– ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ የማጣራቱን ሂደት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፣ ከዓመታት በፊት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች እስከአሁን ያሉበትን ሁኔታና አድራሻቸውን ማወቅ ባለመቻላቸው መንግሥት ቁርጥ ያለ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡ ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ የማጣራቱን ሂደት በትዕግሥት መጠበቅ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
በኦሮሚያና አማራ ብሄራዊ ክልሎች ነዋሪ የሆኑ የጠፉ ሰዎች ቤተሰቦች ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣እስካሁን ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ አድራሻቸው ባለማወቃቸው መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት አርሲ ዞን ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ የሆኑት አቶ ዩሱፍ ኡስማን እንደገለጹት፣ ወንድማቸው አቶ ነዲ ገመዳ በ1984 ዓ.ም በታጣቂዎች ተይዞ እስከ አሁን ድረስ የት እንዳለ አያውቁም፡፡እርሳቸው እንደሚሉት ወንድማቸው ከሀረር አካባቢ ከተያዘ በኋላ በቢሾፍቱ አየር ሀይል ግቢ ውስጥ ታስሮ እንደነበር በወሬ ከመስማት ውጭ የት እንደታሰረ እንኳን አያውቁም፡፡
መንግሥት የወንድማቸውን አድራሻ እንዲያሳውቃቸው ከአንድም አራት ግዜ ለሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም እስከ አሁን ምላሽ አላገኘሁም የሚሉት አቶ ዩሱፍ፣ ወንድማቸው በሕይወት ካለ እንዲያገናኛቸው ሞተውም ከሆነ ቁርጡን እንዲያሳውቃቸው መንግሥትን ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በዚሁ ክልል ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ሀሮማያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዲ ቃሲም በበኩላቸው፣ የአጎታቸው ልጅ ሞሀመድ ሀሶ በ1987 ዓ.ም ከሃሮማያ ከተማ በመንግሥት ታጣቂዎች ተይዘው እስከ አሁን የት እንዳሉ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት አቶ ሙሀመድ ሀሶ የት እንደታሰሩ እንዲጠቁማቸውም ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላሏቸው የመንግሥት
አካላት ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውንና የአቶ ሙሀመድ እናትም በልጃቸው ጉዳይ ሲብሰከሰኩ ኖረው መሞታቸውን አስረድተዋል፡፡ አቶ አብዲ መንግሥት ታሥረው የተሰወሩ ሰዎችን በተመለከተ በስቃይ ውስጥ ላለነው ቤተሰቦቻቸው አንድ ነገር ማለት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሌላው ተወላጅነታቸው በአማራ ብሔራዊ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የሆኑት አቶ ዳኛቸው አስናቀ ደግሞ ወንድማቸው የሆኑት መምህር ጌትነት አስናቀ በ1986 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ለም ሆቴል አካባቢ ተይዘው እስከ አሁን ያሉበትን አላውቅም ብለዋል፡፡
መምህር ጌትነት በአዲስ አበባ ምስራቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኬሜስትሪ መምህርነት ይሠሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ ከታሰሩ ግዜ ጀምሮ አድራሻቸውን ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት አሁን ካለበት ችግር አንጻር ለጉዳዩ የሚፈለገውን ትኩረት አልሰጠም ያሉት አቶ ዳኛቸው፣ መረጃዎችን አጠናቅሮ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደሚሰጣቸው ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ወንድማቸው ተገድለውም ከሆነ፣ በህይወትም ካሉ ለማወቅ እንደ ጓጉና መንግሥት ቁርጥ ያለ ነገር ቢያሳውቃቸው እንደሚፈልጉ አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ አሽማዊ ሰይፉ፣ ቁጥራቸው አሥራ ሦሥት የሚደርስ ግለሰቦች ቤተሰቦቻቸው በመንግሥት ታጣቂዎች ታስረው የት እንዳሉ እንደማያውቁና ቢሮው ያሉበትን ቦታ በማፈላለግ እንዲያግዛቸው ማመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚያቀርቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንዳሉ አቶ አሽማዊ ጠቅሰው፣ከሁሉም ዞኖች መሰል ጥያቄ ያላቸው ሰዎች መረጃ ተጣርቶ እንዲመጣ መልዕክት መተላለፉን አስረድተዋል፡፡ መረጃው በሚገባ ከተጠናቀረ በኋላ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን ግለሰቦቹ የሚያቀርቡትን ጥያቄ የመመለስ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የክልሉን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የማስጠበቅ ግዴታ ተጥሎብናል ያሉት አቶ አሽማዊ፣ ጉዳዩ ውስብስብ በመሆኑ የማጣራቱን ሂደት በትዕግሥት መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ፍርዴ ቸሩ በበኩላቸው ፣ካለፉት አራትና አምስት ወራት ወዲህ አንዳንድ የክልሉ ተወላጆች ወደ ቢሯቸው እየመጡ ታስረው የጠፉባቸው ሰዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ቢሮአቸው መጥተው አምስት ሰዎች ማመልከታቸውን አስታውቀዋል ፡፡
አንዳንዶችም በቀጥታ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እየሄዱ እንዳመለከቱ ጠቅሰው፣ ከፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቢሮ ጋር በመነጋገር የማፈላለጉ ሥራ እየተሞከረ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ በቅርቡ የ2011 በጀት ዓመት የአምስት ወራት የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠር የሀገሪቱ ዜጎች የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ እና ተቋሙም ከአመልካቾች የሚያገኘውን መረጃ መነሻ አድርጎ የማረጋገጥ ሥራ ቢሠራም ግለሰቦቹ ሲያዙ የፍርድ ቤት ትዕዛዝም ሆነ ያዢው ማን እንደሆነ በውል ባለመታወቁ ሥራውን በሚፈለገው ደረጃ ማከናወን ማስቸገሩን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2011
ኢያሱ መሰለ