና የከፈሉት መስዋዕትነት የሚያኮራም ጭምር ነው። ‹‹ … ይህቺ ክብሯን የደፈራችኋት አገር እኮ ‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች› የተባለላት ቅድስት አገር መሆኗን ታውቃላችሁ? ይህቺ የቆማችሁባት ምድር ለእብሪተኞች ረመጥ፣ እንደ እሳት የምታቃጥል መሆኗን ብታውቁ ኖሮ ምን ያህል ጥርሳችሁ በሃዘን እየተፋጨ በተንገጫገጨ ነበር። ግን ግብዝ ሆናችኋል፤ በኃይላችሁ ተማምናችኋል። እኔ የምፈራው የሰው ሰይፍ አይደለም። የእናንተ እብሪት፣ የእናንተ ጉልበት ትንሽ ጉም ነው፤ ነፋስ የሚበትነው። እና የፋሺስት ኢጣሊያን የበላይነት ከምቀበል ሞቴን እመርጣለሁ። ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የዘረጋችውን ቅድስት አገሬን እብሪተኛ ሲደቀድቃት እንዲኖር አልፈቅድም፤ እምነቴም በፍፁም አይፈቅድልኝም! … የኢጣሊያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ! የኢጣሊያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን! … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ! … ሞቴ አያሳፍረኝም። የምሞተው ለአገርና ለትልቅ ሕዝብ ነው!›› ያሉበት ንግግራቸው ለሐይማኖታቸውና ለአገራቸው የነበራቸውን ፍቅርና ክብር የሚያሳይ ቅዱስ ንግግር ነው። በስምንት ጥይቶች ተደብድበው ነፍሳቸው ስላልወጣች ጭንቅላታቸው በሦስት ተጨማሪ ጥይቶች እንደተመታ ታሪኩን ላነበበ ሰው የከፈሉትን መስዋዕትነት መራራነት ይገነዘባል።
በሰውነታቸው ስድስት ቦታዎች ላይ ተመትተው በከባድ የህመም ስሜት ውስጥ ሆነው ሲዋጉ የነበሩትና የጠላት ጦር ‹‹በወታደሮቼ ላይ ጉዳት አድርሷልና ተላልፎ ይሰጠኝ›› ብሎ ሲጠይቅ ‹‹ከአገሬ አፈር የሚደባልቅ ቤልጅግና ጎራዴ ይዤ እንጂ ጫት ተሸክሜ የምመጣ እንዳይመስልህ›› ብለው በመመለስ የጠላትን ጦር ድል ያደረጉት የወልወሉ ጀግና ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ጀግንነት የወገንን ደም ያሞቃል።
በአርበኝነት ትግላቸው ምክንያት ወደ ኢጣሊያ ተወስደው ታስረው የነበሩት፣ ከኢጣሊያ እስር ቤት አምልጠው ተዋጊ በማደራጀት የፋሺስትን ጦር በዚያው በሀገሩ ፋታ የነሱት፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ‹‹የኅብረት ኃይሎች/ጦር (Allied Powers)››ን ጦር እየመሩ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አስረው ሮም ከተማ የገቡት፣ በርካታ የጀርመን ከተሞችን ከናዚዎች ነፃ ያወጡትና በኢትዮጵያ ፈፅሞ የማይደራደሩት የኮሎኔል አብዲሳ አጋ የጀግንነት ተግባር እንዴት ተደርጎ ቢነገር/ቢፃፍ ይጠገባል?!
‹‹አገራችንን ምንም ቢሆን ጠላት አይገዛትም፤ ምድራችን በጠላት እግር አትረገጥም፤ በየበ ረሃችን እንመሽጋለን፤ እስከመጨረሻው የደም ጠብታና እስከመጨረሻው የነፃነት ጊዜ እንዋጋለን›› እያሉ በአድሮ ፆለሌ፣ ዓብይ ዓዲ፣ ማይጨው፣ ሲልዳ፣ ዓምደ ወርቅ፣ ጸለጌ፣ ድገርሻ፣ ተላላ፣ ጎቶቾ ቢላና በሌሎች ስፍራዎች በተደረጉ ውጊያዎች የፋሺስትን ጦር ድል ያደረጉት ሌተናል ጀኔራል ኃይሉ ከበደ፤ በመጨረሻ ወለህ ላይ ወድቀው በፋሺስት ጦር አንገታቸው የተቆረጠውና አስክሬናቸው ወደ ገደል የተወረወረው ለአገራቸው ክብር እንጂ ለራሳቸው ጥቅምና ዝና አልነበረም።
የሦስት ወራት ነፍሰ ጡር ሆነው ሳሉ ባለቤታቸውና የባለቤታቸው ወንድም የተገደሉባቸው፣ ልጃቸው በእስራት የተጋዘባቸው፣ ለመውለድ ተቃርበው እንኳ ከጠላት ጦር ጋር እየተፋለሙ ደማቅ ድሎችን ያስመዘገቡት፣ በውጊያ መሐል ሳሉ ወንድ ልጅ የተገላገሉት እንዲሁም የአራስነት ጊዜያቸውን ያሳልፉባት በነበረችው ደሳሳ ጎጆ ላይ የቦምብ ናዳ ይወርድባቸው የነበሩት ታላቋ አርበኛ ክብርት ወይዘሮ ከበደች ሥዩም በሸዋ፣ በወለጋና በጎጃም ተዘዋውረው ጠላትን የተፋለሙበትን የጀግንነታቸውን ተዓምር ለማመን የተቸገረ ሰው አይፈረድበትም።
የራስ አበበ አረጋይ፣ የራስ መስፍን ስለሺ፣ የራስ ደስታ ዳምጠው፣ የራስ ውብነህ ተሰማ (አሞራው ውብነህ)፣ የሌተናል ጀኔራል ጃገማ ኬሎ፣ የደጃዝማች ባልቻ ሳፎ፣ የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ የደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ የደጃዝማች በቀለ ወያ፣ የደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት፣ የደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ የደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል፣ የዘርዓይ ደረስ፣ የሸዋረገድ ገድሌ፣ የዶክተር መላኩ በያን፣ የወይዘሮ ስንዱ ገብሩ፣ የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ እና የሌሎች እልፍ ኢትዮጵያውያን አርበኞችን የጀግንነት ታሪክ ጽፎ/ተናገሮ ለመጨረስና ሰምቶ/አንብቦ ለማመን ይከብዳል።
ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎችና መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን አርበኞች በፀረ-ፋሺስት ተጋድሎው ወቅት ስለከፈሏቸው መስዋዕትነቶችና ስለጀግንነታቸው በዝርዝር ጽፈዋል። አንጋፋው የእንግሊዝ ጋዜጣ፣ The Guardian እ.አ.አ በጥቅምት 3፣1935 ዕትሙ ‹‹… የፋሺስቱ ሙሶሊኒ ወታደሮች በኢትዮጵያ ላይ ዘምተው ወረራ ፈፅመዋል፤ ኢጣሊያ ሀፍረት የተከናነበችበትን የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀል ቆርጦ የተነሳው ሙሶሊኒ፣ ለቅኝ ገዢዎች ያልተንበረከከችውን የጥቁሮች አገር የመያዝ የረጅም ጊዜ ምኞትና ፍላጎት ነበረው … ምንም እንኳን ፋሺስት ኢጣሊያ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ከባድ ጥፋት ቢያደርስም፣ ኢትዮጵያውያኑ በጀግንነትና በጥንካሬ እየተዋጉ ይገኛሉ›› በማለት ጽፏል።
አንጋፋው የታሪክ ጸሐፊ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹… የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር የተከተለው መንገድ በበርካታ ጥፋቶችና ወንጀሎች የታጀበ ነበር። የጭካኔውን ዓይነት መዘርዘር ቢከብድም፣ የመርዝ ጋዝ መጠቀሙ፣ የቀይ መስቀል ሆስፒታሎችንና አምቡላንሶችን በቦምብ ማጋየቱ፣ የተማረኩ እስረኞችን ያለፍርድ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደሉ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ እንዲሁም በግራዚያኒና በሌሎች ሹማምንት ትዕዛዝ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን መረሸኑ የአረመኔነቱን ወሰን ያሳዩ ተግባራት ነበሩ።
… በተለይ የየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ የበርካታ ንፁሃን ኢትዮጵያውያንን በሕይወት የመኖር መብት የቀማ፣ የአዲስ አበባን ጎዳናዎችና መንደሮች በደም አበላና በሬሳ ክምር ያጥለቀለቀ ፍፁም አረመኔያዊ ድርጊት ነበር፤ አውሮፓና አሜሪካ ተምረው ወደ አገራቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ለአምስት ዓመታት በዘለቀው የወረራና የግፍ ዘመን የፋሺስት የጭካኔ ግብር ሰለባዎች ሆነዋል …›› በማለት ጽፈዋል።
የድሉ ምስጢሮች
እጅግ ዘመናዊና ጅምላ ጨራሽ የሆኑ የጦር መሳሪዎችን የታጠቀውና ቁጥሩ የበዛው የፋሺስት ጦር ኋላቀርና በቁጥርም ጥቂት የሆኑ መሳሪያዎችን በያዙት ኢትዮጵያውያን አርበኞች መሸነፉን በቀላሉ አለመቀበል የሚያስወቅስ አይደለም። ይልቁንስ ‹‹ግን የኢትዮጵያውያን የድል ምስጢር ምንድን ነው?›› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
የዘመናዊ ኢትዮጵያን ታሪክ በሳልና ሚዛናዊ በሆነ ትንታኔ ያቀረቡት የታሪክ ምሁሩ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ፡ ከ1848-1966›› በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹ … የኢጣሊያ አገዛዝ ከተመሰረተ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ አገር አቀፍ የሆነ ተቃውሞ ነበር የገጠመው፤ ምንም እንኳ ጣሊያኖች በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ተቃውሞውን ለማዳከም ቢሞክሩም ሰጥ ለጥ ብሎ የተገዛላቸው አንድም ክልል ወይም ብሔረሰብ አልነበረም። የኢትዮጵያውያን አርበኞች ትግል የኢጣሊያ አገዛዝ በአብዛኛው በከተሞች ብቻ እንዲወሰን አስገድዶታል።
አርበኞቹ ምግብ ሲቸግራቸው የዱር አራዊትን እያደኑና ፍራፍሬ እየለቀሙ ይመገቡ ነበር፤ መድኃኒትም ቢሆን ባህላዊ ወጌሾች ነበሩ የሚያክሟቸው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች የነፃነት ትግል በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንዱ አኩሪ ታሪክ ነው። ኢትዮጵያውያን ሲሉ ለመሞት ዝግጁ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው፤ የአርበኞቹና የመላው ኢትዮጵያውያን ትግል የኢጣሊያን አገዛዝ በመገዝገዝና በማመንመን ለመጨረሻ ውድቀቱ አብቅቶታል። የፋሺስት ኢጣሊያ ሰራዊት በአርበኞች ጥቃት ተደናብሮና ተጎሳቁሎ በመጨረሻ እንግሊዞች አገሪቱን ነፃ ለማውጣት ለከፈቱት ዘመቻ ክፉኛ ተጋልጦ ሌላ ውርደት ተከናነበ።
ፋሺስት ኢጣሊያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመው ግፍ ከአዕምሮ የሚጠፋ ድርጊት አይደለም። ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ነፃነት ለማስጠበቅ የከፈሉት መስዋዕትነትም አኩሪነቱ የድሉ ባለቤት በሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር ይኖራል … ›› በማለት አስረድተዋል።
ፕሮፌሰር ፓንክረስት በበኩላቸው ‹‹ … ኢትዮጵያውን ከደረሰባቸው ጭፍጨፋ የተረዱት አንድ ነገር ነበር፤ ከዚያ በኋላ የእነርሱ የሚሉት ነገር እንዳልቀራቸውና ብቸኛው ዕድላቸው ለነፃነታቸው መታገል። ብዙ ዓይነት አሟሟት መኖሩን የተገነዘቡትና ለነፃነትና ለአገር ክብር መሞት ኩራት መሆኑን ያልተጠራጠሩት ኢትዮጵያውያን፣ የፋሺስት ኢጣሊያን ጦር በየቦታው በመውጋት መቀመጫ አሳጡት። ከአዲስ አበባ ጭፍጨፋ ያመለጡት የከተማዋ ነዋሪዎች በዱር በገደሉ የነበሩትን አርበኞች ተቀላቀሉ፤ የዝነኛው የሸዋ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ ተከታዮች መብዛትም የዚሁ ማሳያ ነበር።
በመጨረሻም ከአምስት እልህ አስጨራሽ የትግል ዘመናት በኋላ ነፃነታቸውን በቆራጥነታቸው ያስመለሱት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሉዓላዊነትና ክብር ውድ ሕይወታቸውን ሰውተዋል። በነፃነት ትግሉ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ያልተሳተፈ ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል›› ብለዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ግዙፉን የፋሺስት ጦር ድል ያደረጉት ከራሳቸው ጥቅም እንዲሁም ከውስጥ ልዩነቶቻቸው በላይ አገራቸውን በማስቀደማቸው፣ በመተባበራቸውና በመደማመጣቸው ነው!
ይህ ትውልድ ምን ይማር?
የዘንድሮውን የአርበኞች ድል መታሰቢያ ሲከበር ኢትዮጵያ በበርካታ አስጨናቂ ችግሮች ተወጥራ የምትገኝበት ጊዜ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። አገሪቱን ከውስጥም ከውጭም እረፍት የነሷት የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎችና የዘመናት የውጭ ጠላቶቿ በጋራ ሆነው እረፍት ነስተዋታል። በእርግጥ ኢትዮጵያ ቀደም ሲልም ጀምሮ በጎ የማይመኙላት የውጭ ጠላቶች አሏት። እነዚህ ጠላቶቿ ጫናቸውን ሊያሳርፉባትና በለስ ከቀናቸውም ታሪክ ሊያደርጓት ኃይላቸውን ሁሉ አሟጠው የሚጠቀሙት የውስጥ ባንዳዎችን በመጠቀም ነው። የአሁኑ ችግሯ የከፋ የሆነውም ባንዳዎቹ አድማሳቸውን አስፍተው ለውጮቹ ጠላቶች ሰርግና ምላሽ ስለሆነላቸው ነው።
ስለሆነም ይህ ትውልድ የውጭ ጠላት መኖር ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር እንዳልሆነና ከውጭ ጠላቶች ይልቅ የውስጥ ጠላቶች የበለጡ አደገኞች መሆናቸውን ሊገነዘብ ይገባል። ይህን ሀቅ ሳይገነዘብ ‹‹ኢትዮጵያን እወዳለሁ … ኢትዮጵያን አተርፋለሁ›› ማለት ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው ዓይነት ቀልድ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስለጀግኖች አርበኞች የአገር ፍቅርና መተባበር ትርጉም በሚገባ መረዳት ይጠበቅበታል።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ነፃነት ሰማዕታት!!!
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2013