ጥንት ድሮ ያኔ ከፀሃይ እና ጨረቃ ልደት ማግስት፤ የአዳም አካላት ከምድር አፈር ከመበጀታቸው አስቀድሞ፤ የመላእክት ጥዑም ልሳን በውብ ዜማ ከመቃኘቱ በፊት፤ ልቡን በትእቢት አጀግኖ በተከታዮቹ ውዳሴ ከንቱ ራሱን ከፈጣሪ ጋር ያገዳደረው ሳጥናኤል ወደጥልቁ ከተወረወረ በሺህዎች የሚቆጠሩ አመታት ነጎዱ።
ሁለቱ የፍቅር እና የጥላቻ አባቶች፤ የፅድቅ እና ኩነኔ ሀያላን፤ በዚህ ሁሉ ዘመናት ውስጥ ከቶም ሊጠብ በማይችል ልዩነታቸው መቻቻል በሌለበት ሚዛን በብርሃን እና ጨለማ ዙፋን ላይ ተቀምጠው እልፍ ዘመናት ተቆጠሩ።
በዚህ የአፅናፍ ያክል ተብሎ እንኳን ሊገለፅ በማይችለው ግብራቸው ውስጥ ሳጥናኤል የእለተ አርብ እጅ ስራ በሆነው የአዳም ዘር የጠላት ፈተና አብዝቶበታል። የዚህ ፈተና ፍፃሜው ዛሬ ይሁን ነገ፤ ሳምንት ይሁን ለከርሞ ሳይታወቅ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህም የሰው ልጅን ከፅድቅ ጎዳና እያሰናከለ ከቀዝቃዛው መቃብር ጀርባ ከሞት በኋላ ባለው ዘለአለማዊ ህይወት ቃላት የማይገልፀውን መከራን መደገስ ነው።
በዚህ ምክንያት ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ፤ ከፀሃይ መውጫ እስከ መጥለቂያ ያሉ ህዝቦች የሀጥያት ትራፊክ አደጋ እንደተለመደው የብዙዎችን የዘለአለም ህይወት ዛሬም እየቀጠፈ ይገኛል።
ጌታዬ በዝሙትና በስካር፤ በግድያና በማንገላታት ራሳቸውን በፍጥነት የሚያሽከረክሩ የሰይጣን ተተኪዎች ለጉድ ተፈብርከዋል። እነዚህ ዳግማዊ ዲያብሎሳዊያን ለእውነት ቅድሚያ የማይሰጡ ናቸው። ባልተፈቀደላቸው የህይወት መስመር በሰፊው ጎዳና በፍጥነት ይጓዛሉ። በአካል እና ዋጋው ሊተመን በማይችለው ንብረትነቱ የፈጣሪ በሆነው ነፍስ ላይ ከፍተኛ ውድመትን በማድረስ ላይ ናቸው። ሰይጣን ይሰራው የነበረውን ሥራ ተቀብለውት ለእርሱ እፎይታን በመፍጠር ቀን ከሌት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በክፋት ሥራ ላይ ተጠምደዋል።
የሰው ልጅ ወደዚህች ምድር ሲመጣ በህይወት መንገድ ላይ ራሱን በሰላም እንዲያሽከረክር ነበር። ዛሬ ላይ ግን በተገላቢጦሹ ለበጎ ስራ ሁሉ ቅድሚያ በመስጠት ፈንታ ክፋትን ተሸክሞ ይዞራል። የጉዞው መዳረሻ እስከሆነው ማረፊያው በእርጋታ የቀኝ መንገዱን ይዞ በመልካም ጎዳና ላይ መገኘት ተስኖታል። የሰይጣንንም ግብሩን ተረክቦታል። የሚገርም ዘመን ነው።
ተፈራራን እኮ። ጥላችንንም፣ ምናችንንም…ያደናቀፈውንም፣ ያስነጠሰውንም የምንጠራጠርበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከክፋት መብዛት የተነሳ፣ እንደሚባለው፣ ለሰላምታ ከተጨባበጥን በኋላ ሁሉም ጣቶቻችን ላለመጉደላቸው ወደምንፈትሽበት ዘመን እየተጠጋን እኮ ነው። ደግነቱ ኮሮና የሚሉት ጉድ መጥቶ ከመጨባበጥ አትርፎናል እንጂ። መተማመን ጠፍቶ በቦታው ክፋት ሲተካ የሚሆነው ይኸው ነው። የሰይጣንን ግብር ተክቶ ለእርሱ እፎይታን መስጠት ነው።
ሰውን በክፉ ሥራ አሳስቶ ማስጓዝ የሰይጣን አንዱ ስልት ነው። በስፋታቸው እና ብልጭልጭነታቸው ወደር ያልተገኘላቸው፤ ከክፍያ ነፃ የሆኑ ጊዜያዊ ምቾት ያላቸው የሚመስሉትን የእኩይ መንገዶችን እለት ተእለት በማስተዋወቅ ይሰራል። በርካታ ነፍሶችን ዘለአለማዊ ህይወትን ከሚያገኙበት መንገድ በማንሳት ወደ ዘለአለም ስቃይ፤ መከራ ብሎም መዳረሻው የሞት ሞት በሆነበት እርኩስ ሀጥያታዊ መንገድ እያካለበ ይነዳቸዋል። አሁን ላይ ግን ይህ ግብር የሰው ልጅ ሆኗል።
እንግዲህ በዚህ ዘመን አለመተማመንና መከራ በዝቷል። በየቦታው ጦርነት ብሎም እርስ በእርስ እንደ በግ መተራረድ ሆኗል። ግብሩ የሰይጣን ቢሆንም ዛሬ ላይ ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ግን የሰው ልጆች ናቸው። እና ለሰይጣንም ሥራውን አቀለሉለት ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ጥጋብና ድሎት፤ ስስትና ፍቅረ ነዋይ፤ ክፋትና ተንኮል፤ ድፍረትና ስድብ፤ ፀብና ጥላቻ፤ ሃሰትና ክህደት፤ ትእቢትና ንቀትን እንደ መርፌ ተወግተውት ነው የሚውሉት። ዝሙትንም ፊታውራሪ አድርገው ነው የሚንቀሳቀሱት። አንዳንዶቹን የክፋት ጥጎችማ ሰይጣን ራሱ የሚያውቃቸው አይመስልም። አንዳንዴ እንዲያም ተደብቆ ልምድ የሚቀስም ይመስለኛል።
እማሆይ በጾም ተደብቀው እንቁላል ሲጠብሱ ሰው አያቸውና “እንዴት በጾሙ እማሆይ?፡ ቢሏቸው፣ “ሰይጣን አሳስቶኝ ነው” አሉ። ሰይጣን ራቅ ብሎ ያያቸው ስለነበር፤ “ኧረ ይህችን ዘዴ ገና ዛሬ ከእርስዎ ሰማሁ” አላቸው ይባላል። እና ሰይጣን እያስተማረን ወይስ እያስተማርነው ነው?
ሰይጣን ሥራውን ካስፋፋ በኋላ፤ የሰው ልጅ ቅናትና ተንኮል ውስጡ ሰፍረውበት በሸንጋይ ቃላት ያሰበለት መስሎ የገዛ ወንድሙን ደም እንዲያፈስ ተደረገ። ጥንት በሰይጣን ክፋት ሲጠነሰስ በእርሱ ጥፋት ሌላው ባንድነት ሲወቀስ ነበር። አሁን ደግሞ ሆን ብለው እያጠፉ ሰይጣን አሳስቶኝ ነው ይላሉ። ይኼስ ያሳፍራል።
ቃየን የአዳሙ የሰው ልጅ መግደልን በሰው መነሳትን፤ በጭካኔ ጣርያ ራስን መሳትን ከሰው ልጅ ተማረ። ከዚያም ክፋት ነው በሚለው ዝም ብሎ መቼ ቀረ? እርሱም ተገበረው። ዛሬም ላይ ያሰቡልን መስለው እኛን የሚገሉ ብዙዎች አሉ።
ነብስ እያጠፉ ደምም እያፈሰሱ በተንኮል በክፋት ከሱ የማያንሱ ምድሪቷን አጥለቅልቀዋል። እና ሰይጣን ምን በወጣውና ወደ ምድር መጥቶ ይስራ። ብዙ ለፍቷል፤ ደክሟል፤ አሁን ጡረታ ወጥቶ የክፋት ሥራውን ምድር ላይ ከሚሰሩለት እጆች እየተቀበለ መኖር አይሻለውም ትላላችሁ።
የቅናት ዛር ለብሰው ውስጣቸው ያቄመ፤ በሰው ስኬት ታመው የሚቃዡ፤ በሱሶች ተከበው ቅሌት ተከናንበው መስመር የለቀቁ፤ ስንቶች ናቸው? መረን የወጣን በርቱ የሚሉን ተግሳፅ አልቆባቸው ነውን? ሰውን ለጥፋት ማጨት እንዴት የየእለት ሥራ ይሆናል? ወገን ሰይጣንማ እፎይ ብሏል። የሚያስተን አጠገባችን አብሮን የሚውለው ነው። ያረከሰን ወዳጅ መስሎ ተኮንኖ ያስኮነን የኛው ሰው ነው።
ከሁሉም ነገሮች በላይ ሰብአዊነት መግነን በነበረበረበት ሰዓት የተከመረብን የጥላቻ ደመና አስፈሪ ሆኗል። መቼም ሁሉም ሰው ደግ፣ ሁሉም ባለ ክንፍ መሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ቢያንስ ግን ክፋት አይሎ የሰይጣንን ስራ እስከ መረከብ አያስደርስም ነበር። ህብረተሰባችን መሀል ሰይጣንን ሊያስደምም የሚችል ጥላቻ በዚህ ደረጃ ሲስፋፋ ማየቱ ግን እጅግ አሳሳቢ ነው።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013