
በእስር ቤት የረሃብ አድማ ላይ የነበረው ሩስያዊው ተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ በወህኒ ቤቱ ሆስፒታል ገብቷል። ባልደረቦቻቸው ግን ደህና ወሬ እንሰማለን የሚል ተስፋ የለንም በማለት በጤናቸውና ስብዕናቸው ላይ ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።
የሩስያ የወህኒ ቤቶች ባለሥልጣናት በሰጡት ትዕዛዝ ናቫልኒን ሆስፒታል አስገብተነዋል ያለው የሀገሪቱ የፌዴራል ወህኒ ቤቶች መምሪያው ባወጣው መግለጫ ነው፡፡
“በአሁኑ ሰዓት ናቫልኒ አጥጋቢ የጤና ሁኔታ ላይ ነው፣ ሃኪሞች በየቀኑ እየተከታተሉት ነው፣ በፈቃዱ የቫይታሚን ህክምና እየተሰጠው ነው” ብለዋል በመግለጫው።
ተቃዋሚ መሪው አሌክሲ ናቫልኒ፣ ከሞስኮ በስተምስራቅ ወደሚገኝ በከባድ ጥበቃ ሥር የሚገኝ ሆስፒታል መግባቱን በሚመለከት ከደጋፊዎቻቸው በኩል ለጊዜው የተሰማ አስተያየት የለም፡፡ ቀደም ብሎ ግን አንድ የናቫልኒ ባልደረባ “ስለጤናው ደህና ወሬ እንሰማለን ብዬ አልጠብቅም፣ ከውስጥም ጥሩ አያያዝ ሊኖር ይችላል ብየም እንደዛው አልጠብቅም “ ብሎ ነበር።
በእስር ቤት ቆይታው የረሃብ አድማ ላይ የቆየው አሌክሲ ናቫልኒ ለልብ ድካም ወይም ኩላሊቱ ከጥቅምውጭ የመሆን የከበደ አደጋ ላይ እንዳለ የሚጠቁም የደም ምርመራ ውጤት ቤተሰቦቹ እና የግል ሃኪሞቹ ይፋ ማድረጋቸውንም የቅርብ ጓደኛው ተናግሯል። ይህንኑ ተከትሎም የናቫልሊ ደጋፊዎች ሀገር አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ የተጠራው በፈረንጆቹ ረቡዕ አፕሪል 27 ሲሆን ቀኑ የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን ከክሬምሊን ቤተ-መንግሥት አጠገብ ዓመታዊ የሀገሪቱ ሁኔታ መግለጫ ንግግራቸውን የሚያደርጉበት ዕለት ጋር የተሳሰረ ነው። በመሆኑም በመዲናዋ ሞስኮ በናቫልኒ ደጋፊዎች እና በፖሊሶች መካከል ከባድ ፍጥጫ እንደማይቀር የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የናቫልኒ ሃኪሞች ይፋ ያደረጉት የደም ምርመራ ውጤት የሚያሳየው በሰውነቱ የፖታሲየም ንጥረ ነገር መጠን እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ እንዳለ ነው። ይህም በማናቸውም ደቂቃ የልብ አመታት ችግር ወይም የኩላሊት እክል ሊከሰትባቸው እንደሚችል ያሳያል፤ በፍጥነት ካልታከሙ በቀናት ጊዜ ውስጥ ህይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ሲሉ ሃኪሞቹ በፊርማቸው ባወጡት ደብዳቤ አሳስበዋል ሲል ጤናቸው ያለበትን ሁኔታ ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ እርሳቸው ላይ የሁለት ዓመት ተኩል እስራት ተፈርዶባቸው ከሞስኮ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ወህኒ ቤት የሚገኘው የአርባ አራት ዓመቱ አሌክሲ ናቫልኒ ህክምና እንዲያገኝ በመጠየቅ የረሃብ አድማውን ከጀመረ ሦስተኛ ሳምንታትን አሳልፏል፡፡ ዓርብ ዕለት ባለሥልጣናቱ ‘በግድ ትበላለህ’ እያሉ እየዛቱብኝ ነውም ብሎ እንደነበር ዘገባው አስነብቧል። ቀደም ብሎም “ከረሜላ ኪሴ ውስጥ እየከተቱ እና ዶሮ እየጠበሱ ሊያስጎመዡኝ እየሞከሩ ነው” ብሎ መናገሩን ሮይተርስ አስታውሷል፡፡
ተቃዋሚ መሪው ከባድ የወገብ ህመም እና የእግር መደንዘዝ እንዳለበት ለሳምንታት ሲናገር ቆይቷል። ጠበቆቻቸው እንዳሉት ከባድ ሳልና እራስ ማዞርም አለበት፥ አሌክሲ ናቫልኒ የህመሙ ምክንያት ባለፈው ዓመት ነሃሴ ወር ላይ ከደረሰበት የመመርዝ ጥቃት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እሳቸው እና ምዕራባውያን መንግሥታት የመርዝ ጥቃቱ ተጠያቂ የሩሲያ መንግሥት እንደሆነም ተናግረው ነበር። የክሬምሊን ቤተ-መንግሥት በበኩሉ እጃችን የለበትም፣ ስለመመረዛቸው ማረጋገጫም የለም በማለት ምርመራ አናካሂድም ማለቱን አስታውሷል ዘገባው።
የሩስያ መንግሥት አሌክሲ ናቫልኒ ያሉበት የእስር ቤት ሁኔታ መልካም እንደሆነ እንዲያሳዩ እና ናቫልኒ ታምሜያለሁ የሚለው ከሌሎቹ የተለየ አያያዝ እንዲሰጠው ነው የሚሉ ሪፖርቶች የሚያወጡ የመንግሥት ዜና ማስራጫዎችን ማሰማራቱ ተገልጿል።
በዘገባው ስማቸው በውል ያልተገለፁት የመንግሥት የዜና ማስራጫዎች ይህንኑ ተግባር ሽፋን ሰጥተው እንዲሰሩም ትዕዛዝ መሰጠቱንና የእስር ቤቱ አያያዝ እንደማንኛውም ዜጋ ለናቫልኒ ስብዕናቸውን ባከበረ መልኩ እየተጠበቀ መሆኑን ዘገባው አክሎ አስነብቧል፡፡
ናቫልኒ የእስር ቤቱ አያያዝ በጣም ከባድና በውስጡም ያለው አያያዝ በተለይ በእርሳቸው ላይ የከፋ እንደሆነ ቀድመው ፍንጭ ሰጥተው እንደነበር አስታውሷል፡፡
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013