መዲናችን አዲስ አበባ በየዕለቱ ከምታስተናግዳቸው በርካታ ትዕይንቶች አንዱ በጎዳናዋ ውለው የሚያድሩ ዜጎቿ ጎስቋላ ህይወት አንዱ ነው። አለፍ ሲልም ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው የዕለት ጉርስ ፈላጊ አዛውንቶችን በየጎዳናው ማየት አዲስ ሆኖ አያውቅም። በርካታ ቁጥር ያላቸው ህፃናትና ወጣቶችም በቀኑ ውሎ ረሀባቸውን ለማስታገስ ቤንዚንና ማስቲሽ ሲስቡ፣ ሌሊቱን ደግሞ በብርድ፣ በዝናብና በቁር ተቆራምደው በየጥጋጥጉ ተደራርበው ሙቀት ሲጋሩ ማስተዋል የተለመደ ሆኗል።
የጎዳና ህይወት እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ ለበርካታ ወጣቶች አፈንጋጭ ባህሪይ እንደምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል። ለእነዚህ ወጣቶች ወደጎዳና ሕይወት መውጣት የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ ይታወቃል። አንዱና ዋነኛው ድህነት ቢሆንም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ወጣቶች ደግሞ ወላጆቻቸውን ድንገት በሞት ማጣታቸውና ከቤት ውጭ ያለው ህይወት የተሻለ መስሎ ስለሚታያቸው መሆኑን ይጠቀሳሉ።
ለዚህ እውነታ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በጎዳና ያሉ ልጆች ከሚገጥማቸው ችግር በላይ ከቤተሰብ መነጠላቸው ብቻውን የሚፈጥረው የስነ ልቦና ቀውስ ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ ያልተገባ ባህሪይ እንዲላበሱ፤ ስራ ፈትነትን እንዲለማመዱ፤ ነገን በተስፋ እንዳይመለከቱ ምክንያት ሆኖ ለሀገር ሸክም ይሆናሉ። በተመሳሳይ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና የወጡ አንዳንዶች ደግሞ፤ እራሳቸውን ለመለወጥና ከአስከፊው የጎዳና ህይወት ለመውጣት በርካታ የስራ ዕድል አማራጮችን ተጠቅመው ህይወታቸውን ለመቀየር ዝግጁ ይሆናሉ።
ከሚገኙበት አስከፊ ማንነት ለመላቀቅ ከሚተጉና ዓላማ ሰንቀው ህልማቸውን ለማሳካት ሌት ተቀን ከሚታትሩ ብርቅዬ ወጣቶች መካከል ሀየሎም ሞናናው አንዱ ነው። ሀየሎም ሕይወቱን በጎዳና ከመሰረተ የቆየ ቢሆንም፤ ታሪኩን ለመለወጥ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ዛሬ ከጎዳና ሕይወት ወጥቶ የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል።
“አባት የቤተሰብ አስተዳዳሪና ምሰሶ ነው” የሚለው ሀየሎም ጎዳና ለመውጣቱ መነሻ ወላጅ አባቱን በጨቅላ ዕድሜው በሞት ማጣቱ እንደሆነ ይናገራል፤ የዛኔ እናቱ እሱን ጨምሮ አምስት ልጆቻቸውን በወጉ የሚያስተዳድሩበት ገቢ አልነበራቸውም፤ ሀየሎም የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ባዘነ። እናቱንም ለማገዝ ሲል ያልሞከረው አልነበረም። እንዳሰበው ግን አልቀናውም። ገና በዘጠኝ ዓመቱ የጎዳናን ሕይወት “ሀ” ብሎ ሊጀምር ተገደደ።
ሀየሎም እህት ወንድሞቹ ወደ ዘመድ ሲጠጉ አንድ ወንድሙ ወደ ማደጎ መግባቱን ይናገራል። እሱ ግን ለአስር ተከታታይ ዓመታት ጎዳና ላይ ሊቆይ ግድ አለው። በዚህ ህይወት የሚገጥሙትን መልካምና ክፉ ነገሮች ሁሉ እንደአመጣጣቸው ተቀብሎ ሲጋፈጣቸውም ቆየ። ያም ሆኖ ግን ነገን የተሻለ ለማድረግ የሰነቀውን ራዕይ አልረሳም። የተበተነ ቤተሰቡን መልሶ ነገን በተሻለ ለመኖር የሰነቀውን ዓላማም አልዘነጋም።
ወጣቱ ሁሌም ቢሆን በውስጡ ያደመቀው የተስፋ ቀለም ደብዝዞበት አያውቅም። ይህን እውነታ ለማሳካትም ብርቱ ከመሆን ሊርቅ አይወድም። ዓላማውን ዳር ለማድረስ ደግሞ ዘወትር እንደተጋ መዋልን ምርጫው ሲያደርግ ቆይቷል። ልፋቱ ፍሬ እንዲይዝለትም እሱን ከመሰሉ አጋሮቹ ጋር በላቡ ወዝ ማደርን ፈቅዷል።
ሀየሎም በጎዳና ቆይታው ከ42 መሰል ባልንጀሮቹ ጋር በመሰባሰብ «ዲዚ» (ብረት) እየለቀመ መሸጥን ለመደ። ይህ መሆኑም ለኪሱ ገንዘብን አስገኘለት። ጓደኞቹ በመግባባት እየተሳሰቡ አቅማቸውን ሊደግፉ ታተሩ። የእርስ በርስ መዋደዳቸውም ለቁጥር የበዙ መልካምና ክፉ አጋጣሚዎችን በጋራ እንዲያልፏቸው ምክንያት ሆነ።
ዋል አደር ሲል አርባ ሁለቱ የጎዳና ጓደኛሞች የአንድ በጎ ፈቃደኛ ወጣትን አይን ማረኩ። ይህ መሆኑም መልካም ስነ-ምግባርን እንዲላበሱ ምክንያት ሆነ። ነገን ተስፋ እንዲያደርጉ በሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርም መታገዝ ጀመሩ። ሀየሎም ይህኔ የውስጡ ሀሳብ ሊሳካ መሆኑ ገባው። እሱን ጨምሮ ጓደኞቹን ከተለያዩ ሱሶች በማራቅ፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ መኖር ጀመረ።
ወጣቶቹ አፈንጋጭና ያልተገባ ባህሪን በማስወገድ «አሌክስ» እያሉ ከሚጠሩት በጎ አሳቢ ወጣት ዓለማየሁ ተስፋንና መልካም ባህሪን ገንዘብ ማድረግ ቻሉ። ዓለማየሁ በተለይም ሀየሎም ለትምህርቱ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት በመረዳቱ በወር 35 ብር እየከፈለ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቱን በማታው ክፍለ ጊዜ መማር እንዲችል አደረገ።
ዓለማየሁ ልጆቹን የበለጠ ለማገዝ የውጭ ዜጎችን አስተባብሮ ለሶሰት ዓመታት የግንዛቤ ማሰጨበጫ ስልጠናዎች እንዲሰጣቸው ዕድል ከፈተ። በዚህ አጋጣሚምም ልጆቹ ሼድ ተከራይተው በመጠለያ እንዲቆዩ አደረገ። ሀየሎምን ጨምሮ ትምህርታቸውን መቀጠል የሚፈልጉትን በመለየት በቀኑ ክፍለጊዜ እንዲከታተሉ ተመቻቸላቸው። ቀሪዎቹ ደግሞ እንደየፍላጎታቸው የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ በተፈጠረላቸው የስራ መስኮች መሰማራት ቻሉ።
“ጎዳና ላይ ሆኜ እንኳን ትምህርት ስማር ደብተሬን ዝናብ እንዳይነካብኝ በጀርባዬ አድርጌ ተንጋልዬ ነበር የምተኛው” ሲል ሀየሎም የትላንቱን ማንነት ዛሬ ላይ ቆሞ ያስታውሳል። በጎዳና ህይወት የጎልማሶች ትምህርትን የጀመረው ሀየሎም፤ የተፈጠረለትን ዕድል ተጠቅሞ ዓላማውን ለማሳካት ዛሬም እየተማረ ይገኛል። ወጣቱ አሁን በአድማስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሁለተኛ ዓመት የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተማሪ ነው። ታታሪውና ሩቅ አሳቢው ወጣት።
ሀየሎም የጎዳናን አስከፊነት ከክረምቱ ፈተና ጋር ያይዘዋል።በዚህ ጊዜ ለጎዳና ነፍሶች ዝናብና ብርዱን መቋቋም ቀላል አይሆንም። ይህን ሲያስብ ከጓደኞቹ ጋር የነበረው መልካም ጊዜ ውል ይለዋል። አንዱ ለሌላው የነበረው መከባበርና ጥልቅ ፍቅር ዛሬም ድረስ የማይረሳ ነው።
ወጣቱ ለመማር፣ ለማወቅና፣ ለመለወጥ ባለው ተነሳሽነት በሚኖርበት መገናኛ አካባቢ የቀበሌ ቤትን ማግኘት ችሏል። የትምህርት ቤት ወጪውንም በአካባቢ የምትኖር ሌላ በጎ ፈቃደኛ ታግዘዋለች። ሀየሎም፤ይህን በማግኘቱ ብቻ «ይበቃኛል» ሲል አላረፈም። ዛሬም ያገኘውን በመስራት የዕለት ጉርሱንና የዓመት ልብሱን ይሸፍናል።
ትምህርት ለማንኛውም ሰው ቁልፍና ወሳኝ መሆኑን የሚያምነው ሀየሎም አሁን ላይ ከሚሳተፍባቸው መካከል አንዱ መገናኛ አካባቢ በሚገኘው ዘርፈሽዋል ትምህርት ቤት የጎልማሳችን ትምህርት ማስተማር ነው። በዚህም የሚያገኘውን አነስተኛ ክፍያ የተለያዩ ወጪዎቹን ሸፍኖ ኪሱን ይደጉማል።
«ተግባር ተኮር ተብሎ የሚሰጠውን የጎልማሶች ትምህርት በማስተማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔም ያለፍኩበት ህይወት እንደመሆኑ እንዲህ ነበርኩ እያልኩ ሳስተምራቸውና ምክር ስሰጣቸው ከሌላው ይልቅ በቀላሉ ይቀበሉኛል፤ ያምኑኛል፤ ያደምጡኛል። ይህ ደግሞ ለኔ ትልቅ ስንቅ ነውና የበለጠ እንድሰራ ያግዘኛል» ይላል።
መንግስት አሁን የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማንሳት እያደረገ ያለው ጥረት በጣም መልካምና የሚደገፍ ጉዳይ መሆኑን የሚያምነው ሀየሎም፤ አሰራሩ ላይ የሚስተዋሉ አንዳንድ ክፍተቶች ግን ሊስተካከሉ እንደሚገባ ይጠቁማል። ሀየሎም በአካባቢው የጎዳና ተዳዳሪዎች አስተባባሪ እንደመሆኑ የሚነሱትን የመለየትና የማቅረብ ስራ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን እንዲያሰተባብር ተነግሮታል። ይሁን እንጂ እነሱ የማያውቋቸውና በአካባቢው ያልነበሩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደ መጠለያ መግባታቸው እያሳሰበው ነው።በእሱ እምነት እነዚህ ወገኖች ሲመገቡ ከማየት የዘለለ ድርሻ አልተሰጠንም ባይ ነው።
« በእኛ አካባቢ ያሉ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ወደ መጠለያው ለመግባት ባላቸው ጉጉት እኛን ይጠይቃሉ፤ እኛም ወረዳውን በምናነጋግርበት ወቅት ሞልቷል የሚል ምላሽ ይሰጠናል» ሲል ሀየሎም ስጋቱን ይገልጻል። ወደ መጠለያው የገቡት የጎዳና ልጆች እንዴትና ከየት እንደመጡ ግልጽ የሆነ ነገር እነደሌለ የሚናገረው ወጣት ይህ አጋጣሚ መንግስት ያመጣውን ዕድል ለመጠቀም ሲጠብቁ የነበሩ በርካታ የጎዳና ልጆችን ተስፋ አስቆርጧልና ሊታሰብበት ይገባል ይላል።
ይህ የተጀመረው መልካም ተግባርም ቀጣይነት ኖሮት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል መንግስት ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል። የሚለው ወጣት ሀየሎም የጎዳና ልጆችን የማንሳት ስራው የተከናወነው ያለምንም ጥናትና ውይይት እንደሆነ ይሰማኛል። ምክንያቱም ሁሉንም በአንደ ጊዜ ማንሳት እንደማይቻል የታወቀ ነውና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ህፃናትና የልጅ እናቶች በአካባቢው እንደነበሩ መታዘቡን ይናገራል።
መንግስት ለዜጎቹ በተለይም ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ላደረጉት ከቤተሰብ ቀጥሎ ያለው ሁለተኛ ኃላፊ እንደመሆኑ ትኩረት በመስጠት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ይቀጥል፤ በመጨረሻም ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሆን ችግሮችን በመለየት፣ በመመካከርና በመወያየት ውጤታማና ከሀሜት የጸዳ ስራ ቢሰራ መልካም ነው እያልን፤ የወጣት ሀየሎም ትጋትና ጥንካሬ ከጎዳና ሕይወት አንስቶ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያደረሰው በመሆኑ ብዙዎቻችን ከሱ ልንማር ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2011
በፍሬህይወት አወቀ