
ዓለም በአሁኑ ወቅት በኮሮና ወረርሽኝ እየተናጠች ትገኛለች።
ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ይህ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሀገራቱን እያስጨነቀ ይገኛል።
የበለፀጉ የሚባሉት ሀገራት ለወረርሽኙ ክትባት በማግኘታቸው ዜጎቻቸውን መታደግ እየቻሉ ነው።
ከክትባቱ መገኘት በኋላ በአንዳንድ ሀገራት በቫይረሱ ተይዘው ሕይወታቸው የሚያልፍ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።
ከ53 በመቶ በላይ ዜጎቿን የመጀመሪያ ዙር ክትባት እንደሰጠች የሚነገርላት ሀገረ አሜሪካ የክትባት ፍትሐዊነት መርሕን አልጠበቀችም እየተባለች ትነሳለች።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ገና ፍቃድ ያልሰጣቸው በርካታ የክትባት አይነቶች በአሜሪካ ውስጥ ተከማችተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ የክትባት ክምችት የተለያዩ አገራት በቂ ክትባት ማግኘት ሳይችሉ የአሜሪካ መንግሥት ግን ከሚያስፈልገው በላይ ክትባት እያከማቸ ነው የሚል ትችትንም እንዲስተናግድ በር ከፍቷል።
ባለፈው ወር ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አራት ሚሊየን የአስትራዜኒካ ክትባት ለሜክሲኮ እና ለካናዳ ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር።
በሕንድ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ፤ አሜሪካ ያከማቸችውን ክትባት እንድትለግስ ጫና እየተደረገባት እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
ይህን ተከትሎ ነው አሜሪካ ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ለሌሎች አገራት ልትሰጥ መሆኑን ያስታወቀችው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ክትባቶቹ አስተማማኝነታቸው ተረጋግጦ በቀጣይ ወራት ወደተለያዩ አገራት እንደሚላኩም ይጠበቃል።
ከህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የስልክ ውይይት ያደረጉት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ኦክስጅን፣ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሣሪያ፣ ክትባትና ሌሎችም ምርቶችን ለመስጠት ቃል ስለመግባታቸው ተገልጿል።
መልካምና ሞቅ ያለ እንደነበር በተነገረለት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የስልክ ውይይት ፤ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብተውላቸዋል።
ከድጋፎቹ መካከል የኦክስጅን ነክ ቁሳቁስ፣ የክትባትና ሌሎች ኮቪድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ የሕክምና ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት ተነግሯል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በቀጣይ ሳምንታት የክትባቶቹን ደኅንነት ፈትሾ ፍቃድ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጀን ሳኪ በሰጡት መግለጫ አንስተዋል። ከዚያም ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራዜኒካ ክትባት ወደተለያዩ አገራት እንደሚላክ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሌሎች ሀገራት እንደሚተላለፉ ጠቅሰዋል። ለአገራት ይከፋፈላል የተባለው የተቀረው 50 ሚሊዮን ክትባት በተለያየ የምርት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም እየተነገረ ነው።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ እንዳሉት የትኞቹ አገራት ክትባቱን እንደሚያገኙ በቀጣይ በዝርዝር የሚገለፅ ይሆናል።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እስካሁን ፍቃድ የሰጠው ለፋይዘር ባዮንቴክ፣ ለሞደርና እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተሰኙ የኮሮና ክትባት አምራች ድርጅቶች ነው።
እነዚህ የተጠቀሱት ክትባቶች ለአገሪቱ ዜጎች በቂ ስለሚሆኑ ተጨማሪ የአስትራዜኒካ ክትባት እንደማያስፈልግ ተንታኞች ይናገራሉ።
ስለሆነም አሜሪካ በሀገሪቱ ውስጥ ተከማችተው የሚገኙ ሌሎች ክትባቶችን ለሌሎች ሀገራት አሳልፋ እንድትሰጥ ይመክራሉ።
እስካሁን በአሜሪካ ከ53 በመቶ በላይ የሚሆኑ አዋቂዎች የመጀመሪያ ዙር ክትባት አግኝተዋል።
የባይደን አስተዳደር ወደ 60 ሚሊዮን የሚጠጋ ክትባት ለመለገስ ውሳኔ ማሳለፉ “የክትባት ዲፕሎማሲ” ሲሉ ተንታኞች ገልጸውታል።
ይህ የአሜሪካ አካሄድ ሌሎች ሀገራትም የእሷ ፈለግ በመከተል ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ያነሳሳል።
በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካ በውጭ ሀገራት የምትከተለውን የዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይህ ቀና ያደርገዋል ተብሎም ይጠበቃል።
ሀገራቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸገሩበት ባለበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ 60 ሚሊዮን መጠን ያላቸውን ክትባት ለመለገስ መወሰኗ የዓለም ጤና ድርጅት የያዘውን ሀገራት በፍትሐዊነት ክትባቱን በተባበረ ክንድ ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት የሚደግፍ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥ ኮሮናን ከመከላከል አኳያ ያለባቸው ጫና የተለሳለሰ ይመስላል፤ ምክንያቱም በሀገሪቱ ቁጥሩ ከፍ ያለ የክትባት መጠን ተከማችቶ ይገኛልና። አሁን ላይ በአሜሪካ የሚስተዋለው ችግር የክትባት መጠን መብዛት ሳይሆን ዜጎች ክትባቱን እንዲጠቀሙ ማሳመን የሚለው ነው።
በተጨማሪም ሀገሪቱ በሀገር ውስጥ የምታደርገው የኮሮና የመከላከል ጥረት በሌሎች ሀገራት ጥረት ካልተደገፈ ውጤቱ እምብዛም ይሆናል።
የዓለም ጤና ድርጅት ደጋግሞ ጥሪ እንደሚያቀርበው ኮሮናን የመከላከል ጥረት ውጤታማ የሚሆነው ሀገራት የተናጠል እርምጃ በመውሰድ ሳይሆን በጋራ በትብብር የቫይረሱን ስርጭት በጋራ መከላከል ሲችሉ ብቻ ነው።
ለዚህ ደግሞ አንዱd ና ዋናው የክትባት ፍትሐዊነትን ዓለም ላይ ማስፈን እስካልተቻለ ድረስ የኮሮና መከላከል ተግባሩ እንከን ይገጥመዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013