የሱፍ እንድሪስ
የሀገር መሪ በጦር ሜዳ ሲዋጋ ሕይወቱ አለፈ ቢባል የድሮ ታሪክ ሊመስል ይችላል። ሰሞኑን የዓለም መነጋገሪያ የነበረው በአፍሪካዊቷ ሀገር ቻድ የተሰማው ዜና የ69 ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ወደ ጦር ግንባር ዘልቀው ወታደሮችን በጦር ግንባር ውጊያ እየመሩ ባሉበት ወቅት ቆስለው ለህልፈት መዳረጋቸው ተነግሯል።
ፕሬዘዳንት ኢድሪስ ዲቤ የሰሜን መካከለኛው አፍሪካዊት ሃገርን ለሰላሳ ዓመታት ያህል መርተዋል። በስልጣን ዘመናቸውም የጦር ሰፈሮችን እና የመንግሥት ወታደሮች ከአማፂያን ጋር የሚፋለሙበትን አካባቢ በተደጋጋሚ በመጎብኘት የሚታወቁ መሪ እንደነበሩም ተነግሮላቸዋል። ሟቹ ፕሬዚዳንት ወደስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ሀገራቸውን ወታደር በመሆን ስለማገልገላቸውም እንዲሁ ይነገራል።
አገልግሎታቸውን በጦር ሜዳ ጀምረው በጦር ሜዳ ጨረሱት በማለት ብዙ የሀገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች እያስታወሷቸው ስለመሆኑም በተለያዩ ሚዲያዎች እየተዘገበ ነው። አፍሪካኒውስ የፕሬዚዳንቱን ሞት በተመለከተ ይዞት በወጣው ሐተታ ፕሬዚዳንት ዲቤ በነበራቸው የወታደራዊ ችሎታ የማርሽያል ማዕረግን በቅርቡ አግኝተዋል።
የቻድ ጦር ቃል አቀባይ የሆኑት እዛም በርማንዶን የፕሬዚዳንቱን ሞት ተከትሎ በሰጡት መግለጫ “የቻድ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት፣ የሀገሪቱ መንግሥት መሪ እና የጦር ጠቅላይ አዛዥ ኢድሪስ ዲቤ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በመጠበቅ ላይ በነበሩበት የጦር ሜዳ የመጨረሻ እስትንፋሳቸውን ጥለው ማለፋቸውን አልጀዚራ ዘግቧል።
የሀገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ የፕሬዚዳንቱን ሞት በተመለከተ ግራ የተጋቡ ወይም የተሰጠውን ምክንያት አልቀበል ያሉ ሰዎችም አሉ።
እ.ኤ.አ 2018 ላይ እርሳቸው እንዲህ ብለው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው እንደነበር በበርካታ መገናኛ ብዙሃን እየተወሳ ነው። “የሀገር መሪ የጦር መሣሪያ አንስቶ ወደ ጦር ግንባር ሲሄድ አይታችሁ ታውቃላችሁ? እኔ ያደረኩትስ ጀግና ስለሆንኩ ይመስላችኋል? ወይስ ትጉህ ስለሆንኩ? አይደለም፤ እኔ ይህን ያደረኩት ሀገሬን ስለምወድ፣ ሀገሬን ከሚያተራምስ እና ከሚያሠቃይ ነገር ይልቅ በጦር ሜዳ መሞት ስለምፈልግ ነው።
በስልጣን ዘመናቸውም ከሰሜን በኩል የሚመጡባቸውን የሊቢያ አክራሪ ሃይሎች እንዲሁም ከሱዳን ድንበር አካባቢ ይነሳ የነበረውን የሽብር ተግባር ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር በመሆን በጋራ ሲሰሩ የቆዩ መሆናቸውም እየተዘገበ ነው።
እርሳቸው በአማፂዎች ላይ እንደዘመቱት ሁሉ አማፂዎችም እርሳቸውን ለማጥቃት ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንዳልነበር የሚጠቁሙ ዘገባዎችም ብዙ ናቸው። ከዚህ ቀደም አማፂዎች ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን ለማውረድ ሞክረው እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል። እነዚህ አማፅያን እኤአ 2006 እና 2008 እንዲሁም በ2019 በሃገሪቱ ዋና ከተማ አቅራቢያ ደርሰው ነበር። ይሁንና የመንግሥት ወታደሮች ባደረጉት ፍልሚያ ሊያፈገፍጉ ችለዋል ይላል ዘገባው።
ከእስከዛሬው ከባድ በቅርቡ የተከሰተው ደግሞ በዚህ ወር የተካሄደውን የሃገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ተከትሎ ነበር። በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍልም ከምርጫው በፊት ከፍተኛ ውጥረት እንደነበረ ቅድመ ምርጫ ዘገባዎች ያሳያሉ። ከሳምንታት በፊትም በመንግሥት ሃይሎች ተፈጽሟል የተባለውን ወከባ ተከትሎ ሂውማን ራይትስዎች ፕሬዚዳንት ዲቤ የጥቃት አሻራ አስቀምጠዋል ሲል ወቀሳውን አቅርቦ እንደነበርም ተዘግቧል።
ህልፈታቸውን ተከትሎ ደግሞ ስለእርሳቸው የሚያወሱ እና የእርሳቸው ሚና በተለይ አማፅያንን እና አሸባሪዎችን በመዋጋት ረገድ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው እየተነገረ ነው።
የአፍሪካ ህብረት ባወጣው የሐዘን መግለጫ ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ህብረት ሰላም እና ደህንነት የማስፈን አጀንዳ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው መሆኑን ሲጠቅስ የአፍሪካ ህብረት ሲያደርጋቸው የነበሩትን ሰላማዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ እንዲኖር በማድረግ ረገድ የፕሬዚዳንቱ ድጋፍ የላቀ ነበር ብሏል። በሳህል በረሃ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌም ተጠቅሷል።
ህብረቱ ከቻድ ሕዝብና መንግሥት ጎን በመሆን የዚህን የአፍሪካ የደህንነት እና የሰላም ጀግና ሃዘንን በጋራ እንደሚወጣ አረጋግጧል።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በትዊተር ገጻቸው እንዳሰፈሩት ደግሞ ሕዝቡን እና ሀገሩን በመጠበቅ ላይ የተሰዋው ኢድሪስ ዲቤ እውነተኛ ፓን አፍሪካዊ እና ሀገር ወዳድ መሪ ነበር ብለዋል።
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐመዱ ቡህሪም በተመሳሳይ በትዊተር ገጻቸው ላይ በፕሬዚዳንቱ ድንገተኛ ሞት ድንጋጤ እንደተሰማቸው ገልጸው በቦኮሃራም ላይ ይወሰድ በነበረው የጦር ዘመቻ የቀጠናውን ሃይል በማስተባበር የሟቹ ፕሬዚዳንት ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።
“የሀገሩን ሉዓላዊነት በማስከበር ላይ ሕይወቱ ያለፈው ፕሬዚዳንት ለናይጄሪያ የቅርብ ወዳጅ ነበር። በቀጠናው ላይ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የደቀነውን የገዳዩን እና አሸባሪ ቡድኑን ቦኮሃራምን ለመደምሰስ ያሳዩን ትብብር ከፍተኛ ነበርም” ብለዋል።
በተጨማሪም “የፕሬዚዳንቱ ሞት በእርግጠኝነት ቦኮሃራም ላይ እና እስላማዊ መንግሥት በምዕራብ አፍሪካ በሚል ስም የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ላይ እየተወሰደ ባለው የጋራ እርምጃ ላይ ክፍተት ፈጥሮ ያልፋል። ለዚህም አሸባሪዎችን ለማጥፋት የበለጠ ትብብራችንን አሁን ማጠናከር ይኖርብናል” በማለት የፕሬዚዳንቱ ሞት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013