ዳንኤል ዘነበ
ከሰዎች ጋር በቀላሉ ተግባቢ ነው ።ቀልጣፋና ነገር አዋቂነቱ ከእውቀቱ ጋር ተደምሮ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ አድርጎታል።እርሱ ለትምህርት በሚሰጠው ግምት የተነሳ ጓደኞቹ ሳይቀር ይገረሙበታል።«ለእኔ ትምህርት የእውቀት መሰረት ብቻ ሳይሆን ፤ራሴንና ቤተሰቦቼን ከድህነት የማወጣበት መንገዴ ጭምር ነው»የሚል አባባል ያዘወትራል ።በመዲናችን አዲስ አበባ ተወልዶ አድጎ ፤የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል።ወጣቱ አቡበከር አብዱ መሀመድ ።
አመለሸጋው አቡበከር ለህልሙ እውን መሆን በትጋት ይማራል።በተግባርም ህልሙን እውን ለማድረግ እየተቃረበ ለመሆኑ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በነበረው የትምህርት ሂደት አስመስክሯል።በትምህርት ቤት ህይወቱ በጉብዝናው ተለይቶ የሚታወቀው አቡበከር ፤የ10 ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ መሰናዶ ትምህርት መሸጋገር የቻለው። አቡበከር በዚህ መንፈስ ተሞልቶ የ12 ኛ ክፍል ፈተናውን ተፈተነ።
ዩኒቨርሲቲ ገብቶ፣ ተመርቆ፣ ስራ ይዞ በችግር ተቆራምደው ያስተማሩትን ወላጅ እናቱን ሥለመጦር ዘወትር የሚያልመው አቡበከር፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ውጤት ይፋ ሲደረግ ከህልሙ ጋር የሚጋጭ ክስተት ተፈጠረ። አቡበከር ስለ ክስተቱ አምስት ዓመት ወደ ኃላ ተመልሶ እንዲህ ሲያስታውስ፤ «12 ኛ ክፍል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ፈተና ተፈትኜ ውጤት እየጠበኩ ነበር። የምጠብቀው የፈተና ውጤት ጊዜው ደረሰና ይፋ ተደረገ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ ውጤቴ ሲሰጠኝ፤ ያመጣሁት ውጤት ፍጹም ያልጠበኩት ነበር። ከጠበኩት እጅግ በጣም ዝቅ ያለና፤ወደ ዩኒቨርሲቲ ራሱ የማያስገባ ነው። ይሄንን ስመለከት መኖሬን ለመጀመሪያ ጊዜ ጠላሁ» ሲል ነበር የመኖርን ትርጉም፣የህይወት ጣዕም ከገባው ጊዜያት በኃላ፤መኖሩን ሲጠላ ለመጀመሪያ እንደነበር ያመላከተው።
የ12ኛ ክፍል ውጤቱን ለመቀበል ሳይሆን ለማመን እስከ መቸገር እንደደረሰ አስታውሶ፤ ለቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኑና፤ በትምህርቱ ብዙ ርቀት ይጓዛል ብለው የሚጠብቁት ወላጅ እናቱ ልባቸው እንዳይሰበር በማሰብ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያብራራውአቡበከር፤ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ወራት በቁዘማ በድንዛዜ ስሜት ውስጥ ገብቶም ነበር። በህይወቱ ገጥሞት ከነበረው አስቸጋሪ፣ ፈታኝ ጊዜን በማለፍ ወላጅ እናቱን የሚጦርበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
ከአምስት ዓመት ከገባበት የህይወት ቅርቃር መውጣት መቻሉ እንቆቅልሽ ይፈጥራል። አቡበከር በአንገቱ ሁለት ሜዳሊያዎች፤ በእጁ ወደ ያዘው ዋንጫ በኩራት እየተመለከተ ነበር እንቆቅልሽ የፈታልን፤«በትምህርት ቤቱ የእኔን አቅምና ብቃት የሚያውቁ ተማሪዎች፣መምህራን፣ የሰፈሬ ሰዎች፣ቤተሰቦቼ ጭምር በውጤቱ አብረውኝ አዝነዋል።
በወቅቱ ወደ ዩኒቨርሲቲ መግባት አለመቻል ብቻም ሳይሆን ፤በክፍያ ወደ ግል ከፍተኛ ተቋም ለመግባት የገንዘብ ችግር እንዳለብኝ ሳስብ የበለጠ ስሜቴ ተጎዳ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳለሁ ነበር በሆፕ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት እድል ያገኘሁት።እድሉን በአግባቡ ተጠቀምኩኝ»ሲል ይናገራል።
አቡበከር ትምህርቱን በአግባቡ ተከታትሎ በማጠናቀቅ፤ ታህሳስ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በአካውንቲንግና ፋይናንስ በዲግሪ ለመመረቅ በቅቷል። መንፈሰ ጠንካራው ወጣት ትምህርቱን ከማጠናቀቁ ባሻገር፤ ከተመረቁት 424 ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማምጣቱ ትልቅ ትርጉም እንደሰጠው ይናገራል።
«እኔን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ መሆን ችለናል። ተቋሙ እንዲህ አይነት እድል ባይሰጠን ኖሮ ቤተሰባችን ከፍሎ የማስተማር አቅም ስለሌለው መማር እየፈለግን ሳንማር እንቀር ነበር።
የእኔም ሆነ የጓደኞቼ የህይወት መሥመር ሌላ ሊሆን ይችል ነበር። ስለዚህ እኔ ከፍተኛ ውጤት ማምጣት መቻሌ ተቋሙ በሚያደርገው በጎ ተግባር ስኬታማ መሆኑን መገንዘብ ያስችለዋል። ተቋሙ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ያበረታዋል» ሲል ያብራራል።
ሆፕ ዩኒቨርሲቲ እንደ አቡበከር አይነት በችግር ምክንያት መማር የማይችሉ የነበሩ በርካቶች የነጻ ትምህርት እድል ተጠቃሚ በማድረግ ለህይወታቸው መቀየር አበርክቶ አድርጓል።ታህሳስ 10 ቀን 2013 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲው ከተመረቁት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል ሁለተኛውን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ያጠናቀቀችው ተማሪ በተቋሙ የነጻ የትምህርት እድል ተጠቃሚ ከሆኑት 200 ተማሪዎች አንዷ ናት። በዚህም ተቋሙ ማህበራዊ ሀላፊነቱን ከመወጣት አኳያ በትክክለኛው ጎዳና እየተጓዘ ሥለመሆኑ ያመላክታል።
የሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተረፈ ፈየራ እንደሚሉት፤ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የተቋቋመው ‹በተስፋ ደርጅት ኢንተርፕራይዝ ሥር በመሆን ድርጅቱ የሚሰጠውን ማህበራዊ አገልግሎት በገንዘብ መደገፍ› አንዱ የተቋቋመበት አላማ መሆኑን ይገልጻሉ።
በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ አበርክቶ ማድረግ ሌላው አላማው መሆኑን ይናገራሉ። በ2003 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ የማስተማር ሥራውን መጀመሩን ያስታውሳሉ።ተቋሙ የትምህርት ፍላጎትና አቅም እያላቸው ከፍለው መማር ለማይችሉ ወገኖች ነጻ የትምህርት እድል በመስጠት ማህበራዊ ግዴታውን ለመወጣት የሚከተለው አሰራርን መኖሩን ያመለክታሉ ።
ፕሬዚዳንቱ፤ «ይህም እንደ አቡበከር አይነት በትምህርት ብዙ ርቀት መጓዝ የሚችሉ ነገር ግን በችግር ምክንያት ወድቀው ሊቀሩ የሚችሉ ወገኖችን መታደግ ያስችላል። ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ለብዙዎች የስኬት መደላድልን መፍጠር ችሏል እየፈጠረ ይገኛል። በየዓመቱ 200 ተማሪዎች በመቀበል በነጻ የሚያስተምር ሲሆን ፤እነዚህ ተማሪዎች እንደ ችግራቸው ሁኔታ የኪስ ገንዘብ ፣የምግብ፣ የመኝታ፣ የትምህርት ግብዐቶች እንዲሟላላቸው በማድረግ ይማራሉ። የተማሪዎቹን ሥነ ልቦና ለመጠበቅ ደግሞ በካምፓሱ ውስጥ ቀለል ቀለል ያሉ ሥራዎች በላይብረሪ አካባቢ ፣በካፌ አካባቢ እንዲሰሩ በማድረግ የተረጂነት ስሜት እንዳይፈጠርባቸው ይደረጋል» ሲሉ ያብራራሉ።
የነጻ የትምህርት እድሉን በመጠቀም ላለፉት አስርት ዓመታት በርካቶች ተምረው ከፍተኛ ደረጃ መድረስ መቻላቸውን ያመላከቱት ዶክተር ተረፈ፤ በተቋሙ የእድሉ ተጠቃሚ የነበሩ ተማሪዎቻችን ወደ ሥራ አለም ከተቀላቀሉ በኃላ የተቋሙ በጎ ተግባር ተጋብቶባቸው በአንድ ላይ በመሰባሰብ ችግሮችን የሚደግፍ ኤን ጂ ኦ እስከማቋቋም የደረሱ መኖራቸውን ያመላክታሉ። በተለያዩ ጊዜያት እየመጡ የሚጎበኙና የህይወት ልምዳቸውን ፣እውቀታቸውን በማጋራት ዛሬም ቤተሰባዊነታቸውን የሚያሳዩም በርካቶች መሆናቸውን ጨምረው ይናገራሉ።«ይህም ተቋሙ እየሄደበት ያለው መንገድ ትክክለኛ መሆኑን ይጠቁማል። ከዚህ ባሻገር በሥነ ምግባር የታነጸ ወገኑን ፣ሀገሩን የሚወድና የሚጠቅም ዜጋ ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ስራ እየተሰራ ይገኛል » ሲሉም ይገልጻሉ።
በ2003 ዓ.ምበአምስት የትምህርት ፕሮግራሞች በ250 ተማሪዎች የመማር ማስተማሩን የጀመረው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ፤ ማህበራዊ ሃላፊነቱን መርሆ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ መሆኑን ይናገራሉ። ዶክተር ተረፈ ሲያብራሩ፤ «በኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኝ አንድ የግል ከፍተኛ ትምህርት በትምህርት ዘርፍ ለማሳካት የሚያስቀምጣቸው ተልዕኮዎች አሉት። ብቁና የተሟላ ክህሎት ባለቤት የሆኑ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ማስመረቅ የሚለው አንዱና ዋነኛው ነው። ተቋሙ ሲመሰረት የረጅም ጊዜ እቅድ ተይዞ፣ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች ከ‹ሀ ›እስከ ‹ፐ›በሚገባ በማሟላት የተንጣለለ ካምፓስ በመገንባትና በተጠናከረ መልኩ እንዲደራጅ ተደርጓል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለማለፍ ደግሞ ስምንት ዓመታትን ፈጅቷል፡፡›› ይላሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የመቀበል አቅሙ እስከ ስድስት ሺህ የሚደርስ መሆኑን ያመላከቱት ፕሬዚዳንቱ፤ በየዓመቱ የሚቀበላቸው ተማሪዎች ከሁለት ሺህ እንደማይበልጡ ይናገራሉ። ተቋሙ አቅሙን የገደበበት ምክንያት ደግሞ ተማሪዎቹን በተጨናነቀ መንገድ ማስተማር ስላልፈለገ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህም በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።በተጨማሪም የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ እንዲቻል በውጪ ሀገር ከሚገኙ መሰል ተቋማቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ያነሱት ዶክተር ተረፈ፤ የተለያዩ አለም ዓቀፍ ሥልጠናዎችን ለመምህራኖቻችን እንዲወስዱ በማድረግ አቅምና ክህሎታቸውን የመገንባት ሂደት መኖሩን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሞክሮውን መውሰድ ቢችሉ በስፋት ለሚስተዋለው የትምህርት ጥራት ችግርን የሚያሻሽል መሆኑን ያመላከቱት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2013