አንድን አገርና ሕዝብ የሚፈታተኑ ችግሮች ጎልተው የሚወጡትና ተግዳሮት የሚሆኑት በለውጥ ወቅት ስለመሆኑ ብዙ የማህበረሰብ ሳይንስ ተመራማሪዎች የሚጋሩት እውነታ ነው። አንድም ለውጡ ይዞት የሚመጣው ሀሳብ በራሱ ለመለወጥ የተዘጋጀ ወይም በሂደት የተለወጠ ኃይል የመፈለጉ እውነታ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ለውጡ ይዞት የመጣው አስተሳሰብ ከቀደመው አስተሳሰብ ጋር የሚኖረው ተቃርኖ ነው።
ለውጥ ይዞት የሚመጣው የለውጥ አስተሳሰብ ብዙውን ጊዜ የግብታዊነት ባህሪ ቢላበስም በተጨባጭ ግን ለውጡ በራሱ ቀድመው የነበሩ፣ በአሸናፊነት ገዝፈው የወጡ አስተሳሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ የፈጠሩት ተቃርኖ በራሳቸው መቀጠል የሚያስችላቸውን ዐቅም እያጡ ለመምጣታቸው ማሳያ ጭምር ነው።
የለወጥ አስተሳሰቦች በተጨባጭ ከግብታዊነት ይልቅ በሂደት በማህበረሰብ ውስጥ ተጸንሰው የመወለጃ ጊዜያቸውን በማህበረሰብ ውስጥ ሲጠብቁ ይቆዩና በተሻለ መልኩ ህያውና የሚጨበጥ ማህበራዊ እውነታ ሆነው ለመወለድ ኃላፊነት የሚሰማው ባለሙያ አዋላጅ የሚፈልጉ ናቸው።
የለውጥ አስተሳሰቦችን በማህበረሰብ ውስጥ በማዋለድ ሂደት ውስጥም የለውጡ ኃይል ከፍ ያለ የመሪነት ኃላፊነት ቢኖረውም መላው ሕዝብ የለውጡን የምጥ ወቅት በማሳጠር ሂደት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከለውጥ ኃይሉ የሚተናነስ አይደለም። ለዚህ ደግሞ መላው ሕዝብ ለውጡን ከዕለት ተዕለት የሕይወት ተስፋዎቹና ከመሆን መሻቶቹ ጋር አስተሳስሮ ለውጡ የራሱ ተስፋ ምጥ መሆኑን በአግባቡ መረዳት አለበት።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ተነስተን ሀገራዊ አሁናዊ እውነታዎችን መገምገም ከቻልን ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ነባራዊ እውነታዎች የሚጠበቁ፤ ከመጠበቃቸውን በላይ ከለውጥ ኃይሉም ሆነ ከመላው ሕዝብ ከፍያለ ቁርጠኝነትንና ስትራቴጂክ አጋርነትን የሚጠይቁ ናቸው።
በተለይም ባለፉት 60 ዓመታት ከመጣንበት የሴራ ፖለቲካ አዙሪት ሊያወጣንና የአዲስ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ባህል ባለቤት ሊያደርገን ከሚያስችለው ፍጥረታዊ /አስተሳሰባዊ / አቅሙ አንጻር መጀመሪያ ለውጡን እንደ ሕዝብ፤ ነገዎቻችን እንዲሆኑ ከምንፈልገው መሻታችን አንጻር ል ናየው፣ ልንመረምረው እና ል ንቀበለው ይገባል።
ይህን ለማድረግ ደግሞ ቀደም ባሉት ዘመናት የመጣንባቸውን የተቃርኖ መንገዶችና መንገዶቹ እንደ ሕዝብና እንደ አገር ያስከፈሉንን ከፍ ያለ ዋጋ በአግባቡ ማስተዋል ይገባል። የመጣንባቸው መንገዶች የባላንጣነት አስተሳሰብ መፈንጫ እንደነበሩ፤ እንደአገር ለእርቅ ስፍራ በሌላቸው የተቃርኖ አስተሳሰቦች ተይዘን አቅምና ጉልበታችንን ሁሉ ለዚሁ ገብረን ያተረፍነው ምንም ነገር እንዳልነበር ያመለክቱናል።
አንዱ ሕዝባዊ ሌላው ጸረ ሕዝብ — አንዱ አብዮተኛ ሌላው ጸረ አብዮተኛ- አንዱ የሰላም ሐዋርያ ሌላው ጸረ ሰላም — አንዱ ልማታዊ ሌላው ጸረ ልማት ወዘተ በሚል ለሕዝባችን አንዳች ነገር ጠብ ሊያደርግ ባልቻለ፤ ከዚህ ይልቅ ለአምባ ገነኖች እና ላደቡ ሴረኞች አቅምና ጡንቻ በሆነ መከፋፈል ውስጥ አልፈናል።
በብዙ መፈክሮች የታጀበውና የተሞላው ይህ የቀደመው መንገዳችን በድህነታችን ላይ ድህነት ፤ በቀደሙት ጥቁር ታሪኮቻችን ላይ ተጨማሪ ጥቁር ታሪክ፤ ከዚህም አልፎ ብሔራዊ አንድነታችንና ይህን አስጠብቀው የቆዩ ማህበራዊ እሴቶቻችን ከማኮሰስ ያለፈ የፈጠረልን ነገር የለም።
የቀደሙት የለውጥ ታሪኮች ትክክለኛ አዋላጅ አጥተው፤ የለውጥ ሙሉ ቁመና ስብእና በሌላቸው ሴረኛ አዋላጆች መክነው ቀርተዋል። የሕዝባችን የለውጥ ፈላጊነት፣ ከዚያም በላይ ለለውጥ በየዘመኑ የከፈለው ውድ ዋጋም ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። በየዘመኑ ስለለውጥ የከፈለው ዋጋ ለሚንሰላሰሉ ማህበረሰባዊ ለውጦች አቅም ከመሆን ይልቅ ለውጥን በራሱ በተስፋ እንዳይመለከት ጥላ ሆነውበትም ቆይተዋል።
የለውጥ ጉዳይ የአንድ ማህበረሰብ እድገት መሠረት ነው። ከዚህ የተነሳም ይህ ትውልድ በራሱ የለውጥ ታሪክ ውስጥ እንዳለ የአደባባይ ምስጢር ነው። ትውልዱ እንደ ትውልድ ለራሱም ከዚያም በላይ መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ተስፋና ራዕይ በሰነቀ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
ይህ የለውጥ ምዕራፍ ከሌሎቹ የለውጥ ዘመናት የሚለይበት የራሱ እውነታዎች ያሉት ነው። የመጀመሪያው ለውጡ እንደቀደሙት ለውጦች ያለውን ሁሉ በማጥፋት እንደ አዲስ መጀመር ላይ የተመስረተ አይደለም፤ ከዚያም ባለፈ የለውጡ አስተሳሰብ የማህበረሰቡን ከፍ ያሉ እሴቶች መሠረት ያደረገ ነው። ከዚህም በላይ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት፣ ይቅርታ፣ ፍቅር እና መደመርን መሠረት ያደረገ ነው።
ይህንን ለውጥ ሕያው አገራዊ ታሪክ አድርጎ ለማዋለድ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከፊታችን ያለው ምርጫ ወሳኝ አቅም እንደሆነ ይታመናል። አንድም ባለፉት 60 ዓመታት የተደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች በሙሉ በሚባል መልኩ የሕዝባዊ መንግሥት ምስረታን የሚጠይቁ ናቸው። ይህ ጥያቄ ሕዝብ መንግሥት የመመስረት መብቱን ይጠበቅ የሚል ነውና ይህንኑ ጥያቄ የሚመልስ ነው።
የዚህ ምርጫ ስኬት የሕዝባዊ መንግሥት ምስረታ ጥያቄ አንግበው ከፍ ባለ ድምጽ እየጮሁ ሰማዕት የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትንሳኤ የሚበሰርበት፣ በርግጥም ሞታቸው በትውልዶች መካከል ፍሬ አፍርቶ የአገራዊ ትንሳኤ መሠረት የሚሆንበት ወሳኝ ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን የሚያሳይ ነው።
ከዚህም በላይ የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄ የአስተሳሰብ መሠረት የሆነውን የጠንካራ መንግሥት ምስረታ ማብሰሪያ፣ ከዚህ የሚመነጨውን አገራዊ ክብርና ልዕልና የምንጎናጸፍበት፤ ለጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስኬት አልፋና ኦሜጋ የሆነ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ይህ ታሪካዊ ምዕራፍ ይዞት የመጣውን አገራዊ ተስፋ እውን ለማድረግ መላው ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ለአገራዊ ተጠቃሚነት በቁርጠኝነት ሊሰለፍ ይገባል። የለውጡን ተስፋ በማዋለድ ሂደት የሚጠበቅበትን የማዋለድ ኃላፊነት ራሱንና መጪውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአግባቡ ሊወጣ ይገባል።
ብዙ ትውልዶችን በየዘመኑ ከፍ ያለ ዋጋ ያስከፈለውን ይህን የለውጥ ምጥ በአግባቡ በማዋለድ ፣ ህያውና ተጨባጭ ሀገራዊ ታሪክ እውን ለማድረግ ትውልዱ በሴረኞች የተፈጠረውንና ዕለት ተዕለት እየጦዘ ለለውጡ ተግዳሮት እየሆነ ካለው መከፋፈል ወጥቶ በአንድነት እና በመደማመጥ ይህንን ታሪካዊ ምዕራፍ በስኬት መሻገር ይጠበቅበታል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013