ለምለም መንግሥቱ
‹‹ኢትዮጵያን ለስምንት አመት ያክል አውቃታለሁ:: የተለያዩ የሀገሪቷን አካባቢዎች ለማየትም ዕድል አግኝቻለሁ:: ብዙ የሚወደዱና የሚደነቁ ተፈጥሮአዊ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶች አሏት:: ከታሪካዊ ቅርስዎችዋ መካከልም የላልይበላን ውቅር አብያተክርስትያን ጎብኝቻለሁ:: በጣም ድንቅና የሚወደድ ሥፍራ ነው::›› እንዲህ በአድናቆት ስለኢትዮጵያ ያላቸውን መልካም ስሜት የነገሩኝ ሰው ሚስተር ብሩክ ዋሽንግተን ይባላሉ:: የሮሃ ግሩፕ (ማዕከል) መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው::
ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የሚመሩት ሮሃ ማዕከል ስያሜ የላልይበላ የቀድሞ ስም ወይንም መጠሪያ ሲሆን፣ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥ የህክምና ተቋም ነው:: ይህ ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያለው የህክምና ተቋም በዋናነት የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም ሰዎች መንፈሳዊ ተዝናኖት እንዲኖራቸው አረንጓዴ ልማትን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛዎችንም አብሮ አካቷል:: ግንባታው የሚካሄድበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሥፍራ ቀደም ሲል ለፓርክ የተከለለ ሲሆን፣ አድዋ ፓርክ ተብሎ ተሰይሞም ነበር:: ለህክምና ግንባታ ሲውልም ቀድሞ የታሰበው ፓርክ አብሮ እንዲካተት መደረጉ ነው ሁሉን አቀፍ ያሰኘው:: ሚስተር ብሩክ ዋሽንግተን ማዕከላቸው ሁለት ተልዕኮን በመያዝ አገልግሎት የሚሰጥ ግዙፍ ግንባታ ለማከናወን መታጨቱን እንደ እድለኛነት ይቆጥራሉ::
እርሳቸው እንዳሉት እንደ ህንድ፣ ታይላንድ ያሉ ሀገሮች በህክምና ቱሪዝም (በሜዲካል ቱሪዝም) በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል:: አፍሪካ ለህክምና ወደነዚህ ሀገራት ይሄዳሉ እንጂ በሀገራቸው እየተጠቀሙ አይደለም:: ሰዎች ወደነዚህ ሀገራት ሲሄዱ በየአመቱ በአማካይ ወደ አምስት ሚሊየን ዶላር ያወጣሉ:: ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነ የህክምና ተቋም በመገንባት በሜዲካል ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን ወደ ሥራ መግባቷ ትልቅ ዕድል ነው::
‹‹በመላው ዓለም ስመጥር የሆነና ሰፊ መዳረሻ ያለው አየር መንገድ አላት:: ከተፈጥሮአዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የቱሪዝም መዳረሻ ሀብቷ ጋር ተደምሮ የሮሃ የህክምና ማዕከል ግንባታ ሥራ መጀመሩ ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ከፍ ይላል:: በማዕከሉ የሚሰጠውን ህክምና ፈልገው ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጉዘው ሲመጡ፣ በሆቴል በሚያደርጉት ቆይታ፣ የተለያዩ ዕቃዎችን ሲገዙና እግረ መንገድም በሚያደርጉት ጉብኝትና የሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ ሲራዘም የውጭ ምንዛሪ ግኝቷ ይጨምራል›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው የማዕከሉ መገንባት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን፣ ዜጎችም የህክምና ወጭያቸው ከፍተኛ ናቸው የሚባሉና በሌሎች ሀገሮች የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት በሀገራቸው ለማግኘት ያስችላቸዋል:: ተቋሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከተለያዩ የመንግሥት የህክምና ተቋማት ለሚላኩ (ሪፈር) ለሚደረጉ አገልግሎት ለመስጠት ማዕከሉ ከወዲሁ በዕቅዱ ማካተቱንና 10 ከመቶ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል::
ተቋማቸው ሀገሪቱ ከህክምና ቱሪዝም ፈጥና ተጠቃሚ እንድትሆን የግንባታ ሥራውን እንደሚያፋጥንና በያዘው ዕቅድም የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ አምስት የህክምና ተቋማት በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ማቀዱንና በአፍሪካ ውስጥም ቀዳሚ የህክምና ተቋም እንዲሆን እንደሚሰራ አስረድተዋል::
እንደ ዜጋም እንደ አንድ የከተማዋ የጤና ቢሮ ኃላፊ በግንባታው መጀመር የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ናቸው። ‹‹በከተማ ደረጃም ሆነ በሀገር በጥራትም በፍላጎትም የተሟላና ተገልጋዩን የሚያረካ የህክምና አገልግሎት ባለመኖሩ ህክምና ፍለጋ ወደተለያዩ ሀገሮች የሚሄዱ ዜጎች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ ነው:: ተገልጋዩ ወደማያውቀው ሀገር ሲሄድ ያልታሰበ ወጭ ያጋጥመዋል:: ከሀገሩ ውጭ በመሆኑም የሚሰማው ስሜት ይኖራል:: ተገልጋዩ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ አልፎ ከሚያገኘው ህክምና በተጨማሪ በሀገር ውስጥ ሊቀር የሚገባው ገንዘብ ይወጣል:: በሜዲካል ቱሪዝም በአመት በአማካይ ከአራት ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚወጣ ይገመታል:: ሀገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንጻር ጉዳት ነው:: በመሆኑም የግንባታ መሠረቱ የተጣለው ሮሃ ሁለገብ ግዙፍ የህክምና ማዕከል እነዚህን ሁሉ ክፍተቶች በመቅረፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል::›› ሲሉ ይገልጻሉ።
ሮሃ ሁለገብ ግዙፍ የህክምና ማዕከል ግንባታ የሚካሄድበት ቦታ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች እና ለኢትዮጵያ አየር መንገድም ቅርብ መሆኑ ኢትዮጵያን የህክምና መዳረሻ ያደርጋታል ተብሎ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት መሆኑን ይናገራሉ። በ28 ሄክታር ላይ 12 ቢሊየን ብር ወጭ የሚገነባው ይህ የህክምና ተቋም በሚገኝበት ሥፍራ የወንዝ ተፋሰስ በመኖሩና ዙሪያውን አረንጓዴ ለማልበስ ምቹ መሆኑ የአረንጓዴ መናፈሻ ሥፍራ ሆኖ እንዲያገለግል ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ የከተማዋ ነዋሪም ሆነ ከውጭ የሚመጡ እንግዶች ለህክምና ብቻ ሳይሆን በአረንጓዴ ሥፍራው አካላቸውንና አዕምሮአቸውን በማሳረፍ የመንፈስ እርካታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል::
እስካሁን የነበረው ተሞክሮ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ላይ ትኩረት ያደረገ ነው:: አሁን ደግሞ ሜዲካል ቱሪዝም ተጨምሯል:: በነዚህ በሁለቱ ጉዳዮች እንዲሁም ሜዲካል ቱሪዝም ለህክምና ወደ ተለያዩ ሀገሮች የሚሄዱ ዜጎችን ለማስቀረት፣ ወይንስ ከውጭ በሚመጣው ላይ ትኩረት ማድረግ ነው? በሚለው ላይ ምላሽ እንዲሰጡኝ ዶክተር ዮሐንስ ላቀረብኩላቸው ጥያቄ ኢትዮጵያን ለመጎብኘትና ለተለያየ ጉዳይ ለመምጣት የሚፈልጉ የውጭ ሀገር ዜጎች ለጉዞ ከመነሳታቸው በፊት ማወቅ የሚፈልጉት ወይንም የሚያረጋግጡት ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ተቋምና ሆቴል መኖሩን ነው:: በመሆኑም ኮንፈረስ ቱሪዝምና ሜዲካል ቱሪዝም ተመጋጋቢ ናቸው:: በዚህ ረገድ የህክምና ተቋሙ ለሀገር ትልቅ አቅም ይሆናል:: እንዲህ ያሉ ግንባታዎች በሌሎችም ሀገር በቀል በሆኑ ተቋማትም የሚቀጥሉ በመሆናቸው ከግንባታው ጎን ለጎን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት ተጠቃሚነትን የማሳደግ ተግባር ይከናወናል::
በከተማ አስተዳደሩም ከመቼም ጊዜ በበለጠ ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንቅስቃሴው ተጠናክሯል:: በጤና ዘርፉ ከ62 አመት በላይ ዕድሜ ያለውና አንድ ለእናቱ ተብሎ የሚጠራው የጋንዲ መታሰቢያ እንዲሁም የአበበች ጎበና የእናቶችና ሕፃናት የህክምና ተቋሞች በተለይም ለእናቶችና ለህፃናት በሚሰጡት አገልግሎት ማዕከሉ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል:: መረጃ አያያዝ ሥርአትንም ለማዘመን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል::
ዶክተር ዮሐንስ እንዳሉት፤ የልዩ ህክምና ፍላጎትን በመንግሥት አቅም ብቻ ማሟላት ስለማይቻል እንደ ሮሃ ያሉ ድርጅቶች በህክምናው ዘርፍ ላይ እንዲሳተፉ ማደረግ ተገቢነት ያለው ርምጃ ነው። ተቋሙ ባለሙያዎችንና ሌሎች ከግንባታ ሥራው ጀምሮ ለዜጎች የሚፈጥረው የሥራ ዕድልና የዕውቀት ሽግግር ጥቅሙን ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል ብለዋል::
ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆኑ ጤና ቢሮው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ውጣ ውረድ ሳይገጥማቸው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግና ጉዳዩን በባለቤትነት በመከታተል እስከ ፍጻሜው ለማድረስ፣ ወደ ሥራም ከገባ በኋላ ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል:: የውስጥ አካል ንቅለ ተከላ፣ የጭንቅላትና ህብለሰረሰር ቀዶ ጥገና፣ የመውለድ ችግር ለሚያጋጥማቸው፣ የካንሰርና ሌሎች ህክምናዎች ጎን ለጎን የስልጠና ማዕከልም ሆኖ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ ባለሙያዎችንም በማፍራት እንደሀገር ብቁ የሆኑ የህክምና ባለሙያዎች እንዲኖሩ በማስቻል እንደሚያግዝ ይጠቅሳሉ::
ከዚህ ቀደምም እንዲሁ የልዩ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ለከተማዋ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል ተብሎ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሲኤምሲ አካባቢ መሬት ተረክበው የቀድሞ ጥቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የመሰረት ድንጋይ ማኖራቸው ይታወሳል:: ህዝብ እንዲያውቅ የሚደረገው እንዲህ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል እንጂ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንዲያወቅ አይደረግም:: ውጤት ከሌለና ለታለመለት ዓላማ መዋል ካልቻሉ የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ ምን ትርጉም አለው? ለሚለው ጥያቄ ዶክተር ዮሐንስም የታሰበው ሰራ እስካልተሰራ ድረስ የመሰት ድንጋይ ማስቀመጥ ብቻ ትርጉም የሌለው መሆኑን ያምናሉ።
እርሳቸው እንዳሉት በሽርክና ወይንም በጋራ የሚሰሩ ሥራዎች መጓተት ያጋጥማቸዋል:: በሲኤምሲ አካባቢ የተጀመረውም እንዲህ አይነት ክፍተት አለበት:: ያም ሆኖ ግን ግንባታው ተጀምሯል:: የሮሃ የህክምና ማዕከልን ለየት የሚያደርገው የኢንቨስትመንት አቅሙና ከዚህ በፊት ያለው ተሞክሮ ቀድሞ ታይቶ በመሆኑ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ደብረብርሃን ከተማ ላይ ያቋቋመው የጠርሙስ ፋብሪካን ሰርቶ ያሳየ በመሆኑ እምነት ተጥሎበታል:: የተሰጠውን ቦታ አጥሮ ሊያስቀምጥ ሳይሆን ሊሰራበት መሆኑን ማረጋገጫው ደግሞ ወደ ሥራው ሊያስገቡት የሚያስችሉ የሥራ መሳሪያዎችን አስገብቶ ወደ ግንባታ መግባቱ ነው::
‹‹ብዙዎቻችን በተደጋጋሚ ሲነገር የሰማነውም፤ የምናውቀውም ስለሆቴልና ኮንፈረንስ ቱሪዝም ነው:: ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና ሆና ብዙ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሥብሰባዎችን እያካሄደች ሊጎበኙ የሚመጡ የተለያዩ ሀገሮችን ዜጎች እያስተናገደች ደረጃውን የጠበቀ የህክምና ተቋም የላትም:: ብዙ ጥቅም ማግኘት እየቻለችም አባክናለች›› በማለት ሀሳባቸውን ያካፈሉኝ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ አማካሪ ወይዘሮ ማህሌት ግርማ ናቸው። በከተማዋ ባልተሰሩ ዘርፎች ላይ በማተኮር በተለይም እንዲህ እንደ ጤና ቱሪዝም ያሉ ሥራዎች እንዲሰሩ በከተማ አስተዳደሩ ቁርጠኝነት ተይዟል:: ከእህትማማች ሀገሮች ጋር ቁርኝነት በመፍጠር ይሰራል::
በጤና ቱሪዝም የሚጠቀሙ ሀገሮች ተቋም ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በመሸጥ በኩልም በተለያዩ አጋጣሚዎች ተደራሽ ሲሆኑ ይስተዋላል:: ሮሃ የህክምና ተቋም ከሚገነባቸው አምስት ሆስፒታሎች አንዱን ከአንድ አመት በኋላ ሊያስረክበን ተዘጋጅቷል:: የታለመውን ዕቅድ ለማሳካት ራስን በማስተዋወቁ በኩል ስለተደረገው ዝግጅት ለወይዘሮ ማህሌት አንስቼላቸው መረጃ ትልቅ ኃይል መሆኑንና በዚህ በኩል ያለውን ውስኑነት በመቅረፍ ሥራዎች ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለመሥራት የከተማ አስተዳደሩ መነሳሳቱን ተናግረዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ የባህል የኪነጥበብ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፋይዛ መሐመድ፤ የህክምና ማዕከሉ ቢሮው ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ጋር ቀጥታ የሚዛመድ እንደሆነና ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ይገልጻሉ:: ትልቅ የቤት ሥራ መውሰዱንም ተናግረዋል:: የህክምና ተቋሙ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ ቢሮውም ቀድሞ ዝግጅት በማድረግ እኩል ሥራውን ይጀምራል የሚል እምነት አላቸው:: ተግባራዊ እንቅስቃሴው ሲጀመር ለህክምና የሚመጡት ሰዎች ሲመለሱ ያዩትንና የማረካቸውን ለሌሎች በመንገር የሚያስተዋውቁ አምባሳደሮች እንዲሆኑ ጭምር ቢሮው ይሰራል ብለዋል::
‹‹በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ልማት በመነቃቃት ላይ ይገኛል:: በቅርቡ ለህዝብ ክፍት የሆኑት እንደ እንጦጦ፣ ሸገር፣ አንድነትና ወዳጅነት ያሉ ፓርኮች ለከተማዋ ከፍተኛ መስህብ እየሆኑ በመጡበት በዚህ ወቅት የጤና ቱሪዝምን ለመገንባት ሥራ መጀመሩ ከተማዋ በቱሪዝም መዳረሻ ልትደርስ ያሰበችበትን ከፍታ የሚያረጋግጥ ተግባርና ያለውን ዕድል የሚያሰፋ ነው::›› ብለዋል:: ፕሮጀክቶች የሚጓተቱበት ጊዜ ሳይሆን ተጠናቅቀው ጥቅም የሚሰጡበት ጊዜ ላይ መሆኑንና ሮሃም በገባው ቃል አጠናቅቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል::
በ2020 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንደሀገር የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሮሃ የህክምና ተቋም ትልቅ ተስፏ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የሚጠበቅና የሚጨበጥ መሆኑን የግንባታ ሥራውን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አረጋግጠዋል:: በኃላፊነት እንደሚከታተሉትና በተያዘው ዕቅድ ካልሄደ ርምጃም እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል:: እርሳቸው እንደሌሎች ተናጋሪዎች ሁሉ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት የህክምና ተቋሙ እጅግ ወሳኝ ነው ሲሉ ተደምጠዋል:: በቱሪዝም ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች ቢሰሩም ቱሪስቶች ህክምና አናገኝም የሚለው ስጋታቸው ከፍተኛ በመሆኑ እንደሀገር ስጋቱን መቀነስ ይገባል::
ፕሮጀክቱ በሰባት ወር የምክክር ጊዜ ውስጥ እውን ሊሆን የቻለ በመሆኑ ግንባታውም ፈጥኖ ውጤቱ በተያዘው ዕቅድ እውን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013