ጌትነት ምህረቴ
ምርጫ ዜጎች የዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ከሚገልፁባቸው መንገዶች አንዱ ነው። ህዝብ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጥበትና ለዚህም ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያደርግበት አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሂደት አካል ነው።
ሂደቱ የሚከናወነውም ሁለትና ከዛ በላይ በሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ በፈጠረው እኩል መድረክ ተወዳድረው አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለህዝቡ በማቅረብ የመንግሥት ሥልጣን ውክልና የሚያገኙበት መንገድ ነው።ለዚህም ነው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው የሚባለው።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ህዝቡ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዲሞክራሲያዊ መብቱንና ጥቅሙን የሚያስከብርለትን ፓርቲ በነጻነት መምረጥ እንደሚኖርበት ያሳሳቡት።መንግሥት መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ያለመሸማቀቅ በነጻነት የሚመርጡበትን፣ፓርቲዎች በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳ የሚያካሄዱበትና ምርጫ ቦርድ ስራውን በተገቢው መልኩ የሚያከናውንበትን ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ምርጫ እንዲካሄድ በጸጥታ አካላት ተግባራዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግሯል።
በተለይ የምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የምርጫ ቁሳቁሶች በወቅቱ የሚፈለጉበት የምርጫ ጣቢያና ክልል እንዲደርሱ አስፈላጊው እጀባና ጥበቃ እየተደረገ መሆኑን፤ የዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ከፌዴራል ፖሊስ ፤ከጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ከብሄራዊ ደህንነት አገልግሎትና ከመከላከያ ሚኒስቴር የተወጣጡ አመራሮች ያሉበት አገር አቀፍ የምርጫ ኮሚቴ ተቋቁሞ የጸጥታ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ እየተሰሩ እንደሚገኙና አበረታች ውጤቶችም እየታዩ መሆኑን መንግሥት እየተናገረ ይገኛል።
መቼም ዜጎች በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲጎለብት፣ አገር እንዲለማ፣ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ቀናኢ ፍላጎት አላቸው።ይህ የሚሳካው ደግሞ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ በተመረጠው ፓርቲ ነው።
ስለዚህ የዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብቶች መካከል አንዱና ቀዳሚው በሆነው ምርጫ ለመሳተፍም ዜጎች የምርጫ ካርድ መውሰድ አለባቸው።እናም ዜጎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክር ወቅት የሚያቀርቧቸውን የፖሊሲ አማራጮች በቅጡ በማጤን ለመምረጥ ከወዲሁ የምርጫ ካርድ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።በዚህም ዜጎች ኢትዮጵያን በንጹህ እጁና በታታሪነትየሚያገለግል፣የሚወድና አንድነቷን የሚያስጠብቅ ፓርቲ የሚመረጡበትን መብት ያጎናጽፋቸዋል።
ስለዚህ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ሁሉም ዜጎች በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ መስራት አለባቸው ሲባል ዜጎች ዲሞክራሲያዊ በሆነው ምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ ካርድ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ማለትም ጭምር ነው።ፓርቲዎች ደግሞ በህዝብ ሊያስመርጣቸው የሚችለው የምርጫ ቅስቀሳቸውን ፖሊሲዎቻቸው ላይ ማተኮር ሲኖርባቸው ነው፤ እነዚህን ሁለቱን አንኳር ጉዳዮች ማድረግ ሲቻል በምርጫው ያሸነፈው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያም አሸናፊ ትሆናለች።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በምርጫው የተሸነፈ ፓርቲ ድል ለቀናው ፓርቲ መልካም ጊዜ ተመኝቶ እሱ ደግሞ ለመጪው ምርጫ ራሱን ይበልጥ የሚያዘጋጅበት ሲሆን ነው።እንዲሁም አሸናፊው ፓርቲ ደግሞ ሥልጣኑን ተረክቦ በህዝባዊ መንፈስ አገር የምትበለጽግበትን ትልም ተልሞ ያን የሚያስፈጸም ይሆናል።ይህንን ማድረግ ሲቻል በአገራችን ታሪክ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደረግን ይባላል።ይህ ደግሞ ለዲሞክራሲው ስርዓት መጎልበት መልካም ዕድል ይፈጥራል፤ለመድበለ ፖለቲካ ስርዓት መዳበር መልካም መደላድል ያመቻቻል።በውጤቱም አገርም አሸናፊ ትሆናለች።
ከዚህ አኳያ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን 6ኛ አገራዊ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣በህዝብ ታአማኒ እና ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው።ይህም ምርጫው ህዝብ ፍትሀዊና ነፃ በሆነ መልኩ ተወካዮቹን የሚመርጥበት ሁኔታ ይፈጥራል።እንዲሁም ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ቀዳሚው ሥራ የመንግሥት ቢሆንም በምርጫው የሚፎካከሩ ፓርቲዎችም የራሳቸው የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ከምርጫው ሂደት ጀምሮ እስከ ምርጫ ውጤት ድረስ ሊፈጠሩ የሚችሉ ውዝግቦችን በሰከነ መንገድ መፍታት አለባቸው።ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ ካርድ እንዲወስድ መቀስቀስ ይኖርባቸዋል።በመጨረሻም ድልም ሆነ ሽንፈትን በፀጋ የሚቀበሉበት መሆን ይኖርባቸዋል።ከምርጫ በኋላ ዘላቂ እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ጉዳይም ሌላው ተግባር ነው።ይህንኑ ለማረጋገጥም ከወዲሁ ራስን ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጅት ማድረግ ይገባል።ለዚህም ነው ዛሬ በመላው ዓለም የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተወዳጅና ተመራጭ የሆነው ።
በኢትዮጵያ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል። በዲሞክራሲያዊ ስርዓት የአንድ አገር ህዝብ ይመሩኛል የሚላቸውን እንደራሴዎች መምረጥ መቻሉ አንዱ የዲሞክራሲ ዋና መገለጫ ነው።ምክንያቱም ዲሞክራሲ የሚጎለብተውና የሚዳብረው ዲሞክራሲዊ በሆነ መልኩ ህዝብ መሪውን ሲመርጥ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን አምስት ጊዜ አገር አቀፍ ምርጫዎች ተካሄደዋል። ሆኖም አምስቱም ምርጫ የህዝብ ታአማኒነት የሌላቸው፣ ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑና ህዝብ ተሳትፎ የተቀዛቀዘባቸው በተለይ ደግሞ በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ምርጫ ተከትሎ ሰላምና መረጋጋት የደፈረሰበት ነበር።
በመጪው ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ እስካሁን ከተደረጉት ምርጫዎች የተለየና ምርጫው ሰላማዊ፥ ፍትሀዊና ነፃ ምርጫ ሆኖ እንዲጠናቀቅም መንግሥት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት በተግባርም እየታየ ነው።
ይህም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የሚያስችል ነው።በተለይ በአንድ አገር የዲሞክራሲ ስርዓት መስፈን ህዝቦች ይመራናል የሚሉትንና የፈለጉትን ፓርቲ ነፃ ሆነው እንዲመርጡ ዋስትና ይሰጣል።ህዝቦች የዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የፈለጉትን ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አነፃፅረውና መዝነው አገር ያስተዳድራል የሚሉትን ይመርጣሉ። ጥቅማችንን ያስከብርልናል ብለው ላመኑት ፓርቲ ድምፃቸውን ይሰጣሉ።
ምርጫ ቦርድም ሆነ መንግሥት ምርጫው ነፃ፣ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ተግባራዊ ሥራ ከጀመሩ ውለው አድረዋል።ስለሆነም ከምርጫው ዕለትም ሆነ በኋላም አገር ሰላምና የተረጋጋች እንድትሆን ፤ ሰላማዊ ፍትሃዊ፥ ነፃና ዲሞክራሲያዊና በህዝብ ታማኒነት ያለው እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ማለትም ህዝቡ፥የምርጫ ቦርድ፥ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
በቀጣይ ወር የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ህዝቡ ለእሱም ሆነ ለአገሪቷ ተስፋ እና ለውጥ ያመጣል የሚሉትን ተወካይ ወይም ፓርቲ የሚመርጡበት ስርዓት ለመጠቀም ዜጎች በወቅቱና በምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጭነት ካርድ መውሰድ ይኖርባቸዋል።
በተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሂደት ችግሮች እንኳን ቢፈጠሩ በሰከነና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመፍታት ባህልን ማዳበር አለባቸው።ከዚያም ለሀገሪቱ ይጠቅማል ብለው የሚያቀርቡትን አማራጭ ፓሊሲ ለህዝብ ሳቢ በሆነ መንገድ ከማስተዋወቅ ባለፈ ወደ ትክክለኛ የዲሞክራሲ ጎዳና ለማምራትም ዝግጁ መሆ ን ይኖርባቸዋል።
እናም በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ፍትሀዊና ነጻ እንዲሆን መራጩ ህዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና የጸጥታ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013