ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን በ1945 እና 46 የታተሙ ጋዜጦችን ቃኝተናል። በእነዚህ አመታት ጋዜጣው በየሳምንቱ ይወጣ የነበረ ሲሆን፣በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ስር ዘገባዎች ይቀርቡም ነበር። ባለፈው ሳምንት የከተማ ወሬ በሚለው ስር ይወጡ የነበሩ ዜናዎች ይዘን መቅረባችን የሚታወስ ሲሆን፣በዛሬው እትማችን ደግሞ እንጨዋወት በሚል ከአንባቢዎች ተልከው በጋዜጣው የወጡ ጽሁፎችን ይዘን ቀርበናል።
አንዳፍታ እንጫወት
ከዕለታት ባንደኛው ቀን አንዲት ሴት ከጓደኛዋ ዘንድ ድስት ተዋሰችና በማግስቱ ሁለት አድርጋ መለሰችላት። ጓደኛዋም ምነው እህቴ የሰጠሁሽ አንድ ነበር ፤ለምን ሁለት አድርገሽ ትሰጪኛለሽ ?ብትላት ድስትሽ ወልዶ ነዋ! አለቻት።
እሷም ነገሩን ባለመመራመር በይ እግዜር ይስጥሽ ብላ ተቀበለቻት። በሌላኛው ቀን ደግሞ ድስት አውሳ የነበረችዋ ወደ ጓደኛዋ ሄደችና ድስት ተዋሰቻት ።ድስቱንም የዘነጋች አስመስላ ስላስቀረችው ፤ ባለቤትየዋም ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው ተረት ፤ለራሷ ሁለት እንደ ወሰደች ዘንግታ ያዋሰችዋን ድስት ለመቀበል ሄዳ ከተበዳሪዋ ጋር በተገናኙ ጊዜ እባክሽ ድስቱን መልሽልኝ ብትላት አዬ ጉድ ! ምነው ድስትሽማ ሞቶ አለቻት ።ምነው እኅቴ ድስት ይሞታል ብትላት ባታስታውሺው ነው እንጂ አንቺስ እንዴት ድስት ይወልዳል አለቻትና በነገሩ ሁለቱም እየተደነቁ እየተሳሳቁ ወደ ቤታቸው ሄዱ።
ከጄኔራል ዊንጌት ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት አንዱ ጥላሁን አዱኛ
(ሐምሌ 18 ቀን 1945 ከወጣው አዲስ ዘመን )
አንድ ጠንቋይና አንድ ሰው
ሰውየው ወደ ጠንቋይ ሒዶ መጪውን ኑሮዬን እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ አለው።
(ጠንቋይ) መጪውን ሁኔታህን ለማወቅ ስትፈልግ 0.15 ሳንቲም ይፈለግብሃል ሲል መለሰለት።
(ሰውየው) ይኽው ገንዘቡ ስለመጪው ሁኔታ የምትነግረኝን ለማመን አስቀድመህ ስላለፈው ኑሮዬ እንድትነግረኝ እፈልጋለሁ።
(ጠንቋይ) በጣም ቀላል ነው በቤት ውስጥ ከሚስትህ
ጋር ደስ ሳትሰኝ ትኖራለህ ።
ሰውየው ሚስት አላገባሁም።
(ጠንቋይ) የወዳጅ ጠላት አለህ ።
(ሰውየው) ወዳጆቼ (ባልንጀሮቼ)
እምነታቸውን አላጓደሉብኝም።
(ጠንቋይ) ምናልባት ተሳስቼ ይሆናል ኧኸ) በጣም
ሩቅ ሀገር ሒደህ ነበር።
(ሰውየው) ከከተማ ውጪ አልወጣሁም ።
(ጠንቋይ)እባክህ ጃል! እስኪ እጅህን ዘርጋ፤ አሁን
አንብቤ እደርስበት የለም።
(ሰውየው) እጁን ዘርግቶ ያሳየዋል።
(ጠንቋይ) ገንዘብ በብዙ ትበትናለህ አባካኝ ነህ።
(ሰውየው) እርግጥ አሁን አወቅህ፤ ለአንተ አምጥቼ የሰጠሁክን አስራ አምስት ሣንቲም እንደበተንኩት ይታወቀኛል። ብሎት በዚህ ተለያዩ፤ ይገርማል።
በ.ኪ (መስከረም 23 ቀን 1946 ከወጣው
አዲስ ዘመን )
ጨውና ቅቤ
አሞሌ ጨውና ለስታ ቅቤ ብዙ ጊዜ በጓደኝነት ሲኖሩ፤አንድ ቀን ከነበሩበት ወደ ሌላው ሀገር ለመዘዋወር አሰቡና፤ ከዚያው ከነበሩበት አገር ተነስተው ጫካ ጫካውን ሲሄዱ ሰንብተው በመጨረሻው በአንድ ወገኑ ሰፊ ባህር፤ ደግሞ በሌላ ወገኑ ለጥ ያለ በአሸዋ የተሞላ ሠፊ ምድረ በዳ ወደ ሆነ ሥፍራ ደረሱ።
አቶ አሞሌ ጨው “ቀዝቃዛ ነገር ስረግጥ እታመማለሁ ፤ሰውነቴ ይመነምናል፤ በጭራሽ ቀዝቃዛ ሥፍራ ፤ርጥበት ያለበት ማንኛውም ነገር አይወድልኝም ። ስለዚህ በዚህ ምድረ በዳ እየጎበኘን ብንሄድ ይሻላል” አለና ቅቤን አስቀድሞ መንገድ አጠረበት።
ደግሞ አቶ ለስታ ቅቤ ተንኮሉን አወቀበትና “በበረሃ ስሄድ ውሃ ጥም አልችልም ገላዬ በሙሉ ለስላሳ ነው የአሸዋው ረሞጫ ሲነካኝ ፤ሰውነቴ ሁሉ ይቀልጣል።እንዲያውም ቀዝቃዛ እንጂ የሞቃት ሥፍራ ሙቀት የሚሉት ነገር አጥፊዬ ነው ።ስለዚህ በውሀው ዋኝተን እንድንሻገር እለምንሀለሁ። እንዲያውስ በገዛ እናት ሀገርህ አልሄድበትም፤ የምትለው የተፈጠርከው ከዚህ አይደለም ወይ ?” አለና ብድር መለሰለት።
አቶ አሞሌ ጨው መልሶ ” ዋ! ጓዴ ባልንጀራዬ፤ እንኳን እኔ አስተዋይና ተመራማሪው የሰው ልጅ ቢሆን፤ከወጣበት ተመልሶ ከገባ በቃ ተከተተ ፤አይመለስም። ይልቅስ ስንተዋወቅ አንተላለቅ፤ በየራሳችን ያመጣነው ሀሳብ የተንኮል ነው። እኔ ከአንተ ጋር በውሀ ብሄድ እሞትብሀለሁ፤ጓደኝነቴ ባልንጀርነቴ ይቀርብሃል።
ደግሞ አንተ ከኔ ጋር በአሸዋው ምድረ በዳ ላይ ብትሔድ ቀልጠኽ እንዲሁ ባልጀርነት ይቀርብኛል። ስለዚህ አንድ ምክር ልስጥህ። ይኸውም አንተ የባህሩን ዳር ይዘህ ከኔ ሳትርቅ በውሀው፤ ደግሞ እኔ የየብሱን ወሰን እጅግ ካንተ ሳልለይ በደረቁ ጎን ለጎን ሆነን ሳንራራቅ እንሒድ። አሰብንበት እግዚአብሔር ያደርሰናል፤ መንገዳችንንም ያቃናልናል አለው።
ሁለቱ በነገሩ ስለአሰቡበት በዚኅ አኳኋን ተጉዘው ወደ አሰቡበት ሥፍራ ለመድረስ ቻሉ። ለራስህ የማትወደውን ለባልንጀራህ አታድርግለት ፤ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደደው።
ህላዌ ገብረ እግዚአብሔር
(መስከረም 2 ቀን 19 46 ዓ.ም ከወጣው
አዲስ ዘመን)
ግበ ከረየ ወደሀ ወይወድቅ ውስተ ግብ ዘገብረ። ሰው አንዳንድ ጊዜ ቁምነገሩን እንደያዘ ጨዋታ ወይም ደስታ ያስፈልገዋል። ይሁን እንጂ መቀየምን አይወድምና፤ሌላውን ማስቀየም አያሻውም። ጨዋታ የቁም ነገር መደገፊያ ነው እንጂ ያሰቡትን ሁሉ ለመናገር ስፍራ አያገኝም። ለጨዋታ ብሎ ቁም ነገርን መዝለል ወደ መገመት ያደርሳል። ታዛቢ አለበት ብላክ ሊስት፣አፍ ቀልድ ከለመደ ቁም ነገር ይረሳል።
በዘመነ መሳፍንት ለቤተ መሳፍንቱ ደገጋፊ የሆኑ ሁለት ባለሟሎች ነበሩ። አንደኛው የነጋዴ ወገን የዘመኑን ምክር አዋቂ የነበረ፤፪ኛውም የአገር አቅኚ ወገን የጦር ሰው የሆነ ይኸውም እግሩ ጥቂት ያነክስ ነበረ።
በዚያው በመሳፍንቶቻቸው አዳራሽ በበዓል ቀን ከመዛናት የተነሳ የነጋዴው ወገን በአዛውንቱ መካከል በአማርኛ ለመንካት የጦሩ መኮንን ስሙን ጠርቶ ከዚህ እስከ ምፅዋ ምን ያህል ቀን ይወስዳል ሲል ጠየቀው። የነጋዴው ወገን ሲመልስ በመልካም እግር ነውን? ብሎ መልስ ሰጠ። ባበራችው መብራት ራቷን አዩባት የተባለው ምሳሌ ትርጉም አገኘ። ከዚህ በኋላ ሰው መንካቱን ተወው ይባላል። መንካት ወደ መነካት ያደርሳልና ይህን አለመዘንጋት ነው።
ለማ ተክሌ ጅማ
(ግንቦት 21 ቀን 1945 ከወጣው አዲስ ዘመን)
በ፩ ወረዳ ግዛት ሁለት ሰዎች ነበሩ።(ይባላል) እነዚህ ሰዎች ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ጉዳያቸው ለመሔድ ሁለቱም ከየቤታቸው ተነስተው ቤት ያፈራውን ፩ኛውም ከእራት ተርፎ ባደረ ጐመን፤፪ኛውም በውቅጥ በርበሬ ፍትፍት ቁርስ አድርገው የአፍ ንፅህና ልምድ ስላልነበራቸው ፤መንገዳቸውን ቀጥለው ወደ የጉዳያቸው ሲሄዱ በመንገድ ተገናኝተው ሰላምታ ከተሰጣጡ በኋላ በጐመን ቁርስ ያደረገው ሰውዬ በውቅጥ በርበሬ የበላውን ፤ወንድም የአገርህ በርበሬ ስንት ነው ቢለው፤ ያም ያየውን አይቷልና በጐመን መሣነው አለው ይባላል።
ከሐረር ጠ.ግ.ፖ.ጽ.ቤ
አ.ገ.ስ
(ነሐሴ 29 ቀን 19 46 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013