የአንድ ወጣት ምርታማነት የሀገር ምርታማነት ነው። የአንድ ወጣት ስኬት የሀገር ስኬት ነው። የአንድ ወጣት ውድቀት የአገር ውድቀት ነው። የአንድ አገር ሀብት ሰላምና እድገት የሚለካው በሀገሪቷ ብሄራዊ ግምጃ ቤት ባለው ሀብት አይደለም። ይልቁንም ምን ያህል የአገሪቷ ህዝቦች ያመርታሉ የሚለው ነገር ነው። የሀገሪቷ ምርት፣ እድገት፣ ሰላም፣ ጥረትና የዜጎች ጥቅል ምርታማነት የዜጎች ሰላማዊነት ነው። የአንድ ወጣት ዜጋ ምርታማነት የአገር ምርታማነት ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም የበጎ ፈቃደኛ ማህበር በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው ስድስተኛው ምርጫ የመራጮች ትምህርትና የስነዜጋ ስልጠና ሲያዘጋጅ ‹‹አንድ ወጣት ለአገሩ ምን ማድረግ ይችላል›› ከሚል ሀሳብ ተነስቶ ነው። ሁሉም ሰው አሁንም ወደፊትም ማንነቱ ሰው መሆን ብቻ ነው።
ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽን አካል ጉዳተኞችም በፖለቲካው መስክ በነፃነት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት በመምረጥና በመመረጥ ከሌሎች ጋር በእኩልነት ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ይደነግጋል። በቀጣይ የሚደረገው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን እንዲሁም ወጣቶች በብዛትና በስነ ምግባር የተመራ እንዲሆን ማህበሩ ስነ ምግባር የዜጋና የመራጮች ትምህርት በስፋት በአራት ቋንቋዎች እያስተማረ ይገኛል። በምርጫ አዋጅ 1162/2011 የተቀመጡ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ለማገዝ መድረኮች እየተዘጋጁ ናቸው።
መንግስት በዴሞክራሲዊ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የምርጫ አሰራሮች፣ ቁሶችንና ስፍራዎችን ተስማሚ እንዲያደርግ ጫና እየተደረገ ሲሆን፤ በምርጫው ወቅት ድምፃቸውን በነፃነትና በሚስጥር የሚሰጡበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባዋል። በምርጫ ወቅት እርዳታ ለሚሹ አካል ጉዳተኞች በሚመርጡት ሰው የመታገዝ መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል። አካል ጉዳተኞችም ተመርጠው በማንኛውም ቦታ የማገልገል እድል እንዲኖራቸው ማድረግ እንዲሁም አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን ማሟላት አስፈላጊም ነው።
‹‹አንድ ወጣት ለአገሩ እድገትና ሰላም ምን ማድረግ ይችላል›› በሚል የስልጠና መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር። መስማት ለተሳናቸው ወጣቶች የመራጮች ስነ ዜጋ ትምህርት ተሰጥቷል። ስልጠናው በቀጣይ በሚኖረው ምርጫ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በጋራ ስራዎች የሚከናወኑበት ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ነው። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም የበጎ ፈቃደኛ ማህበር እንቅስቃሴና በመራጮች ስነ ዜጋ ትምህርት ዙሪያ የማህበሩን ፕሬዚዳንት አቶ ዮሀንስ ጣሰውን አነጋግረናል። ተከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡- የማህበሩ አመሰራረትና የሚያከናውናቸው ተግባራት ምንድናቸው?
አቶ ዮሀንስ፡- የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም የበጎ ፈቃደኛ ማህበር በቅርብ የተመሰረተ ማህበር ነው። አገሪቱ ባለፉት ሶስት ዓመት ውስጥ ያለችበትን ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገቡ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ ወጣቶች የመሰረቱት ተቋም ነው። የተመሰረተበትም ዋነኛ ምክንያት አገሪቱ ያለችበት ሰላም እየቀጨጨ ብጥብጥ በየቀኑ እየሰፋ የመጣ ሲሆን፤ ሰው ከመነጋገር ይልቅ መራራቅን እያሳየ ልዩነት እየሰፋ መጥቷል። ይህን ሁኔታ ወጣቱ እያየ ለምን ዝም ይላል በሚል ከተለያዩ አደረጃጀቶች በመውጣጣት ለመስራት ተነሳን።
ወጣቱ በክልሎች መካከል መልካም መስተጋብር እንዲፈጠር፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ ግጭትን ቀድሞ ለመከላከል፣ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ግጭትን ማረቅ እንዲሁም ሰላምን ለማምጣትና ግጭት አፈታት ዙሪያ ላይ እጃችንን ማስገባት አለብን በሚል የተቋቋመ ማህበር ነው። ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በርካታ የሆኑ ስራዎችን በሰላም ዙሪያ እየሰራ ነው። ለወጣቶች በስፋት የሰላም ግንባታ ላይ ስልጠና ይሰጣል። የውይይት መድኮችን ያመቻቻል። የሰላም ክበባትን በየትምህርት ቤቱ እየተደራጁ ሲሆን፤ የሰላም ጋዜጠኝነት በአገሪቱ በስፋት እንዲሰራ ከመገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ጋር በመነጋገር እየተሰራ ነው።
መገናኛ ብዙሀን አራተኛ መንግስት የሚባሉ እንደመሆናቸው አስፈላጊ ምሰሶዎች ናቸው። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን መገናኛ ብዙሀን ህዝብን ወግነው እየሰሩ ነው ብሎ መናገር አይቻልም። የሰላም ጋዜጠኝትን ተግባራዊ ለማድረግ እንዴት እየተንቀሳቀሱ ነው ብሎ ማየት ተገቢ ነው። ከዚህ ባሻገር በወጣቶች መካከል ግንኙነት እንዲኖርና ማህበራዊ መስተጋብር እንዲጨምር ለማድረግም እየተሰራ ነው። ማህራዊ መስተጋብር በአንድ አገር ውስጥ ህዝብን አንድ የሚያደርግ ነገር ነው። ሰላምን፣ ዴሞክራሲንና ልማትን ለማምጣት እንደማጣበቂያ ነው ማህበራዊ መስጋብርን እየተጠቀምንበት ያለው።
ወቅቱ የምርጫ ወቅት እንደመሆኑ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት የመራጮች ትምህርትና ስነዜጋ ማስተማር ፈቃድ አግኝተናል። ስራዎች እየተሰሩ ያሉት ከዚህ በፊት ለወጣቶች በስፋት ትምህርቱ ተሰጥቷል። በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጪም ተሰጥቷል። ሌላው ትምህርቱን ለሴቶች እንዲሰጥ ተደርጓል። አሁን ደግሞ መስማት ለተሳናቸው ስልጠናው እንዲሰጣቸው ተደርጓል። መስማት ለተሳናቸው አዋጁን መሰረት በማድረግ የመራጭነትና የስነ ዜጋ ትምህርት ነው የተሰጠው። በተጨማሪም አንድ ወጣት ልዩነት መፍጠር የሚችልበት ሁኔታ ጎን ለጎን ለማሳየት ነው እየተሞከረ ያለው። በቀጣይነት ደግሞ ማየት ለተሳናቸው ወጣቶች ትምህርቱ ይሰጣል። ማህበሩ በሰላም ዙሪያ ብዙ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የምርጫ ትምህርት ለአካል ጉዳተኞች ከመስጠት በዘለለ በምርጫው ወቅት የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ማህበሩ የሚሰራቸው ስራዎች አሉ?
አቶ ዮሀንስ፡- አካል ጉዳተኞች በምርጫው ወቅት ለሚገጥሟቸው ጉዳዮች ማህበሩ ጣልቃ መግባት አይችልም። ማህበሩ ዋነኛ ስራው ሙግትና ውትወታ ነው። ምክንያቱም በአዋጅ የተሰጠው ስልጣን ስለሌለው ነው። ስልጠናዎች በሚሰጡበት ወቅት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከመንግስት የሚጠበቁ ነገሮችን እንዲያሟላ እንዲሁም በሚካሄደው ምርጫ ውስጥ ማህበሩ የተለያዩ ነገሮች እንዲያሟሉ ውትወታ ነው ሊሰራ የሚችለው። ከዚህ በዘለለ ደግም ያልተከናወኑ ተግባራት ላይ ጫና መፍጠር ነው ሊያደርግ የሚችለው። ለምሳሌ ቴክኖሎጂዎች የሚያስፈልጉ ከሆነ የቴክሎጂ እገዛ እንዲያደርግ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ያልሆነ ምርጫ ጣቢያ ካለ አካል ጉዳተኞችን እንደ ማግለል ይታያል ማለት ነው። ስለዚህ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲኖሩ ሊደረግ ይገባል።
በምርጫ መስጫ ቀን ደግሞ ደጋፊ የሚሆናቸው አካል ይኖራል። ለዚህ ሰው ተገቢ የሆነ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። በአንድ ካርድ ሁለት ሰው ነው ሊሄድ የሚችለው። ምክንያቱም አንደኛው ሰው ድጋፍ የሚሰጥ በመሆኑ ነው። ስለዚህ መንግስት በዚህ ዙሪያ ሊሰራ ይገባል። የአካል ጉዳተኞችን ጥቅም በልዩ ሁኔታ አስከብራለው የሚል ፓርቲ ካለም በአዋጁ መሰረት የተሻለ ጥቅምና ድጋፍ ከምርጫ ቦርድ እንዲደረግለት ስለተቀመጠ ተግባር ላይ እንዲውል ማህበሩ ውትወታ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫው ወቅት እገዛ የሚያደርጉ በጎ ፈቃደኞች ተዘጋጅተዋል?
አቶ ዮሀንስ፡- በምርጫው ወቅት ስራ የሚያከናውኑ በጎ ፈቃደኞች ተዘጋጅተዋል። የስነ ዜጋ ትምህርት ማስተማር ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ምርጫ መታዘብ ማህበሩ ፊቱን ያዞራል። በወቅቱና በምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር መሰረት ነው ስራዎች እየተሰሩ ያሉት። ለምርጫው የተዘጋጁ በርካታ በጎ ፈቃደኞች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዴት ነበር?
አቶ ዮሀንስ፡- በአገሪቱ በተከናወኑ ምርጫዎች ውስጥ የምርጫ ታዛቢ በመሆን አገልግዬ ነበር። በነዚህ ወቅቶች ለብቻቸው መድረክ ተሰጥቷቸው የተሰራበት ጊዜ አልነበረም። በወቅቱ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ስራዎች አለመከናወናቸው በድክመት ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። የነበረው ችግር መቀጠል ስለሌለበት በእኩል መንገድ ሊሳተፉ እንደሚገባ በማሰብ ነው ስልጠናዎች እየተዘጋጁ ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫው የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳና ክርክር መስማት የተሳናቸው ወጣቶችን ተደራሽ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ዮሀንስ፡- በምርጫው የሚሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ቅስቀሳና ክርክር መስማት የተሳናቸው ወጣቶችን ተደራሽ ያደረገ አይደለም። የማህበሩ ዋና አላማም በቴክኖሎጂ መደገፍም ካለባቸው በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ መደረግ አለበት። የምርጫ ቅስቀሳው በምልክት ቋንቋ እንዲተረጎም መደረግ ነበረበት። ይህ ደግሞ ውለታ ሳይሆን ግዴታ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን ፓርቲዎች መስማት ለተሳናቸው ተደራሽ ሆነዋል ብሎ መናገር አይቻልም።
በቴሌቪዥን ከሚተላለፍ ዜና ውጪ ሌሎች ነገሮች መስማት ለተሳናቸው የተዘጋጁ አደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ በሁሉም መገናኛ ብዙሀን እንደመተላለፋቸው መስማት የተሳናቸው ወጣቶችን ተደራሽ ያደረገ ነገር የለውም። ቅድሚያ ፓርቲዎች ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። ፓርቲዎች እነዚህን ማህበረሰቦች በሚገባቸው ቋንቋ ተጠቅመው ሃሳባቸውን ሊገልፁ ይገባል። ምርጫ ቦርድም ይህን ታሳቢ በማድረግ የተመደቡ የአየር ሰዓት ላይ ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ በመሆናቸው ተደራሽ ለማድረግ የአየር ሰዓት እንዲመደብ ማድረግ አለበት። በሚገባቸው ቋንቋም እንዲተላለፍ ጫና ሊፈጥር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቶች ለአገራቸው እድገትና ለሰላም ምን ማድረግ አለባቸው?
አቶ ዮሀንስ፡- ወጣቶች በአንድ አገር ውስጥ ያላቸው ሚና በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ወጣት በብዛት የሚገኝ በመሆኑ የወጣት አገር ነው የሚባለው። እነዚህን ወጣቶች ወደ ተግባር ማስገባት ከመንግስት ብዙ ይጠበቃል። በዚህ ሰዓት ወጣቱ ለአገሩ እድገት የራሱ ሕይወት መቀየር አለበት። የራሱን ሕይወት ሲቀይር የስራ ባህልና ኢኮኖሚውን ያነቃቃዋል። ለወጣቱ የሚያስፈልገው የስራ ባህል አብዮት ነው። የመንግስት ስራ ለወጣቱና ለአገር እድገት እንደማይሆን ወጣቱ ሊረዳ ይገባል። የአገሪቱ የመንግስት ሰራተኛ ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ በየጊዜው እየተመረቀ የሚወጣው ወጣት የስራ ባህል አብዮት አስነስቶ የራሱን ሕይወት ራሱ ነው መቀየር ያለበት። ስለዚህ በዚህ እሳቤ ውስጥ ቢገባ ለአገሩ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሚተርፍ ነገር መስራት ይችላል።
ወጣቱ በሰላም ዙሪያ ሁሌም እየተማገደ ያለው ወጣቱ ነው። ወጣቱን በመተማመን ነው እነሱ መቻቻል ያቃታቸው። “ወጣቱን መስዋዕት በማድረግ ከምንፈልግበት ደረጃ እንደርሳለን” የሚል ሀሳብ ውስጥ የሚገኙ ፓርቲዎች አሉ። ስለዚህ ወጣቱ ሊነቃ ይገባል። ወጣቱ በአዎንታዊ አስተሳሰብ የተሻለ ሆኖ በመገኘት፣ ድምፅ እንጂ ሕይወቴን አልሰጥም ሊል ይገባል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 22/2013