
ቦጋለ አበበ
ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አንድ ክለብ በትንሹ ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ እንደሚያደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የተጫዋቾች ክፍያ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ክለቦች የተጫዋቾችን የወር ደመወዝ መክፈል ስለተሳናቸው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክስ ሲቀርብ በተደጋጋሚ ታይቷል።
የክለቦች የወጪ ዕድገት አንድ መላ ካልተበጀለት በርከት ያሉት ክለቦች በውድድሩ ላይ የመቆየት ዕድላቸው አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ምልክቶች መታየት የጀመሩት ባለፉት አመታት ነው። በተለይም ከሁለት አመት በፊት በየዓመቱ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ የተጫዋቾች ክፍያና አጠቃላይ የበጀት ጫና ምክንያት አደጋ ውስጥ የገቡ ክለቦች ቁጥር አንድና ሁለት እንዳልነበረ ይታወሳል።
መንግሥት ለእግር ኳሱ የሚመድበው በጀትና የተጫዋቾች ክፍያ ነባራዊውን የአገር ኢኮኖሚ ያላገናዘበ፣ የክለቦች የፋይናንስ ስርዓት የሌለበት፤ ዘመናዊ የእግር ኳስ አመራርና አደረጃጀት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሊጉ መቀጠሉ ብዙ ትችቶች አስከትሎ ነበር። ብዙዎቹ ክለቦች ቋሚ ገቢ የሌላቸውና ከከተማ አስተዳደሮችና በመንግሥት ተቋማት በቀጥታ በጀት የሚመደብላቸው መሆናቸው ይታወቃል፤ የተጫዋቾች ዝውውርና ሌሎች ክፍያዎቻቸውም ከዚሁ በጀት ላይ የሚታሰብና የሊጉ ተወዳዳሪዎች በየዓመቱ ከ30 እስከ 80 ሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱበት ደረጃ ላይ ደርሰው እንደነበር ይታወቃል።
ባለፉት አመታት ክለቦችን ከተጫዋቾች ደመወዝ በተጨማሪ በየከተሞች ተዘዋውሮ መጫወት ለከፍተኛ ወጪ እንደዳረጋቸው ወቀሳዎች ቢሰነዘሩም በኮቪድ-19 ምክንያት የዘንድሮ መርሃግብሮች በዙር አንድ ከተማ ላይ መካሄዳቸው ለክለቦች ከትራንስፖርት ወጪ ጋር በተያያዘ በአንፃራዊነት እፎይታን ይፈጥራል የሚል እምነት አሳድሮ ነበር። ያምሆኖ ከክለቦች የስቴድየም ገቢ መቅረት ጋር ተያይዞ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።
የ2013 ዓ.ም. የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከጀመረ በኋላ ጅማ አባ ጅፋር፣ አዳማ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ከተማ እግር ኳስ ክለቦች ክፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ገጥሟቸዋል። ክለቦቹም ጨዋታ እስከማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከወር በፊት ከባህር ዳር ወደ ድሬዳዋ የተዘዋወረው ውድድሩ በሊጉ ተሳታፊ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና በገንዘብ ችግር ምክንያት ለተጫዋቾቹ ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ ተጫዋቾች ቡድኑን ለቀው እስከመበተን መድረሳቸው ሲነገር ቆይቷል። ዘንድሮ በቴሌቪዥን መስኮት የመተላለፍ ዕድል ያገኘው ፕሪሚየር ሊግ በክለቦችና ተጫዋቾች መካከል በሚፈጠር የደመወዝ ክርክር ውዝግብ የሊጉን በጎ ገጽታ እንዳያጠለሽ በርካቶች ስጋት አድሮባቸዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታችኛው ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች፤ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች እንቅጠር በሚል የዳቦ ስም፤ ወደ ላኛው ሊግ ያሳደጓቸውን ተጫዋቾች ጥለው ሌሎችን ለማስፈረም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያወጡ ይስተዋላል። ይኼም ክለቦችን ለከፍተኛ ዕዳ ሲያጋልጣቸው ማየቱ የተለመደ ነው። በአንጻሩ በክለቡ ወስጥ ታዳጊዎችን መያዝ፣ ለወጣቶች ዕድል መስጠትና የክለቦቻቸውን መዋቅር ማስተካከል ላይ እምብዛም በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍረስ እንዳይዳረጉ ያሰጋል።
አንድ አሠልጣኝ ወደ አንድ ክለብ ሲዘዋወር ተጫዋቾችን ቀድሞ ከነበረበት ክለብ ይዞ የሚጓዝበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል። ይኼም የክለቦችን ካዝና ከማራቆት ባሻገር አሠልጣኝ ከተጫዋች ጋር የሚኖረውን የጥቅም ትስስር የሚያጎለበት እንደሆነ ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች አስታየታቸውን ይሰጣሉ።
የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የ2010 የሂሳብ ሪፖርት ክለቦች ከገቢያቸው የላቀ ወጪ እያናጋቸው እንደመጣ አንድ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ለተጫዋቾች የሚያወጣው የገንዘብ መጠን በአራት ዓመት ልዩነት ውስጥ ከብር 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወደ 30 ነጥብ 244 ሚሊዮን ብር ንሯል። ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና ዓመታዊ በጀቱን መሙላት ዳገት ሆኖበት እንደነበር ይታወሳል።
የገንዘብ ጉዳይ አሳስቦት የማያውቀው ቅዱስ ጊዮርጊስም ቢሆን ባለፉት ጥቂት አመታት ገቢና ወጪው እኩል መራመድ እየተሳነው ኪሱ እየሳሳ ስለመምጣቱ የአደባባይ ወሬ ነበር።
ገቢያቸው ከወጪያቸው በእጅጉ የላቀ በሆነበት የአውሮፓ አገራት ሊጎች ውስጥ አንድ ክለብ ገንዘብ ስላለው ብቻ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል ፍትሃዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀም (financial fair play) መከተል የሚያስችል ጠንካራ ህግ አላቸው። ይህ አሠራር ከእኛ ሀገር ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ ተግባራዊ ቢደረግ ችግሩን ለመቆጣጠር ያስችላል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስም ላይ ተመሳሳይ ህግ በማውጣት ፌዴሬሽኑ አንድ ክለብ ለአንድ ተጫዋች ከ50 ሺ ብር በላይ ወርሃዊ ደመወዝ እንዳይከፍል ለማድረግ ቢጥርም ክለቦች በእጅ አዙር ከፍተኛ ገንዘብ ከመክፈል ወደ ኋላ አለማለታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች በየጊዜው ይወጣሉ። ከድሃ አገርና ህዝብ የሚገኝ ገንዘብ የጀርባ አጥንቱ ለሆነው የአገራችን እግር ኳስ የፋይናንስ ስርዓትን ለመቆጣጠር የሚያስችል በልኩ የተሰፋ ጠንካራ የህግ አንቀፅ ማስቀመጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ቢታመንም ወደ ተግባር ሊለወጥ አለመቻሉ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።
መንግሥት ፊፋን በማያስቆጣ መልኩ ለዚህ ችግር መፍትሔ ካላበጀ እንዲህ በቀላሉ እግር ኳሱን መታደግ የሚቻል ባለመሆኑ መፍትሔው ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚኖርበት ይታመናል። ከዚህ ጎን ለጎን እግር ኳሱን አንቆ የያዘው የወሮበላ ቡድኖች ሰንሰለት እስካልተበጠሰ ድረስ የቱንም ያህል የእግር ኳስ አመራር ቢቀያየር ለውጥ እንደማይመጣ ታምኖበት ለጉዳዩ ሁነኛ መፍትሄ ማበጀት ለነገ የማይባል የቤት ስራ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013