በአንድ መንደር የሚኖሩ ሰዎች በምሽት እሳት ተነሳባቸው፤ እሳቱ ቤቶችን አቃጠለ ንብረት አወደመ ፤ የተወሰኑ ከብቶችም ማምለጥ ሳይችሉ የእሳት ራት ሆኑ፤ ገሚሶቹም አምልጠው የጅብና የሌሎች አውሬዎች ራት ሆኑ፤ እሳቱ ከቤቱ አልፎ በግቢያቸውና በአቅራቢያቸው የሚገኙ ዛፎች ማቃጠል ጀመረ።
የመንደሩ ነዋሪዎች ተሰብስበው እሳቱ ለማጥፋት ጣሩ ሞከሩ። ካልተቃጠሉት ቤቶች ያሉ ነዋሪዎች የእንሥራቸውን ውሃ ይዘው እሳቱ ላይ እና ቀጥሎ ያቃጥላቸዋል ባሉት ላይ ውሃውን ረጩ። እሳቱ ሲቃጠል በአቅራቢያው ምንጭ ውስጥ የሚኖሩ እንቁራሪቶች ነበሩ። በምሽት የእሳቱን ውበትና ድምቀት አይተው ተደመሙ። በምንጩ ውስጥ ሆነው በደስታ ፈነጩ ሳቁ፤ ግማሾቹ ግን በእሳቱ ሁኔታ አዘኑ ተሳቀቁ ።
በሚያዝኑትና በሚደሰቱት እንቁራሪቶች መካከል ውዝግብ ተፈጠረ፤ የሚደሰቱት እንቁራሪቶች የሚያዝኑትን አቻዎቻቸውን ምን ያሳዝናችኋል እንደኛ አትደሱትም ወይ? ሞኞች ተላሎች ብለው ሰደቧቸው። በእሳቱ ሁኔታ ያዘኑት እንቁራሪቶችም እሳቱ እኛ ጋርም ሊመጣ ይችላል ብለው መለሱላቸው። የተደሰቱትም እንቁራሪቶች ሞኞች ያልናችሁ እኮ ለዚህ ነው፤ እሳቱ እኛ ጋር እንዴት ነው የሚመጣው? ቢመጣም እኮ ያለነው ውሃ ውስጥ ነው። እንዴት ያቃጥለናል አሉ ?
በእንቁራሪቶቹ መካከል የነበረው ክርክር ሊገታ ስላልቻለ ፤ያዘኑት እሳቱ እስኪጠፋ ዐለት ሥር ሆነን እንሸሸጋለን ብለው ከምንጩ ወጡ። በምንጩ ውስጥ የነበሩት እንቁራሪቶች ፈሪዎች ብለው ሳቁባቸው። የመንደሩ ሰዎች እሳቱን ማጥፋት ስላልቻሉ ወደ ምንጩ መጡ። በጣሳ እየቀዱ እንሥራቸውን ሞልተው በብዛት እየቀዱ ይመላለሱ ነበር። በዚህ መሐል በምሽት ከምንጩ ውሃ ሲቀዱ እንቁራሪቶቹ በእንሥራ ተቀድተው እሳቱን ለማጥፋት የእሳት ራት ሆኑ። በዐለት የተሸሸጉት ግን ዳኑ።
ይህ ተረት በትውፊት (በቅብብል) ለእኛ የደረሰ ነው። በሀገራችን የምናየው የሁከት ድራማ በምንጩ ውስጥ እንዳሉት እንቁራሪቶች እንዳይሆን እንሰጋለን። የጨው ገደል ሲናድ ሞኝ ይስቃል ብልህ ያለቅሳል እንደሚባለው ብሂል ሀገራችንን ከጎሰኝነትና ጎጠኝነት አዙሪት ነፃ ልናወጣት ይገባል።
ሀገራችን ትልቅ ብሔራዊ ጉዳዮች እየጠበቃት ትገኛለች፤ የኮሮና ወረርሽኝን ሥጋት እንዳለ ሆኖ ሀገር አቀፍ ምርጫም ይጠብቀናል። ባለፈው ዓመት ክረምት የመጀመሪያው ሙሌት የተካሄደው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በቀጣዩ ክረምት ሁለተኛው ዙር በእጥፍ ይሞላል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ነገር ግን የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችውን የምሥራቅ ፊታውራሪና ሰላም አስከባሪ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማዳከም ባንዳዎችና ቦዘኔዎች እየጣሩ ነው። የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሀገር ሰላምና ፀጥታ ያስፈልጋል። ቱሪስቶችን ከውጭ ለመሳብና ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባ ለማካሄድም እንዲሁ፤ ይህ ደግሞ በውጭ ምንዛሪ እጥረት እየተንገዳገደች ላለችው ሀገራችን ሌላ የገቢ ምንጭ ነው።
ግብጽን ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱን በጎ የማይመኙ ሀገራት የኢትዮጵያውያን ጎጥና እምነት ተኮር ብጥብጥ በናፍቆትና በጉጉት የሚጠብቁት ነው። ምናልባት በየቦታው የሚሰማው ሁካታ የታላቁ ህዳሴ ግድብ እንዳይሞላ ታስቦ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠሩ አይከፋም።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግሥት ሥልጣን የተረከበው ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ነው፤ ለውጥ ይመጣል ብለን ስንናፍቅ ነውጥ እያየን ነው። ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ነበሩ። ግን ማን ይጨርሳቸው?
የኢትዮጵያ ሰላም ሲደፈርስ ምዕራባውያን እጃቸውን አጣጥፈው የሚያዩበት አንዳች ምክንያት የላቸውም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሰላም መናጋት ለምስራቅ አፍሪካውያን ትልቅ ስጋት ነው፤ይህም ጦሱ ለራሳቸው ለምዕራባውያን የሚተርፍ በመሆኑ ነው።
ሕጻናትን፣ አዛውንትና ሴትን መግደል ጀግንነት አይደለም፤ መሣሪያ ያልታጠቁ ወንዶች መግደል እንኳ ከጀግና ተራ የሚያስመድብ አይደለም። የፈሪ ዱላ የሚያስብል ነው። የመንግሥት ኃላፊነት የዜጎችን ደህንነትን መጠበቅ ነው።
እነ ማንዴላ ፣እነ ጋንዲ ስማቸው ከመቃብር በላይ የሆነው ከቂም በቀል ነፃ ሆነው ሀገራቸውን ነፃ አውጥተው ስለመሩ ነው። መሪዎቻችን የነሱን ፈለግ ይከተሉ ፤ ተጨቁነን ነበር ብሎ መጨቃጨቅ ለሀገር ፋይዳ ያለው አይመስለኝም።
ምርጥ ዘር ነን ሲል የነበረው የጀርመኑ ሂትለር፤ አይሁዶች ሰብስቦ ጨፈጨፈ ፤ቀስ በቀስም ሌሎች ሀገሮችን ማጥቃት ጀመረ ፤በዚህም የዓለም ጦርነት ተፈጠረ። ስለዚህ የፖለቲካ ስልጣን የበላይነትን ለመቆናጠጥ ሲባል በንጹሃን ዜጎች ደም መነገድ በኋላ ኋላ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከትል ከሂትለር መማር ይበጃል።
የአንድ መንግሥት አብይ ሥራው የዜጎች ሰላም መጠበቅ፣ የሀገርን ሉዓላዊነትና ደህንነት ማስከበር ነው። የዜጎች ሰላም ሲጠበቅ ሕዝቦች በሰላም ወጥተው በሰላም ይገባሉ፤ ይማራሉ ያስተምራሉ፣ ይነግዳሉ ያተርፋሉ፣ ሌሎችም በኩራት ገበያ ወጥተው የዕለት ምግባቸውን የዓመት ልብሳቸውን ይሸምታሉ። አርሶ አደሩ ያርሳል፤ ምርቱን ያፍሳል ፣አርብቶ አደሩም እንስሳቶችን እያረባ ኑሮውን ይመራል ። አገርም ትለማች፤ ኢንዱስትሪው ይስፋፋል ። ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ይፈጠራል ። የዜጎች የኑሮ ደረጃ እየተሻሻለ ይመጣል።
ለመዝናናትም ሆነ ለመጽናናት የሀገር ሰላም አስፈላጊነት አያጠያይቅም። የሞተን ለመቅበር ሰላም ያስፈልጋል። ለመማርም ሆነ ለመማረር ለማብሰልም በሉት ለመብሰል የሀገር ሰላም ወሳኝ ነው። በየቦታው የምንሰማቸው ሁካታዎችና ረብሻዎች ዜጎችን እረፍት እየነሱ ነው። ጋጠወጥነት እየነገሠ የዜጎች ሰላም እየደፈረሰ ነው።
የኢትዮጵያ ሰላም ደፈረሰ ማለት የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ሰላም ሁሉ የሚናጋ መሆኑን ለመናገር የፖለቲካ ሳይንቲስት መሆን አይጠበቅብንም። ግብር ለሚገብረው ዜጋ መንግሥት ሰላምና ደኅንነቱን ማስጠበቅ አለበት።
ጋጠወጦች እየፈነጩ በኢትዮጵያ ሁከትና ዕልቂት ሊያመነጩ ቢችሉም ሥልጣን መቆናጠጥ ግን አይችሉም። የሚሰሙ ድምጾች ትሻልን ትቼ ትብስን እንደሆነብን የሚያመለክቱ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት በሠሩት መልካም ሥራ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልካም ሥራ የሚያደበዝዙ እየበዙ ነው። ፤ለዜጎቻችን ጥንቃቄ ይደረግ፤ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ።
ይቤ ከደጃች. ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2013