ከባለፉት ሦስት ዓመታት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ጥቅማቸው የተነካባቸው ሃይላት በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር ሴራቸው በህዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖርና ሀገር እንዳይረጋጋ ሲሰሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክንያት ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
መንግሥት ከብዙ ጊዜ ማባበልና ትዕግስት በኋላ የህግ ማስከበር ርምጃ በመውሰድ የሴረኞችን መረብ መበጣጠስ፣ አደጋዎችን የመቀነስ ሥራ ሠርቷል።ይሁንና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚል አቋም ይዘው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሱ ኃይሎች እዚያና እዚህ አዳፍነው ያስቀመጡት እሳት ድንገት እየተነሳ ንጹሃንን ሲለበልብ ይታያል።
ከሰሞኑ በአጣዬና በጭልጋ የተመለከትነውም ለዚህ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ከአንድ ወር ገደማ በፊት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ ተከስቶ በነበረ አለመረጋጋት ከ300 መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቦ ነበር። ሰሞኑን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በአማራ ክልል አጣዬ እና አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙትን ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ አንፆኪያ፣ መኮይና ሸዋሮቢት በተባሉ ስፍራዎች ከባድ ግጭት ተቀስቅሶ የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲቀጥፍ የብዙዎች ቤት ንብረታቸው በእሳት ወድሞባቸዋል፤ በርካቶችም ቀያቸውን ለቀው ተሰደዋል።
በእነዚህ በተከታታይ እየተፈፀሙ ያሉ ሁከት አዘል ጥቃቶች እና ግጭቶች ምክንያት ቁጥሩ የበዛ ሰው ሕይወት ከመጥፋቱ በተጨማሪ ዜጎች በነፃነት ማህበራዊ ኑሯቸውን መምራት ተስኗቸዋል።
መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም አረጋግጦ ወደ ብልጽግና ጉዞው እንዳይንደረደርና መጪው ምርጫ እንዳይከናወን የሚፈልጉ ጸረ ሰላም ሃይሎች ዛሬም ለንጹሃን ሞትና ለህዝቦች መፈናቀል ምክንያት እየሆኑ ነው።ስለሆነም የዚህን አገር የማፍረስ ዓላማ ያነገበ ሴራ በመገንዘብና የጸረ ሰላም ሃይሎችን ደባ ተገንዝቦ እያንዳንዱ ሰላም ወዳድ ዜጋ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ፤ ከተፈጠሩም እንዳይባባሱ በማድረግ የራሱንና የወገኑን ሰላምና ደህንነት ሊታደግ ይገባል።
መንግሥት እንደመንግሥት ህዝብን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል።በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመራሮችና የጸጥታ ሃይሎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም መረሳት የለበትም።ሁሉንም ዜጋ አንድ አድርጎ ከመመልከትና ችግሮች እንዳይባባሱ ከማድረግ ይልቅ ለወጡበት ብሄረሰብ ብቻ ተቆርቋሪ መሆን ህዝብን ማስተዳደር የሚመስላቸው ኃላፊዎችም ራሳቸውን ከዚህ መሰል አጉል ተግባር ማቀብ ይገባቸዋል።
አመራሮች የሚመሯቸውን ህዝቦች እኩል መመልከትና በፍትሃዊነት ማገልገል ይኖርባቸዋል።የሀገርን ሰላም ከሚያናጉ፣ በህዝቦች መካከል ልዩነትንና መራራቅን ከሚፈጥሩ ንግግሮች ሊታቀቡ ይገባል።‹‹ዋሽቶ ከማጣላት ዋሽቶ ማስታረቅ›› እንዲሉ ሁል ጊዜ የህዝቦችን ሰላምና ፍቅር በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩም ይገባል።
ሰሜን ሸዋ ዞን የደፈረሰውን ሠላም ለመቆጣጠር የተቋቋመው የዕዝ ማዕከል – ኮማንድ ፖስት የጸጥታ ስጋት በተባሉ አካባቢዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ከባድ ጉዳት እንዳይደርስ ዋነኛ ሥራው አድርጎ መስራት የሚኖርበት ሕዝቡን ከጉዳት መጠበቅና ማረጋጋት ላይ መሆን ይኖርበታል። የደፈረሰውን ሰላም ለመመለስና ዜጎች ወደ ቤታቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን እንዲቀጥሉ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል በአካባቢዎቹ ተሰማርተው አጥፊዎችን ለፍትህ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።
በርግጥ ፖሊስ፣ ልዩ ሃይልና፣ መከላከያ ሠራዊት ለሰላምና ደህንነት የቆሙ ዘቦች እንደመሆናቸው ተልዕኳቸው በማንኛውም ሰው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም ነው።የጸጥታ ሃይሉ የተሰጠውን ኃላፊነት ሥራ ላይ የሚያውለው ከወገንተኝነት በጸዳ መልክ መሆን ይገባዋል።
በተጨማሪም እያንዳንዱ ዜጋ ሰላሟ የተረጋገጠ ሀገር እንድትኖረው የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት።ማናችንም ብንሆን ከራሳችንና ከብሄረሰባችን በፊት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የምትቀጥልበትን ሁኔታ አስበን መስራት ይኖርብናል።ዛሬ በአንድ ብሄረሰብ ማዕቀፍ ውስጥ ነን ብለን በጉያችን የምንደብቃቸው አጥፊዎች ነገ ለህልውናችን አደጋ የሚፈጥሩ መሆናቸውንም መገንዘብ ይኖርብናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እውነተኛ የሀገርና የህዝብ ተቆርቋሪ ከሆኑ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አውድ ተገንዝበው ከአደጋ ሊታደጓት ይገባል።የአገራችንን ሰላምና ዕድገቷን የማይፈልጉ የውጭና የውስጥ ጠላቶቿ ተቀናጅተው እየሰሩ ባለበት በዚህ ወቅት በህዝቦች መካከል የሚፈጠረው ግጭት ለምን ዓላማ ተፈልጎ እንደሚነሳ ማስገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር ጣታቸውን ወደ መንግሥት የሚጠቁሙና በህዝቦች ስቃይ የሚቆምሩ ፖለቲከኞችም ሀገር አፍራሾች በሚቀዱት ቦይ መፍሰስ ጉዳቱ ከባድ መሆኑን ተገንዝበው ራሳቸውን ከጥፋት መንገድ ማራቅ ይገባቸዋል።
በአጠቃላይ ሁላችንም ስለ ሀገራችን ሰላምና ስለህዝባችን ደህንነት የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማበርከት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ከሁላችንም የሚጠበቅ ግዴታ ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15/2013