ኢትዮጵያ እንድትፈርስ፣ ህዝቧም እንዲበተን አጥብቀው የሚሠሩ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር እያጋጩ ፤ ህዝብን በህዝብ ላይ ፣ ህዝብን በመንግሥት ላይ እያነሳሱ የሀገር ሰላም ጨርሶ እንዲደፈርስ ከውስጥና ከውጭ ሆነው የሚሠሩ ናቸው። የተለያየ የጥፋትና የእልቂት አጀንዳ በመቅረጽ የሀገርንና የህዝብን ሰላም ለማናጋት ቀን ከሌሊት በቅጥረኝነትና በተላለኪነት ይተጋሉ።
ዜጎችን በማያውቁት፣ ባልነበሩበትና ባልሠሩት ትርክት እየተረኩ ሲላቸው በዘር ፤ ሲያሻቸው ደግሞ የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት ያለዕረፍት ይተጋሉ። እነዚህ ኃይሎች በፈጠሯቸው ሴራዎች በተለያዩ አካባቢዎች ብዙዎች ህይወታቸውንና ቤት ንብረታቸውን አጥተዋል። ከቀያቸው ተፈናቅለውና ተሰደው ለችግር ተጋልጠዋል። ይሄ ሰላምን የማደፍረስ እንቅስቃሴ አሁንም ቀጥሏል።
የኢትዮጵያን ልማት፣ እድገትና ብልጽግና የማይፈልጉ እነዚህ የጥፋት ቡድኖች የሀገርን ሰላም እያደፈረሱ፣ ትናንትም ነበሩ፤ ዛሬም ቀጥለዋል፤ ነገም ሊኖሩ ይችላሉ። ሴረኞችን ማሸነፍ የሚቻለው ታዲያ በየጊዜው የሚወረወሩ አጀንዳዎችን በአስተዋይነት በማክሸፍና በቀደዱት የጥፋት ቦይ ባለመፍሰስ ፣ የውስጥ አንድነት በማጠናከርና ሁሉም በየደረጃው በአንድነት የሰላም ዘብ በመሆን ብቻ ነው።
ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች የሚሰሙና የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች ብዙ ናቸው። በጸጥታ ችግር ምክንያት ወጥቶ መግባት ስጋት መሆኑም ይታወቃል። ህዝብም በማያውቀው ነገር ህይወቱን እያጣ ፣የአካል ጉዳት እየደረሰበት እና ቤት ንብረቱን እያጣ ይገኛል። ይሄ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ክስተት ነው። ይሄን በሴረኞች የተተበተበን የሰላም መደፍረስ ማቆም የሚቻለው በሰለጠነ የጦር ሠራዊት ብቻ ሳይሆን በህዝብ ትብብር ጭምር ነው።
ህዝብ ከተባበረ የማይወጣውና የማይወርደው ዳገትና ቁልቁለት አይኖርም። ከህዝብ ፊት የሚሸሸግ ምንም ነገር ስለማይኖርም ህዝብ ከተባበረ የጥፋት ኃይሎችን መንጥሮ ማውጣትና የጥፋት አጀንዳውን አስቀድሞ በማወቅ ማክሸፍ ይችላል።
ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ለማንም ለምንም ነገር የሰላም ዋጋው ትልቅ ነው። ያለ ሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ እና ነግዶ መክበርና ማትረፍ አይቻልም። በፖለቲካ ፓርቲ መሳተፍ፣ መወዳደርና ሀገር ለመምራት ማሰብ የሚቻለው ሀገርና ህዝብ ሰላም ሲሆኑ ብቻ ነው። ካለ ሰላም ሀገር፣ ሃይማኖትና እምነት ፣ወልዶ ከብዶ ወግ ማዕረግ አይቶ መኖር ጭራሽ አይታሰብም። ስለዚህ ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም ትልቅ ዋጋ ልንሰጥና ስለሰላም ልንዘምር ይገባል።
በሀገራችን ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የቀረው ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ነው። ለምርጫው አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተካሂዷል። የመራጮች ምዝገባ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውንና ፕሮግራሞቻቸውን እያስተዋወቁ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ።
ይሄ የሆነው በሀገራችን አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ነው። ነገም የምርጫ ድምፃችንን የምንሰጠው መምረጥም ሆነ መመረጥ የሚኖረው የሀገር ሰላም ሲኖርና ጸጥታው አስተማማኝ ሲሆን ነው። ሰላም ከሌላ የምናስበውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ቀርቶ በህይወት መኖር አጠያያቂ የሚሆንበት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ስለዚህ በሀገራችን ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉ ወገን ስለሰላም ሊቆም ይገባል።
ሰላምን የማስከበር ጉዳይ ለእገሌና ለእገሊት የሚባል አይደለም። ሁሉም ሰው፣ ሁሉም ተቋም ፣ የሃይማኖት ድርጅት ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ሁሉ የሰላም ጉዳይ ይመለከተዋል። አሁን ሀገራችን ባለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ሰላምን ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መቀመጥ ወይም ዳር ሆኖ መመልከት ተገቢ አይደለም።
በእርግጥ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሰላምን የማስከበር ጉዳይ የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ ነው። ሆኖም ግን በሀገር ላይ ሰላም ሲደፈርስ ተጎጂው እያንዳንዱ ዜጋ ነውና ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እና ከመንግሥት ጎን ሆኖ መተባበር አለበት።
የሰላም ጉዳይ ለተወሰነ አካል ወይም ቡድን የሚተው ስላልሆነ መንግሥት ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መላው ህዝብ ሰላም የጋራ ጥቅም መሆኑን በመረዳትና ከሁሉም ነገር በፊት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት በዚህ ወቅት ለጋራ ሰላም በጋራ ሊቆሙ ይገባል። ያስፈልጋልም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 14/2013