
የስፖርት ማህበራት አበረታች ቅመሞችን(ዶፒንግን) በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በቂ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ከኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከስፖርት ማህበራት አመራሮችና ከተለያዩ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት የተወጣጡ አካላትን ያሳተፈ ስልጠና ሰሞኑን በአዳማ ከተማ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በስልጠናው ላይ ለተሳታፊዎች ‹‹ጽሕፈት ቤቱ ከየት ወዴት?›› የሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የጽሕፈት ቤቱ አጀማመርና አሁን የደረሰበት ሁኔታ፤ አደረጃጀትና አሰራር እንዲሁም ተቋማዊ ነጻነትን በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል ።
አቶ መኮንን ኢትዮጵያ በዶፒንግ ዙሪያ ያላትን ተሞክሮ ለሌሎች አገራት በማጋራት ረገድ ያከናወነቻቸውን ተግባራት በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የባለ ድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን አለበት? የሚሉ ጉዳዮችንም አንስተዋል ፡፡ በተጨማሪም የስፖርት አበረታች ቅመሞች ወይም ዶፒንግ በአገራችን ስፖርት መሠረታዊ ችግር እንደሆነ በመጥቀስ፣ የኢፌዲሪ መንግስት ይህን በአግባቡ በመገንዘብ ችግሩን ከመሰረቱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡ ለዚህም በኢትዮጵያ እስካሁን ያለው አፈፃፀምም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ይህ እንቅስቃሴ በተጠናከረ መንገድ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።
እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፤ የስፖርት ማህበራት ባለሙያዎች ከምንም በላይ የዶፒንግ ጉዳይ በዋናነት የሚመለከታቸው በመሆኑ በመጀመሪያ ራሳቸውን ከችግሩ ነፃ በማድረግ የበኩላቸውን ገንቢ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ፡፡ አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን በመዘርጋት የፀረ ዶፒንግ ጉዳይን የእቅዳቸው አካል በማድረግና አስፈላጊውን ሀብት በመመደብ ትኩረት ሰጥተው ዶፒንግን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ስራዎችን መስራት ይገባቸዋል ፡፡
ከዚያ በተጨማሪ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በዚህ ዓመት የፀረ አበረታች ቅመሞችን የተመለከተ ጉዳይ በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል ። ይህም ታዳጊዎች ስለጉዳዩ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ግንዛቤው እንዲኖራቸው ይረዳል ብለዋል ፡፡
ጎረቤታሞቹ የምስራቅ አፍሪካ የረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ፈርጦች ኬንያና ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ያላቸውን መልካም ስም ያህል በስፖርቱ ትልቅ አደጋ እያንዣበበባቸው እንደመጣ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱ አበረታች መድኃኒት ወይም ንጥረነገሮች ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ሩሲያንን የመሳሰሉ ታላላቅ አገራት ከታላላቅ ውድድሮች እስከ መታገድ እንደደረሱ ደርሰዋል፡፡
እነዚህ አገራት አትሌቶቻቸው በብዛት አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ ሆነው ከመገኘታቸው ጋር ተያይዞ በመንግሥት ጭምር ይደገፋሉ በሚል ከውድድሮች መታገዳቸው ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ እንዳደረገው ይታወቃል፡፡ የዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒቶች ኤጀንሲ እነ ሩሲያን በቀጣበት ወቅት ኢትዮጵያና ኬንያ አደጋው በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሰጋቸው በማሳወቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ምክረ ሃሳብ ሲሰጣቸው እንደነበር አይዘነጋም ፡፡
ሁለቱ አገራት በተለይም ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታ በመስራት አበረታች ውጤት ማስመዝገቧም በኤጀንሲው ጭምር ተመስክሮላታል፡፡ ያም ሆኖ ስጋቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ለማለት ግን አይቻልም። እኤአ 2019 ላይ የዓለም አትሌቲክስ ኢትዮጵያና ኬንያን በአበረታች መድኃኒት(ዶፒንግ) ምክንያት ስጋት ካለባቸው አገራት ቀዳሚውን ደረጃ እንደሚይዙ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
ሁለቱ አገራት ባለፈው ዓመትም በአበረታች መድኃኒት ስጋት ቁንጮውን ደረጃ መያዛቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተው ነበር ፡፡ ለዚህም በእነዚያ ዓመታት በርካታ የአፍሪካ አገራት አትሌቶች አበረታች መድኃኒት ተጠቃሚ ሆነው መገኘታቸው ማሳያ ተደርጓል ፡፡ ቤላሩስና ዩክሬን ሁለቱን የአፍሪካ አገራት ተከትሎ ስማቸው ከቁንጮዎቹ ተርታ ተፅፎ እንደነበረም ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል፣
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013