በኢትየጵያ ታሪክ ውስጥ ታላቅ አሻራ ካኖሩት መካከል አንዷ ናቸው፡፡ በውሳኔ እና በጠንካራ አመራር ሰጪነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በማህበረሰቡ ልማድ የኮሰመውን ሴትነትን ያነሱ በዚህም የአይችሉም መንፈስን የሰበሩ ጀግና ንግስት ተብለዋል፤ ግርማዊት ንግስተ ነገስት ዘውዲቱ፡፡
ንግስት ዘውዲቱ ሚያዚያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም ከሸዋ ንጉስ ምንሊክ እና ከወረኢሉ ተወላጅ ከወይዘሮ አብቺው ሸዋ በእነዋሪ ከተማ ተወለዱ፡፡ ለዳግማዊ ምንሊክ ሶስተኛ ልጅ ናቸው፡፡
በጥቅምት 13 ቀን 1875 ዓ.ም የአጼ ዮሐንስ ልጅ ራስ አርአያ ስላሴን ወረኢሉ ላይ በተክሊል እና በቁርባን አገቡ፡፡ በዚያ ጊዜ ራስ አርያ ስላሴ የ12 ዓመት ዕድሜ ሲሆኑ የወይዘሮ ዘውዲቱም ዕድሜ ስድስት ዓመት ከስድስት ወር ነበር፡፡ ጋብቻው 5 ዓመት ከ7 ወር ከቆየ በኋላ ራስ አርአያ ስላሴ ሰኔ 19 ቀን 1880 ዓ.ም አረፉ፡፡
ከዚህ በኋላ ንግስት ዘውዲቱ ከደጅዝማች ጓንጉል ዘገየ ሴት ልጅ ወለዱ፤ እርሷም የሁለት ዓመት ዕድሜ ሳለች በህጻንነቷ ተቀጠፈች፡፡ ከዚህ ቀደም ደግሞ ለደጃች ውቤ አጥናፍ ሰገድ ተድረው አራት ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ተፋትተው በ1893 ደጃች ጉግሳ ወሌን አገቡ፡፡
ዳግማዊ በ1901 ዓ.ም በታመሙ ጊዜ አባታቸውን እያስታመሙ ተቀመጡ፡፡ ዳግማዊ ሚኒሊክ በታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ሲሞቱ በልጅ ኢያሱ ትዕዛዝ ፋሌ በርስታቸው ላይ ተቀማጭ ሆኑ፡፡ በዚያም ሳሉ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም በመኳንንት እና በህዝብ ቃል ተመርጠው በአባታቸው በዳግማዊ ምኒልክ ዙፋን ተቀመጡ፡፡
በዚያኑ ጊዜ መኳንንቱና ሚኒስትሮች መክረው ባላቸው ራስ ጉግሳ ከባለቤታቸው ጋር አዲስ አበባ እንዳይኖሩ እና ወደ ግዛት አገራቸው እንዲሄዱ ስለተወሰነ ባልና ሚስቱ ተለያይተው እንዲኖሩ ሆነ፡፡ በመጋቢት ወር 1922 ዓ.ም ባላቸው ራስ ጉግሳ ከመንግስት ጋር የነበራቸው አለመግባባት ወደ ግጭት እንዳያመራ ለማስታረቅ ሞክረው ሙከራቸው ሳይሳካ ቀርቶ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም እንቺም ላይ በተደረገው ውጊያ ራስ ጉግሳ ሞቱ፡፡ ንግስት ዘውዲቱም መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም አርፈው ቀብራቸው አዲስ አበባ በታዕካ ነገስት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡
አብርሃም ተወልደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 24/2013