
አብርሃም ተወልደ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በዚህ ሳምንት ከተፈጸሙ ሁነቶች መካከል አንዱ የአጼ ቴዎድሮስ ህልፈት ነው:: መቅደላ አምባ ላይ የዐፄ ቴዎድሮስ ሠራዊት እና በሎርድ ኔፒዬር የተመራው የእንግሊዝ ሠራዊት ጦርነት ገጥመው፣ ድሉም የእንግሊዞች ሆነ። ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ከመውደቅ ራሳቸውን ማጥፋትን መረጡ:: ሽጉጣቸውን ጠጥተው የሞቱትም ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ነበር። ቀብራቸው በመቅደላ መድኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ተከናውኗል።
መነሻ
የውስጡንም ሆነ የውጪውን አደጋ፤ የሚፋለሙትን መሳፍንትም ሆነ የ“ቱርክ”ን ከበባ በቅጡ ተረድቶ ለመቋቋም የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት ካሳ ኃይሉ ናቸው:: በ1847 “ዳግማዊ ቴዎድሮሰ” ተብለው ዙፋኑን ሲጨብጡ የዘመናዊት ኢትዮጵያን ልደት ያበሰሩ ተብለውም ይጠቀሳሉ:: ካሳ “ቴዎድሮስ” ለመሆን የበቁት በልዩ የግል ባህሪያቸው ነው:: ራሳቸውን ዐቢይ ተልዕኮ ሊፈጽሙ የታጩ አድርገው ማየታቸው፣ ወታደራዊ ችሎታቸው፣ ጀግንነታቸውና ደፋርነታቸው በተጨማሪም አዲስ ነገር ተቀባይነታቸው ነው ለእዚህ ያበቃቸው:: ከሽፍትነት ወደ ዐጼነት ራሳቸውን ማሸጋገር የቻሉም ይባላሉ:: በዘመነ መሳፍንት ተወልደው የዘመነ መሳፍንት እድሜን ለማሳጠር የበቁ ናቸው::
የቴዎድሮስ ትውልድ እና ዕድገታቸው ለኋላኛው የፖለቲካ ህይወታቸው አስተዋጽኦ አድርጓል:: ለስልጣን መቆናጠጫና ለዘመኑ ፖለቲካ መለማመጃ ትምህርት ቤት የሆናቸውን ቋራን (ምንም እንኳን ኋላ በራሳቸው ሃይል ቢያደላድሉትም) ከመነሻው ባለቤትነቱን ያወጁት የቤተ ዘመዱ ግዛት ስለሆነ ነበር::
በወቅቱ ከነበሩት የዘመነ መሳፍንት ተዋንያን አንዱ የደንቢያው ገዥ ደጃዝች ማሩ የካሳ ዘመድ ሲሆኑ፣ ቋራን ጨምሮ በየቦታው ተበታትነው የሚገኙት ግዛቶች በጥቅሉ “የማሩ ቀመስ” ተብለው ይታወቁ ነበር:: ደጃዝማች ማሩ በ1820 “በኮሶ በር ጦርነት” ላይ ሲወድቁ ግዛቱ ወደ ደጃዝማች ክንፉ ተላለፈ:: በጎንደር የተወለዱት እና አንዳንዴ ካሳ ማሩ እየተባሉ የሚጠሩት ካሳ ኃይሉም ወደ ቋራ የሄዱት ከዚሁ ከኮሶ በር ጦርነት በኋላ ነው::
ካሳ በቋራ በደጃዝማች ክንፉ ቤት አደገ:: በዚህን ጊዜ ግብጻች ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት በብርቱ ይፋለሙ ከነበሩት መሳፍንት አንዱ ደጃዝማች ክንፉ ነበሩ:: በ1829 “ወድከልተቡ” በተባለ ስፍራ በግብጽ ጦር ላይ ትልቅ ድል በመጎናጸፉቸውም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስመ ጥር ሆኖው ነበር:: የአባታቸው ልጅ ለሆኑት ካሳ ግን ብዙም ፍቅር አያሳዩዋቸውም ነበር:: የዚህም ምክንያት ክንፉ ካሳን የልጆቹ ጣውንት አድርጎ እንዳየው ይገመታል::
ክንፉ “የማሩ ቀመስ”ን ለልጆቹ ለማውረስ በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት ካሳን እንቅፋት ሆነው ስላዩዋቸው በክፉ አይን ተመለከቷቸው:: የማታ ማታ ግን ያ ሁሉ ልፋትና ጠላትነት ከንቱ ሆነ:: ክንፉ እ.አ.አ በ1939 ሲሞቱ “የማሩ ቀመስ” ለክንፉ ለልጆችም ሆነ ለካሳ አልሆነም:: የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን ወረሱት::
ያኔ ነው ካሳም በስርዓት ያጡትን በጉልበት ለማግኘት የሽፍትነትን ጉዳና የመረጡት፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሌሎች እንደሳቸው ያኮረፉ ባለሟሎችን እና ተራ ቀማኞችን እየመሩ በቋራ በረሃ መንቀሳቀስ ጀመሩ::
የካሳ ስብዕና የታነጸው በዚሁ ሽፍትነት ዘመናቸው ነው ቢባል እምብባዛም ከእውነት የራቀ አይሆንም:: ዘላቂ የሆኑት የካሳ ባህሪያት ቅርጽ የያዙት በዚሁ ዘመን ነበር:: ከእነዚህም ባህሪያት አንዱ ምቾት እና ብልጭልጭ ነገር አለመውደድ ነው:: ካሳ በኋላም ቴዎድሮስ የወታደሮቹን ኑሮ የሚጋራ መሪ ነበር:: እንደ ገበሬ አርሶ እና ዘርቶ እንደ ወታደር ይዋጋ ነበር:: ሌላው ባህሪው ደግሞ ለፍትህና እኩልነት መቆርቆር ነው::
እንደ ዝነኛው የእንግሊዝ ሽፍታ ሮቢን ሁድ ካሳም ከነጋዴ የዘረፉትን ገንዘብ ለገበሬዎች ማረሻ መግዢያ ለግሰዋል:: በኋላ ክፉ መዘዝ ያመጣባቸውን የቤተ ክህነትን መሬት ወርሰው ወታደሮቹን ለመቀለብ መሞከራቸውም የዚሁ የማደላደል ስሜት አንዱ ነጻብራቅ ነው:: ካሳ በሽፍትነት ዘመናቸው ነው ከግብጾች ጋርም መጋጨት የጀመሩት:: ቱርክ ተብሎ ከሚጠራቸው ጋር ያደረጉት የእድሜ ልክ ፍልሚያ እና ኢየሩሳሌምን ከነሱ ነጻ አወጣለሁ የሚለው ህልማቸውም የተጸነሰው እዚሁ ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ ነው::
የካሳ ስም እና ዝና በቋራ አካባቢ እየገነነ ሲሄድ ባለስልጣናቱ ራስ ዓሊን እና እናቱን እቴጌ መነንን መሳብ ጀመሩ:: ከሃይል ዘዴ ይሻላል ብለውም በጦር ያገኙትን የቋራ ግዛት መረቁላቸው:: በጋብቻ ለማሰርም የዓሊን ልጅ ተዋበችን ዳሩላቸው:: ካሳ ለተዋበች ያላቸው ፍቅር ቋሚ የሆነውን ያህል ከአባቷ እና እናቷ ጋር ያደረጉት እርቅ ግን ውሎ አላደረም::
የዜና መዋዕል ጸሐፊው ዘነብ አንደሚተርክልን በየጁ ቤተ መንግስት በደል እና ንቅት ቢበዛበት ካሳ እንደገና የሽፍትነት ኑሮውን ቀጠለ:: ከሁሉም ከሁሉም ተረት ሆኖ የቀረው “ይኸን የኮሶ ሻጭ ልጅ አንጠልጥዬ እመጣለሁ” ብሎ የፎከረውና ተማርኮ የፉከራ ቃሉን በኮሶ እንዲውጥ የተገደደው ደጃዝማች ወንድይራድ ነበር:: ምርኮነቱ ለንግስቲቱ ለመነንም አልቀረላትም:: ጦሯ በካሳ ተበትኖ ንግስቲቱም ለጥቂት ቀናት የካሳ ምርኮኛ ሆና ነበር::
እንደ ዘመነ መሳፍንት የፖለቲካ ባህል ቢሆን ኖሮ ቴዎድሮስ የሰሜን ኢትዮጵያ መሳፍንትን አንድ በአንድ ድል አድርገው ዘውድ ሲቀዳጁም “የፈለኩት ተሟላልኝ” ብለው በተዝናኑ ነበር:: እሳቸው ግን በዚህ በቃኝ አላሉም:: ፊታቸውን ወደ ወሎ እና ሸዋ አዞሩ:: በዚህ ድርጊታቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ አድማስ ተከልሎ የነበረውን የዘመነ መሳፍንት ፖለቲካ እንደማይታጠፍ አድርገው አሰፉት::
የቴዎድሮስ የሸዋ ዘመቻ አንዱ እና ትልቁ ውጤት ያንን የጎንደር ፖለቲካ ገሸሽ ብሎ ወደነበረው ግዛት በማያሻማ ሁኔታ ወደ ማዕከል ጎትቶ ማስገባቱ ነው:: ይህ ሂደት ቀጥሎና አድጎ ሚኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሲሆን፣ ሸዋ ከድንበር ግዛትነት ወደ ማዕከልነት ልትሸጋገር በቃች:: ቴዎድሮስ ከሸዋ በፊት ወሎንም አስገብሯል::
ቴዎድሮስና ዘመናዊ ስልጣኔ
ፕሮፌሰር ዶናልድ ክራሚ የቴዎድሮስ ህይወት እና ገጽ ባህሪይን ሲገመግሙ “ ማብራራቱ እና መተንተኑ ቢጎለውም የዘመናዊ ስልጣኔ ሀሳብ የገባው የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ንጉስ ነበር” በማለት ጽፈዋል:: ይህ ማለት ከቴዎድሮስ በፊት የነበሩት ነገስታት እና መሳፍንት አንዳንድ የዘመናዊ አሰራር ሀሳቦች አልነበራቸውም ማለት አይደለም:: እንደ ቴዎድሮስ ግን በስፋት እና ያለመታከት ሐሳቡን ግቡ ለማድረስ የጣረ ንጉስ አልነበረም:: ይሁን እንጂ ቴዎድሮስ አገሪቷን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት የሚያስችለውን ንድፍ በደንብ ካለመቅረጹም ሌላ በሚወስዳቸው ተቃራኒ ርምጃዎች ምክንያት ከዓላማው ተደናቅፏል::
የሚያደርጓቸውም የለውጥ ሙከራዎች የዳበሳ እንጂ ሁለገብ የሆነ የለውጥ ፕሮግራም የተከተሉ አልነበሩም:: ከዘመነ መሳፍንት የወረሷቸው ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅሮች ብዙም ሊያራምዳቸው አልቻለም:: ስለሆነም የጀመሯቸው ወታደራዊና አስተዳደራዊ ለውጦች የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ መሰረት ስላልነበራቸው አየር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ:: የአውሮፓውያንን የቴክኒክ እርዳታ ለማግኘት አጥበቀው ቢማጸኑም የሚሰማቸው አላገኙም:: በመጨረሻም ቴዎድሮስ ብቸኛ እና ግራ የተጋቡ የለውጥ ሐዋሪያ ሆነው ቀሩ::
በአደራጃጀት በኩል ቴዎድሮስ ለማምጣት የፈለጉት ዐብይ ለውጥ ተጠሪነታቸው ለመሳፍንቱ የነበረውን የተበታተኑትን ሰራዊቶች ባንድ አገር አቀፍ ብሔራዊ ሰራዊት መተካት ነበር:: በዚህም መሰረት ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ ወታደሮች በአንድ ሬጀመንት ተሰልፈው እንዲዋጉ በማድረግ ከጠባብ የአካባቢ ስሜት ተላቀው ሰፋ ያለ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞከረዋል:: የአስር አለቃ፣ የአምሳ አለቃ፣ የሺ አለቃ፣ የሚባሉ አዳዲስ የማዕረግ ስሞችን በመፍጠር እስካለንበት ጊዜ ድረስ በግልጋሎት የቆየውን የስልጣን ተዋረድ መስርተዋል::
ሌላው ቴዎድሮስ ለውጥ የመጣበት ምክንያት የባሪያ ንግድን የተመለከተ ነበር:: ከሸዋ ዘመቻ መለስ በጎጃም ሲያልፉ ባሶ ገቢያ የተኮለኮሉትን ባርያዎች አይተው ሁሉም አርነት እንዲያገኙ ካደረጉ በኋላ ቅጽበታዊ ውሳኔ በመስጠት ባላቸው ልዩ ችሎታ ሴት እና ወንድ እያፈጣጠሙ አጋብተዋቸዋል:: ይህ መላ በግዛቱ የባሪያ ንግድ መከልከሉን የደነገገበት ዐዋጅም ነበር:: በቃሉ (ወሎ) ወታደሮች በምርኮ ያገኟቸውን ባሮች እንዳይሸጡ አግደዋቸዋል::
ዘመናዊ ስልጣኔን ወደ አገሩ ማስገባት እንደሚሻ ማንኛውም መሪ ቴዎድሮስም ስር ነቀል የሆኑ ለውጦች ለማምጣት ደልዳላ የፋይናንስ መሰረት እንደሚያስፈልግ ይገነዛበሉ:: ይህንን አደርጋለሁ በማለትም ነው ከቤተ ክህነት ጋር መጋጨት ውስጥ የገቡት:: ይህም ግጭት የፍጻሜያቸው መጀመሪያ ሆነ:: ቴዎድሮስ ከጥንቱም ለካህናት ብዙ ፍቅር አልነበራቸውም:: “አረግራጊ፣ አቴና ወጊ፣ ወገቡን ሰባቂ” እያሉ ይዘልፋቸውም እንደነበርም ይገለጻል::
ቴዎድሮስ ቤተ መንግስትን ብቻ ሳይሆን የቤተ ክህነትንም አሀዳዊነት ለማረጋገጥ ታጥቀው የተነሱ መሪ ነበሩ:: ከዓላማዎቻቸው አንዱ ለሁለት መቶ አመት ዓመታት ያህል የተለያዩ ችግሮችን እየፈጠረ የነበረውን የቤተክህነት ጉዳይ በማስተካከል ለቤተ መንግስቱ አጋር የምትሆን አንድ ቤተ ክህነት ማቋቋም ነበር::
ከዚያ በኋላ ቴዎድሮስ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትን በመቀበል በአቡነ ሰላማ እጅ በጦር ለያዙት ዙፋን ቡራኬውን አግኝተው ጥቂት ዓመታት በስምምነት ቆዩ:: ይህ ትብብር መንፈስ ግን ዘለቄታ አላገኘም፤ ንጉሱ የህዝቡ ተቀባይነት እንደጠበቁት ሊያገኙ አልቻሉም::
በንጉሱ እና በካህናቱ መካከል ቅራኔ እየተፈጠረ መጣ፤ በመሬት ጉዳይ ዋና ግጭት ተከሰተ:: የካህናቱን ተቃውሞ ለአራት ዓመታት ከተመለከቱ በኋላ ንጉስ ካህናቱ ከሚያስፈልጓቸው በላይ ነው ብለው የገመቱትን መሬት ለገባሮች አከፋፈሉ::
የቴዎድሮስ ፍጻሜ
የንጉሱ የመጨረሻ ዓመታት በውስጥም ሆነ በውጭ ጽልመትን የተላበሱ ነበሩ:: በውስጥ ግዛት ከግዛት ሳይለይ አጠቃላይ አመጽ ተቀሰቀሰባቸው:: በውጭም ቢሆን እርዱኝ ብለው እጃቸውን ከዘረጉላቸው አውሮፓውያን ያገኙት መልስ ዝምታ ወይም ንቀት ብቻ ነበር::
እሳቸውም ከጭንቀት እና ከመከፋት የተነሳ ጭካኔን መፍትሔ አድርገው ያዙት:: ጠላታቸውን እና ወዳጃቸውን እንኳን መለየት አልቻሉም:: በሁሉም ላይ የቁጣቸውን መቅሰፍት እኩል አወረዱባቸው:: ይህም ሁኔታውን አባባሰው:: በውስጥ ጠላቶቻቸውን ይበልጥ አበራከተባቸው፤ በውጭ ደግሞ ለፍቅርና ለወዳጅነት ደብዳቤዎቹ ደንታ ያልሰጡት እንግሊዞች ተነሱበት:: ሊረዱት ያልተዘጋጁት ሊያጠፉት ተነሱ:: በነሱ ስሌት አውሮፓውያንን ለማሰር የሚጋበዝ የአፍሪካ መሪ በቸልታ ሊታለፍ አይገባውም::
በታሪክ እንደሚታወቀው ቴዎድሮስ በ1847 ንጉሰ ነገስት ከሆኑ ጀምሮ አመጽ ተለይቷቸው አያውቅም:: እስከ ዘመናቸው ፍጻሜያቸውም አንዱን አመጽ አብርደው ሳይጨርሱ ሌላ እየተነሳባቸው ካንዱ ግዛት ወደ ሌላው እንደተንቆራጠጡ ነው ያሳለፉት:: በጎጃም ተድላ ጓሉ የጎን ውጋት ሆኑባቸው። ወደ መናገሻ ከተማው ቀረበ ሲል ደግሞ የወልቃይቱ ጥሶ ጎበዜ የንጉሱን ስልጣን እያዳከመ ይግረምህ ብሎ አንዴ ጎንደር ከተማን ለመያዝ በቃ::
የፖለቲካ ዕድሉ እንዲህ አልሰምርላቸው ሲል እና ቁጣቸው ቅጥ እያጣ ሲመጣ የቴዎድሮስ ሰራዊት እየመነመነ ሄደ:: በ1858 ገደማ ሰራዊት እየከዳው ሲሄድ ቀድሞ በስድሳ ሺህ ይገመት የነበረው ጦሩ ወደ አስር ሺህ አሽቆለቆለ:: የንጉሱም የመንቀሳቀሻ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቶ በደብረ ታቦርና በመቅደላ መስመር ተወሰነ:: ይህም እየቀነሰ መጥቶ በደብረ ታቦርና በመቅደላ መስመር ተወሰነ::
ይህም ቢሆን በአማጽያን ጥላ ስር ወድቆ በ1860 መጀመሪያ ላይ ንጉሱ መቅደላ ላይ ለመመሸግ ተገደዱ:: ይህ ሽሽት የዓላማው መክሸፍ የመጨረሻው ምልክት ነበር:: ኢትዮጵያን አንድ አደርጋለሁ ብሎ የተነሳው ጎበዝ ባንድ አምባ ተከተተ:: በመጨረሻ ለእንግሊዙ ጦር መሪ ለሮበርት ናፒየር በጻፈው ደብዳቤ (የኑዛዜ ደብዳቤ) ማለት ይቻላል መቅደላን የአረማውያን ስፍራ ብለው ገልጸውታል::
የቴዎድሮስ ህይወት በሶስት ስፍራዎች ይጠቃለላል ማለት ይቻላል:: እነሱም ቋራ፣ ጋፋት እና መቅደላ ናቸው:: የመጀመሪያው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ መቆናጠጫው ሁለተኛው የዘመናዊ ስልጣኔ መዲናው፣ ሶስተኛው የመጨረሻ ምሽጉ ሆነ:: በእዚህ ምሽጉ እያለም ነው ህይወቱ ያለፈው::
ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም ሦስት ሰዓት ላይ እንግሊዞች በመቅደላ ምሽግ ላይ የመጨረሻ ጥቃት አደረሱ። ንጉሱ፣ የሃይል ሚዛኑ ወደ እንግሊዞቹ ሙሉ በሙሉ አንዳጋደለ ስለተረዱ ለወታደሮቻቸው “ተፈጽሟል! በእርሱ (በአንግሊዙ የጦር አዛዥ) እጅ ከምወድቅ ብሞት ይሻለኛል” ብለው ከአጠገባቸው ዞር አሉ:: ወዲያውም ከንግስት ቪክቶሪያ የተላከላቸውን ሽጉጥ መዘው በጀግንነት ራሳቸውን በማጥፋት ይህችን አለም በጀግንነት ተሰናበቱ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013