ዘመናዊነት ውስብስብ ፍልስፍናዊ ፅንሰ-ሐሳብ ሲሆን፤ ከጥንት አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሉ ምሁራንን ያነጋገረ ርእሰ-ጉዳይ ነው።ሕይወት እና የጋራ ህልውና፣ የታሪክ ንባብና የወደፊት እቅድ በዘመናዊነት እሳቤ ላይ ይመረኮዛሉ። እንዲያውም አንድ ማኅበረሰብ የሕይወት አረዳዱ ለዘመኑ ባለው እሳቤ ላይ ይመሰረታል ብለው የሚሞግቱም አሉ።
የዘመናዊነት እሳቤና የዘመን መንፈስ ሐተታ ያላቸው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ፤ ከሕይወት ትርጉምና ንጽረተ- ዓለም ጋር ያላቸውን ቁርኝት መረዳት የዚያን ማኅበረሰብ የኅሊና ካርታ ለማንበብ፣ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ለሚደረግ የፖለቲካ ኢኮኖሚና የባህል ሽግግር፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ትልቁን ሚና ይጫወታል። ለዛሬው የአንድን ማህበረሰብ የመዘመን አረዳድ፤ ቁሳዊ ግንባታውና አስተሳሰባዊ መዋቅሩን ከሚያሳዩ ጉዳዮች “የአልባሳት ፋሽንና ዘመናዊነትን” ዓለም አቀፋዊ እሳቤውንና ኢትዮጵያዊ መልኩን እንመልከት።
ለእይታ የሚጨነቅ ማህበረሰብ ራስን በዘመናዊነት ለመግለጽ በአልባሳት፣ በጌጣጌጦችና የሰውነት ጥበቦች ተውቦ መታየትን ይሻል። ራስን ማሳያ ከሆኑት ነገሮች ውስጥ ደግሞ አልባሳት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።አልባሳት እንደ ብርድ፣ ሙቀት እና ሌሎች አካባቢያዊ ሁኔታዎችን መሠረት አድርገው ይለበሳሉ። የሰውን አካል ከመጠበቅ በተጨማሪም በተለያዩ ፋሽኖች ተሰርተው ያስጌጡታል።ይህም የፋሽን ዋና ሚና ከሆኑት መካከል የሰውን አካል የማስጌጥ ዝንባሌ ያሳያል። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች ፋሽን በዘመናዊ አለባበስ ላይ የድምፅ ተግባር ያለው ነው ሲሉ ይደመጣሉ።
በተለይ ባደጉት አገራት ፋሽንና ዘመናዊነት የግለሰባዊነት መገለጫ ሲሆን፤ ሥራን፣ ደረጃንና ስብእናን ለማሳየት አለባበስን እንደ ሐሳብ ልውውጥ አይነት ይጠቀሙበታል።በዚህም የማንነት ግንባታ እንደ ማህበራዊ ሂደቶች ከፋሽን ስርዓት ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ግንኙነቶች መሆናቸው ይነገራል።ይህም የፋሽን እና የዘመናዊነት ፅንሰ ሀሳቦችን ግንኙነት ያሳያል።
ፋሽን፤ አልባሳት እንዴት እና መቼ መለበስ እንዳለባቸው ስለ ዘመናዊነት ሁኔታ መረጃ የሚሰጥ ነው የሚሉት የፋሽን ዲዛይን መመህሩ አቶ ሚኪያስ ታደለ ናቸው። ፋሽንን የማይቀበሉትም እንኳ ከእዚህ እሳቤ ጋር የተገናኙ ስለመሆናቸውም ነው የሚያብራሩት።ሰዎች ወቅታዊ አዝማሚያዎችን እንደሚከተሉና ይህም በየጊዜው እንደሚለዋወጥ ይናገራሉ።በፋሽን ጽንሰ ሀሳብና ተግባሩ ላይ በመመርኮዝ ፋሽን በተለይ በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በዘመናዊ ማንነት ግንባታ ውስጥ የማዕዘን ድንጋይ እንደነበረ ያሳያሉ ፡፡
ፋሽን ቁልፍ ባህሪው ፈጣን እና ቀጣይነት ያለው መሆኑን የሚያብራሩት ባለሙያው፤ የዘመናዊነት እሳቤም እንዲሁ ከዚህ ጋር እንደሚታይ ይጠቅሳሉ።ከዘመናዊው ማህበረሰብ ዋነኛ ገጽታዎች መካከል ዛሬ ላይ ፋሽን አንዱ እንደሆነና በየጊዜው ጥራት ባላቸው ዲዛይኖች ዘመኑን እንዲዋጁ ተደርገው እንደሚዘጋጁ ይገልጻሉ።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ይህ በጥቂቱም ቢሆን በአሁኑ ወቅትም እየተተገበረ ይገኛል።ፋሽን ከዘመናዊነትና ከዓለም የኢኮኖሚ እድገት ጋር እያደገ መጥቷል።እያንዳንዱ ፋሽን ወቅትን እያስተዋወቀ ይገኛል።ሰዎች በማህበራዊ ህይወታቸው ቀለል ያለውን የመዘመኛ መንገድ ሲከተሉ ፋሽንንም እንደ አንዱ ይጠቀማሉ።ፋሽንን ከዘመናዊነት እሳቤ ጋር ማስኬድ ቄንጠኝነት አይደለም።ፋሽን እንዲያውም ኑሮን ለማቅለል ሰፊ እድል ይሰጣል።ከብዙኃን ጋርም ያስተሳስራል።
ባለሙያው፤ የግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) ትልቁ ውጤት በፋሽን ላይ ነው ይላሉ። ሁሌም አዲስ ፋሽን ሲመጣ ከመቅጽበት በሁሉም ሥፍራ ተደራሽ እንደሚሆን፤ አዲስ ነገር ሲመጣ ደግሞ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ይዞ መምጣቱ ስለማይቀር መርጦ መጠቀም የማህበረሰቡ ፈንታ እንደሆነ ይናገራሉ።ታዲያ በጎውንና ኑሮን ማቅለያ የዘመናዊነት ሥሪት እንደ ፋሽን ስለሚቆጠር ሰዎች ከመጠቀማቸው አይቦዝኑም።ፋሽን አልባሳት ደግሞ ከምርጫዎቹ ተርታ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው በማለት፤ ተከታዩንም ምክር ይሰጣሉ፡፡
“እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ፋሽን ከዘመናዊነት አስተሳሰብ ጋር ሲቆራኝ ምክንያታዊነት መያዝ ይኖርበታል።ፋሽንን የሚያዘወትሩ ሰዎችም የልብሱን ስሪት አሊያም የአለባበስ “ስታይሉን” ለምን ብለው መጠየቅ ይኖርባቸዋል።ለምሳሌ ሱሪ ዝቅ አድርጎ መልበስን መኮረጅ ሳይሆን ለምን ሰዎች ዝቅ አድርገው ለበሱ የሚለውን መጠየቅ ይገባል።ትልትል ፋሽን አልበሳት በዚህ መልኩ ስለምን ተዘጋጁ የሚል ጥያቄንም ማንሳት ተገቢ ይሆናል።
አሊያ ሁሉን አልባሳት እንደመጣ በዘመናዊነት እሳቤ መቀበል ባህልን ሊመርዝ ይችላል።ፋሽን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከአዎንታዊ የበለጠ እጅግ አሉታዊ የሚሆንበት አጋጣሚም ሊፈጠር ይችላል። ምክንያቱም አልባሳት እንደ ቋንቋ መረጃ ይሰጣሉ። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፋሽን እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ ውስብስብ ደረጃ ላይ ስለ ደረስ ማህበራዊ ቀውስ ላይ ሊጥል ይችላል፡፡” በማለት ፋሽን ዘመናዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የህብረተሰቡን ሥነ ምግባራዊ መርሆዎች የሚስማማ መሆን እንዳለበት ያመላክታሉ።በማይታወቅ ማንነት ከመጠራትና ትችት ከመሰንዘር ምርጡን ፋሽን መርጦ መልበስ ብልህነት እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ምንም እንኳን ዛሬ ፋሽን ለሁሉም ርካሽ በሆነ መንገድ በብዛት የሚመረቱበት ወቅት ላይ ብንሆንም፤ ከዚህ ቀደም ግን ትልቅ አቅም ይጠይቅ ነበር።በባህር ማዶ በተለይም በአውሮፓ ፋሽን ከዘመናዊነት የማይነጠል ክስተት ነው። እንዲያውም የ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢንዱስትሪ አብዮት እድገት ተደርጎም ይነገራል።በተሻሻለ ቴክኖሎጂ፣ በሥነ ውበት እንዲሁም በሀብትና በኢንዱስትሪ በበለፀገ ማህበረሰብ ውስጥ ፋሽን ማበብ ችሏል።የፋሽን አልባሳትን ከወጣቶች የመዘመን ሀሳብ ጋር ለማጣጣምም ተሞክሯል፡፡
ዘመናዊነት ሲዘምን ወይም ሲጋርድ? በሌላ ቀውስ ውስጥ ላለማለፍ መጠንቀቅ ተገቢ እንደሆነ የሚያብራሩት ባለሙያው፤ ፋሽንን በዘመናዊነት አይን መመልከት የራስን ባህልና ማንነት ባልተጣረሰ መልኩ ለመከተል እንደሚረዳ ይመክራሉ።በጨርቃ ጨርቅና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዛሬ ላይ ሁሉም ሰው ፋሽን የመከተል መብት ቢኖረውም፤ ፋሽን አሁንም የማኅበራዊ ልዩነት ሚናን እንደሚጫወት ጠቅሰው፤ ነገር ግን ወሳኙ ሁኔታ ነገሮችን በአፅንዖት ማየት ነው ይላሉ፡፡
ፋሽንን መከተል ከተሟላ ቅርፅና ትርጉም ካለው ሁኔታ ጋር በማዛመድ መሆኑን በመግለጽ፤ እንደ ንግግርና ሌሎች ማህበራዊ ሁኔታን የሚያንፀባርቁ የግል ባህሪዎችም በአልባሳት ላይም ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ፤ እንዲሁም የማህበረሰቡ ሕሊና ዘመናዊነትን ሲበይን ፋሽንን ከሕይወት ምሕዋር ጋር ቀይጦ፣ ከማኅበራዊ ገቢርና ከተፈጥሮ ዑደት ፍሰት ጋር አዳቅሎ ማየት እንደሚያስፈለገው ይመክራሉ፡፡
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 25/2013