በሀገራችን ለውጡን ተከትሎ ሀገራዊ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ያስቻሉ፣ ለለውጡም አንድ ትልቅ ትርጉም የሰጡ ተግባራት መከናወናቸው የሚታወስ ነው ። ይህንንም ተከትሎ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ከስደት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ችለዋል ። በሀገር ውስጥም የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በተሻለ መልኩ ቀና ብለው መሄድ የቻሉበት ዕድልም ተፈጥሯል።
ይህ ዕድል ድንገት በአንድ ምሽት በሥልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች ተስማምተው በይሁንታ ተግባራዊ ያደረጉት ሳይሆን ብዙ ዜጎች ህይወታቸውን ገብረው የተገኘ ትልቅ የፖለቲካ ድል ነው ። የዘመናት የትውልዶች እውነተኛ መሻት ምላሽ ነው።
ይህን ታሪካዊ እውነታ ወደ ሀገርውስጥ የገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ ለዓመታት አንድም በአጫዋችነትና አድማቂነት በሌላም በኩል ደግሞ አንገታቸውን ደፍተው በተፈቀደላቸው ልክ ያህል ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትንሳኤ ያህል የሚቆጠር ዕድል ይዞ መምጣቱ ይታመናል ።
ይህንን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ሀገራዊ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ለመክፈት ራሳቸውን አዘጋጅተው በአዲስ መንፈስና በተሻለ ተስፋና የፖለቲካ ዲሲፕሊን በፖለቲካው መድረክ ተቀላቅለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጥቂት አይደሉም።
በሌላ በኩል ለሀገርና ለህዝብ ብሎም ለፓርዎቹ ለራሳቸው እጣ ፈንታ ትልቅ እድሎች ይዞ የመጣውን እውነታ ገና ከጅምሩ ትርጉም አልባ የሆነ መንገድ በመያዝ ከፖለቲካ ፓርቲነት ወደ የነፍሰ ገዳዮች ጥርቅም የተለወጡ መኖራቸውም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
እነዚህ ኃይሎች ምንም የማያውቁ ንጽሃንን በማንነታቸው ምክንያት በአስከፊና በአሳዛኝ ሁኔታ በመግደል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ረጅም መንገድ ተጉዘዋል። በንጹህነቱ ምስክር የማያስፈልገውን ገበሬ በቀዬው ሀገር ሰላም ብሎ በተቀመጠበት በአሰቃቂ ሁኔታ ለህልፈት ዳርገውታል። ዛሬም እየዳረጉት ነው።
የእነዚህ ኃይሎች ትልቁ ዓላማ በህዝቦች መካከል መቃቃርንና ሐገራዊ ትርምስን በመፍጠር ከዚህ ሀገራዊ ትርምስ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ቁመራ ነው። በተለይም በአማራና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል ያለውና የነበረውን አብሮነት ጭካኔ በተሞላበት ግድያ ችግር ውስጥ በመክተት ሀገራዊ አንድነቱን ስጋት ውስጥ መክተትን ዓላማ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው።
ለዚህ ደግሞ በማንም ላይ የጥይት ቃታ ለመሳብ ወደ ኋላ የማይለው የኦነግ ሸኔ ቡድን በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ቡድኑ የትህነግ የክፋት ዘር ማፍያ ማሳ ከመሆን ባለፈ የኦሮሞን ህዝብ ከለላ በማድረግ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ከፍ ያሉ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግድያዎችን ሲፈጽም ቆይቷል።
ከዚህ በላይ እወክለዋለሁ ፣ እታገልለታለሁ የሚለውን የኦሮሞ ህዝብ ሳይቀር ሰላም በመንሳት፤ በህይወት እያሉ በእሳት ሲያቃጥል በጠራራ ጸሀይ በጥይት ሕይወታቸውን ሲቀጥፍ ቆይቷል። ቡድኑ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚፈጽመው የግድያ ተግባሩ በየዕለቱ የዜጎችን ሞት እንድንሰማና እንድንለምደው አድርጎናል።
በየክልሉ እየተንቀሳቀሰ በሚፈጽማቸው ግድያዎች ብዙ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ አጥተናል። ይህ ነፍሰ ገዳይ ቡድን በሚያፈሰው ደም ያህል የገዘፈ እስኪመስል ድረስ ገዝፎ የሚታይበት እውነታም ተፈጥሯል። በተጠና መንገድ አድብቶ እየሄደበት ያለው የጥፋት መንገድ ዛሬም ብዙ ዜጎቻችንን እያሳጣን ነው። የህዝቡንም ትዕግስት ክፉኛ እየተፈታተነ ነው።
የቡድኑ የጭካኔ ተግባር ሰው የሆነን ፍጡር ትዕግስት ከፍ ባለ ሁኔታ የሚፈታተን ነው። ቡድኑ እያደረገ ያለውን ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ለማውገዝ የሚከብደው ሰብአዊ ፍጡር አለ ብሎ መገመት የሚቻል አይደለም። ቡድን በጭካኔ ተግባሩ ትናንት እንደተወገዘ ሁሉ ዛሬም ነገም በታሪክ ውስጥም እየተወገዘ መኖሩ የማይቀር ነው።
ከሁሉም የሚከፋው ግን የዚህን ነፍሰ ገዳይ ቡድን ግድያን የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ የተሻለ መንገድ አድርገው ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ ሃይሎች ጉዳይ ነው። እነዚህ ሃይሎች በንጹሀን ዜጎቻችን ደም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየሄዱበት ያለው መንገድ በቀደሙት ዘመናት ሀገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ስለመሆኑ ዋቢ መጥቀስ አያስፈልግም።
ትህነግ ትናንት በትግራይ ህዝብ እየማለና እየተገዘተ በትግራይ ወንድሞቻችን የነጻነትና የእኩልነት ሀገራዊ ራዕይ በተከፈለ መስዋዕትነት ፍጹም አምባገነን ሆኖ መገለጡ የአጋጣሚ አይደለም። ይህ ደግሞ ሕዝብን የቁመራ ካርድ አድርጎ የመጠቀሙ እውነታ ማሳያ ነው። ይህ ቡድን በትግራይ ህዝብ እስከ መጨረሻዋ ሰዓት ሲቆምር እንደነበር አሁንም ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ለቁመራ ካርዱ የትግራይን ህዝብ ለመጠቀም እየሞከረ ነው ። ለትግራይ ህዝብ ያለእኔ የሚለው እውነታ ምን ሀቅ እንዳለው ደግሞ ዛሬ ላይ የትግራይ ህዝብ የገጠመውን ፈተና ማየት በቂ ነው።
ዛሬ ላይ ነፍሰ ገዳዮች በህዝባችን ላይ በተለይም በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸሙት ባለው አስከፊ ወንጀል ከማንም በላይ እኔ ይሰማኛል የሚል ያልተገራ ሀሳብና ቋንቋ ይዘው የህዝብን የተጎዳ ስሜት የመቆመሪያ ካርድ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉ ፓርቲዎችና ግለሰቦች እየሄዱበት ያለው መንገድ አሳፋሪ ነው።
ተግባሩ የአማራን ህዝብ የቀደመ የስነ ልቦና መሰረት ሊያናጋ የሚችል ፤ ከዛም በላይ የአማራን ህዝብ የሚያሳንስና ከነፍሰገዳዮቹ ባልተለየ መልኩ በህዝብ ጉዳት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቁመራ ነው ።
የአማራ ህዝብ በማንነቱ እየደረሰበት ያለው ግድያ ለምን እንደሆነ የሴራው መሰረቱና ግቡ ምን እንደሆነ የአደባባይ ሚስጥር በሆነበት ሀገር የአማራን ህዝብ ክፉ ቀኖች የፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ ካርድ አድርጎ የመምረጡ ጉዳይ የአማራ ህዝብ በሀገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ያለውንና የነበረውን ታሪክ ማሳነስ ነው ።
በአማራ ህዝብ ላይ ማንነትን መሰረት አድርጎ የሚደርሰው ግድያ ሊቆም ይገባል። የአማራ ህዝብ ላይ የሚደርስ ግድያ በመላው ህዝባችን ላይ የሚደርስ ግድያ ነው። ይህ የማይሰማው ዜጋ የለም ።ግድያዎችን ለማውገዝ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው ።
መንግስትና የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ለዜጎች የደህንነት ማስተማመኛ መስጠትም ይጠበቅባቸዋል ። ይህንንም አድርገው ተጨባጭ እርምጃና ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።ይህ የህግም የሞራልም ኃላፊነታቸው ጭምር ነው።
በዜጎች ሞት ለመቆመር የሚደረገው ጥረት በኢትዮጵያዊ ስነልቦና እና እሴት ነውር ስለሆነ ፈጥኖ መቆም ይኖርበታል። በዜጎች ደም መነገድ በቀደመው ዘመን ብዙ ዋጋ ያስከፈለን፤ወደ ፊትም የከፋ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ሊያተርፈን የሚችል ባለመሆኑ ሊቆም ይገባል።
በአጠቃላይ ግድያውም ቁመራውም ፈጥኖ ሊቆም ይገባል። እስካሁን የሆነው በቂና ከበቂ በላይ ነው። የንጹሃን ደም ፍትህ እንዲያገኝ ሁላችንም ልንጮህ ይገባል ። የኔ ጩኸት ከእንትና ይበልጣል ብሎ ማሰብ እና ይህንንም የፖለቲካ የቁመራ ካርድ ለማድረግ መሞከርም ነውር ነውና ይህም ሊቆም ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2013