አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን «የኢሳት ቀን» ብሎ የሰየመውን የምስጋናና ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ቅዳሜ የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ ትናንት በጣይቱ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫውን የመሩት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እንደገለጹት፣ ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ የሚደረገው ዝግጅት ኢሳት ህዝባዊ መሰረቱን ለማስፋትና ራሱን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም ከሀገር ውስጥ እድምተኞቹ ጋር ፊት ለፊት የሚገናኝበት ነው፡፡ በዝግጅቱ ላይ ታዋቂና አንጋፋ የሙዚቃና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ህዝቡ ለኢሳት አጋርነቱን የሚያሳይበትና በገቢም እንዲጠናከር ድጋፍ የሚያደርግበት ይሆናል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ በሚከናወነው በዚህ ዝግጅት ዋዜማ የካቲት 8 ቀን 2011 ዓ.ም በዝግጅቱ ለመታደም ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ የኢሳት ጋዜጠኞች፣ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችና ሌሎች የኢሳት ባልደረቦች አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡ ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ 3 ሰዓትም በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ የሃይማኖት መሪዎች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ፖለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጋዜጠኞች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ይደረግላቸዋል፡፡ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡት ጋዜጠኞችም ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር መገናኛ ብዙኃን ጋር ቆይታ እንደሚያደርጉ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡ አቶ ውብሸት እንደተናገሩት ሲሳይ አጌና ፣ መሳይ መኮንን እና አበበ ገላውን ጨምሮ አስር ጋዜጠኞች ለዝግጅቱ ሀገር ቤት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
«በኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውን ልሳን የሆነው የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አሁንም እንደ ወትሮ ተጠናክሮ ይቀጥላል» በሚል መሪ መልዕክት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳረጊያ ላይ «ኢሳትን ለመደገፍና መስዋዕትነት የከፈሉትን የህዝብ ልጆች ለማመስገን በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተገኙ» የሚል ጥሪ በዝግጅቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ተላልፏል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
የትናየት ፈሩ