ለውጡን ተከትሎ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሀገርን አንድነትና ደህንነት አደጋ ላይ የጣሉ መጠነ ሰፊ የሴራ ተግባራት ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑ ይገኛል። ትህነግ ከሄደበት ከለየለት ሀገር የማፍረስ አኩይ ተግባር ጀምሮ ከህዝባችን ጋር ለዘመናት አብረው የቆዩ ሐገራዊ እሴቶችን የሚፈታተኑ የተለያዩ አኩይ ተግባራት ታቅደው ጊዜና ቦታ ተለይቶላቸው ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ካካበተው የአብሮነት እሴቶችና ችግሮችን ያለከፋ ጉዳት የመፍታት የካበተ ባህል አንጻር ሁኔታዎች የተገመዱበትን ሴራ ያህል ጥፋት ባያስከትሉም ሀገርና ህዝብን ግን ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍለዋል።
በአንድ በኩል የትህነግ ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በህዝባችን ውስጥ የዘራው ሀገር አፍራሽ ሴራ፤ በሌላ በኩል ለውጡ የመጣበት መንገድ በቀደሙት ዘመናት ከነበረው የለውጥ አስተሳሰብና መንፈስ የተለየ መሆኑ በራሱ የፈጠረው ተግዳሮት ተዳምረው ሀገራዊ የስጋት ምንጭ ሆነዋል ።
ከዚህም በላይ ለውጡ ይዞት የመጣው ተስፋ ስጋት የሆነባቸው የውጪ ሀይሎች ውስጣዊ ችግሮቻችንን እንደ መልካም አጋጣሚ የማየታቸውና ለዚሁ ዓላማቸው የሚያድሩ አፍራሽ ቡድኖችን በቀላሉ ማሰለፍ መቻላቸው ሌላኛው የተግዳሮቱ ገጽታ ነው። የተለያዩ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ሲመቻቸው በግልጽ ሳይመቻቸው በስውር እየሄዱበት ያለው የሴራ መንገድም ሀገራዊ ፈተናውን አሳድጎታል ።
እነዚህ ተግዳሮቶች ለውጡ ይዞት ከመጣው ተስፋና ለውጡ ራሱ ከመጣበት አዲስ የፖለቲካ ባህል አንጻር የሚጠበቁ ስለመሆናቸው ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ድንገትም ከመጣንባቸውና ለመከኑ የለውጥ ጊዜያት ከከፈልናቸው ከፍ ያሉ ዋጋዎች አኳያ ሲነጻጸርም ኪሳራው የከፋ ነው ሊያስብል የሚያስችል አይደለም ።
በርግጥ ሀገሪቱ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ብዙ የሟርት ቃል ስታስተናግድ ቆይታለች። ዛሬም እነዚሁ የሟርት ቃሎች መገለጫቸው ይለዋወጥ እንጂ አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር አደባባይ የመሙላታቸው እውነታ የተለመደ ሆኗል ። በተለይም ለውጡና የለውጡ ሀሳብ በተጨባጭ በጥቅማቸው ላይ የመጣባቸው ቡድኖች ባላቸው አቅም ሁሉ ለውጡን ከማቆሸሽና ከማጥላላት የተኙበት ጊዜ የለም።
በአንድ በኩል ሀገራዊ ራዕይና ኃላፊነት የተሸከመ ተቋም እንዳይኖር፤ በሌላ በኩል በህዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲኖር በስፋት በተሰራበትና ዛሬም እየተሰራበት ባለበት የውጪ ሀይሎች ጊዜው አሁን ነው ብለው ባለ በሌለ አቅማቸው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሠላምና አስተማማኝ ጸጥታ የማስፈንን ስራ ከምንም በላይ አቅሎ ማየት ተገቢ አይሆንም።
የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫ በመከፋፈል በሚፈጠር ክፍተት ነፍስ ለመዝራት የሚሞክሩ ኃይሎችን ጨምሮ በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሃገራዊ አለመረጋጋቱ የፖለቲካ ትርፍ ያመጣልናል በሚል የተተሳሳተ ስልት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ባሉበት ሁኔታ መላው ህዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሰላምና የመረጋጋት ስራው የኔም ጭምር ነው ብሎ መንቀሳቀስ ካልቻለ አደጋው ሀገራዊ መሆኑ የማይቀር ነው።
ይህ እውነታ በለውጥ ወቅት የሚፈጠር ከመሆኑ አንፃር ተጠባቂ ቢሆንም መንግሥት እያንዳንድዋ እንቅስቃሴ ሐገራዊ የለውጥ አመራሩን የሚጎዳ ከመሆኑ አንጻር ከዛም በላይ ሐገራዊ የደህንነት ስጋት እየሆነ ስለሚሄድ በተገቢው አግባብ ሊከታተላቸውና በማያዳግም እርምጃዎች ሊያስተካክላቸው ይገባል።
ወቅቱ መላው ህዝባችን ብዙ ተስፋ የሰነቀበት ከመሆኑ አንጻር ይህንን ማህበራዊ እውነታ ለውጡን ለማስቀጠል እንደ አንድ ትልቅ አቅም አድርጎ በማየት የህዝቡ የለውጥ ስሜትና መንፈስ ከመቀዛቃዙ በፊት ፈጣን ስትራቴጂክ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል። እርምጃዎቹ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ስለማምጣታቸውም በአግባቡ ማሰብ ይፈልጋል ።
በየቦታው የመንግሥትን ትኩረት ለመበታተን በሚደረጉ እኩይ ተግባራት እንደ ሀገር እየከፈልነው ያለው ዋጋ ዕለት ዕለት እየጨመረ መምጣቱ ፤ ከዛም ባለፈ ዜጎች የደህንነት ስጋት ውስጥ የመግባታቸው እውነታ በመለውጡ የነበራቸውንና አሁንም ያላቸውን ተስፋ ሊሸረሽረውና ወደ ተስፋ መቁረጥ ሊወስደው እንደሚችልም ልብ ሊባል ይገባል ። ይህ ደግሞ በራሱ ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ የከፋ እንደሚሆን ለማሰብ አይከብድም።
በተለይም በጸጥታና ደህንነት ዙሪያ የሚሰሩ የፌዴራል ሆነ የክልል ተቋማት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ተቀራርበው ሊሰሩና ተናበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ከተሰጣቸው ከፍ ያለ ሀገራዊ ኃላፊነት አንጻርም በተሻለ ተጠያቂነት የሚንቀሳቀሱበትና የተልዕኮ ውጤታማነትን የሚያጎናጽፋቸውን የአሰራር ስርዓትን ሊከተሉም ይገባል ።
መላው ህዝባችንም ቢሆን እስካሁን የመጣንበት የለውጥ መንገድ እንደ ሀገርና ህዝብ ብዙ ዋጋ ያስከፈለን ቢሆንም ለውጡ ይዟቸው ከመጣቸው የተሻሉ ነገዎች አንጻር ነገሮችን በሰከነና በተረጋጋ መልኩ ማሰብ እና ለነገሮች ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል። ለዚህም ህገወጦችን ማጋለጥ፣ ለመንግሥት ትክክለኛ መረጃ መስጠትና ሰላሟን ማስጠበቅ ይኖርበታል።
ጠላቶቻችን በቀደዱልን የጥፋት ቦይ መፍሰስ ከዛሬ ይልቅ ነገ የከፋ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል ለአፍታ መዘንጋት የለብንም ። ዛሬ በአንድም ይሁን በሌላ እየከፈልነው ያለው ዋጋ ሌላ ተጨማሪ ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል በተገቢው መንገድ ማሰብ ይጠይቃል።
ዛሬ ያለችው ሀገር ብዙ መስዋዕት በከፈሉ ዜጎች የመስዋዕት ደም የተገነባች እንደመሆኗ መጠን ፣ ለነገው ትውልድ የምናስረክባትም ሀገር በተመሳሳይ መስዋዕትነት የተገነባች እንደምትሆን ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም። ዛሬ በተለያየ ሴራ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰማእት ዜጎቻችን ለነገ ተስፋ ያደርግናት ሀገር የመስዕዋት ምሰሶዎች ናቸው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12/2013