ወሃቤ ሰላም ዋለልኝ ሲሳይ
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ ወቅቱ ያመጣው ኮሮና ቫይረስ አብሮ ይዞት የመጣውና የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ በህክምና ባለሞያዎች የተሰጠው ምክርና በመንግስትም የተላለፈው መመሪያ ብዙ ተረስተው የነበሩ ያለባበስና የሰላምታ አሰጣጥ ባህሎቻችንን እንዳስታውስ ስላደረገኝ ይህችን ማስታወሻ ለማቅረብ አሰብኩኝ ፤
የኮረና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከል ያስችላሉ ተብለው ከተሰጡት የጥንቃቄ ስልቶችና መመሪያዎች በእጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥና በቅርብ ተጠጋግቶ መቀመጥ ወይም መቆም በሽታው ከሰው ወደ ሰው ከሚተላለፍባቸው መንገዶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እጅ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥና ተጠጋግቶ መቀመጥም ሆነ መቆም እንዲቀር ፤ እንዲሁም እጅን በየጊዜው በሳሙና መታጠብ በሽታውን ለመከላከል ይረዳል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎችና ምክሮች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የጤና ባለሞያዎችና ከመንግስትም በተደጋጋሚ በመሰጠት ላይ ሲሆኑ ከዚህ ላይ በጣም የገረመኝና ይህን ማስታወሻ ለማቅረብ የገፋፋኝም አንዳንድ ወገኖቻችን የእጅ ሰላምታ መለዋወጥን ለማቆም ሲቸገሩ ማየቴ ነው ።
በእጅ መጨባበጥ የሚደረግ ሰላምታ ያልነበረና ከምእራቡ ዓለም የወረስነውን የእጅ ሰላምታ አሰጣጥ ከዛሬው 50 እና 60 ዓመት በፊት ከመሃል ከተማችን ጀምሮ ወደ ተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በገባበት ወይም በተ ጀመረበት ጊዜ አባቶቻችን ይህን ባህላችን ያልሆነ የእጅ ሰላምታ አሰጣጥ አንቀበልም ብለው ሲከላከሉ እንደነበር በልጅነት እድሜዬ በአይኔ የተመለከትኩትና የቅርብ ጊዜ ትዝታዬ ነው አሁን ደግሞ ይህንኑ ቀደም ሲል ባህላችን ያልነበረውንና በስንት መከራ የተቀበልነውን የእጅ ሰላምታ አሰጣጥ ጤናን ያቃውሳል ህይወትንም ያሳጣል እየተባለ እየተነገረንም ለማቋረጥ ስንቸገር መታየቱ የሚገርም ነው።
የእጅ ሰላምታ አሰጣጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መቼ እንደገባ/ እንደተጀመረ እኔ አላውቅም ጥናትም አላደረክሁም። አንዳንድ ምንጮችና የእድሜ ባለጸጋ የሆኑ አባቶች እንደሚያስረዱት ከሆነ የእጅ ሰላምታ አሰጣጥ ወደአገራችን የገባው ከኢጣሊያ ወረራ ጋር ተያይዞ በጣሊያኖች አማካይነት እንደነበር ሲናገሩ አድምጫለሁ። እኔ ተወልጄ ያደግኩት በሰሜን ምእራብ የሀገሪቱ ክፍል በወቅቱ የአውራጃ አስተዳደር ዋና ከተማ በነበረ አካባቢ ሲሆን በህጻንነት እድሜዬ ማለትም በ40ዎቹ መጨረሻና በ50ዎቹ መጀመሪያ ላይ በጆሮዬ እንደሰማሁትና በዓይኔም እንዳየሁት በወቅቱ የነበረው የሰላምታ አሰጣጥ በእጅ በመጨባበጥ አልነበረም። በምትኩ ተስተካክሎ በመቆም ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ ወይም እንደምን አደራችሁ በማለትና እጅ በመንሳት ሲሆን ሰላምታ የቀረበለት/ላት ወይም የቀረበላቸው ሰዎች ደግሞ ተቀምጠው ከነበረ ከተቀመጡበት በመነሳት፤ ቁመው ከነበረም በለውጡ አንገታቸውን ዘንበል በማድረግ አብሮ ይስጥልን እግዚአብሔር ይመስገን እንደምን ውላችኋል ወይም አድራችኋል በማለት ነበር አጸፋዊ ሰላምታ የሚሰጡት እንጂ እጅ በመጨባበጥ የሚደረግ የሰላምታ ልውውጥ ፈጽሞ አይታወቅም ነበር ፤ እንዲያውም አንዳንድ ግለሰቦች ለትምህርት ውጭ አገር ቆይተው ወደ አካባቢው ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ ወይም አንዳንድ የመንግስት ሠራተኞች ከማእከል / ከአዲስ አበባ ወደ አካባቢው በስራ ተመድበው በሚመጡበት ጊዜ የእጅ ሰላምታ ለመስጠት እጃቸውን ሲዘረጉ ህብረተሰቡ ምን ባለጌ ሰው ነው፤ እንዴት እጅህን ልጨብጥህ ይለኛል እያለ ያሳፍራቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፤ በሌሎች የሐገሪቱ ክፍሎች የነበረው የሰላምታ ልውውጥም የሚገለጹበት ቋንቋዎች እንደ ብሔረሰቦቹ ቋንቋ ከመለየቱ በስተቀር የሰላምታ አሰጣጡ ስርዓት ግን ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ እንደነበር ለመረዳት ችያለሁ።
ሌላው ከሰላምታ አሰጣጥ ጋር አብሮ ሊታወስ የሚገባው
1. ሰላምታ የሚሰጠው ለባለስልጣኖችና በእድሜ ለገፉ ሰዎች ከሆነ ለክብር ሲባል ሰላምታ የሚሰጠው ሰው የለበሰውን ጋቢ በትምህርተ መስቀል አጣጥሎ ለብሶ ወይም ቀኝ እጁን አውጥቶ ጋቢውን በመልበስ ሲሆን በእድሜ ተመጣጣኝ ለሆነ ሰው ሰላምታ በሚሰጥበት ጊዜ ግን ምንም ልዩ አለባበስ አይጠይቅም ነበር፤
2. ማንኛውም ሰው ፈረስ ወይም በቅሎ ጋልቦ በሚሄድበት ጊዜ እሱ ከሚሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒው ወይም በተመሳሳይ አቅጣጫ የሚጓዝ መንገደኛ በሚያጋጥመው ጊዜ ሰውየውን ቢያውቀውም ባያውቀውም ከፈረሱ ወይም ከበቅሎው ላይ ወርዶ ሰላምታ መስጠት ግዴታው ነው። ነገር ግን ገና ከመውረዱ በፊት ቀድሞ በእግሩ የሚጓዘው መንገደኛ ከፈረሱ ወይም ከበቅሎው ላይ እንዳይወርድ ከተከላከለው እና ከፈቀደለት ላይወርድ ይችላል ፤ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚጓዙት ሁሉም መንገደኞች በቅሎ ወይም ፈረስ የጋለቡ ከሆኑ ቢተዋወቁም ባይተዋወቁም ሁለቱም ከፈረስ ላይ ወርደው ሰላምታ ይሰጣጣሉ እንጂ በፈረስ ወይም በበቅሎ ላይ እንዳሉ ሰላምታ ተሰጣጥቶ መተላለፍ በማህበራዊ ህጉ የተፈቀደ አልነበረም፤
3. ማንኛውም ሰው ሌላ ሰው በሚያገኝበት ወይም በምታገኝበት ጊዜ ቢያውቀውም /ባያውቀውም/ ባታውቀውም እንዴት ዋልክ ወይም ዋላችሁ ብሎ/ብላ ሰላምታ ማቅረብና ሰላምታ የቀረበለት/ላት ሰውም እግዚአብሔር ይመስገን ወይም አልሃ ምዲልላሂ ደህና ነኝ ብሎ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረብ በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያለውና የሚከበር ማህበራዊ ህግ ነበር። ይህን ማህበራዊ ህግ በመተላለፍ ሰላምታ ሳይሰጥ የሚያልፍ ግለሰብ ቢኖር እንደ እንስሳ የሚቆጠርና ለአምላክ ሊቀርብ የሚገባውን ምስጋና እንዳስቀረ ተቆጥሮ በህብረተሰቡ ዘንድ ወቀሳ ይደርስበት ነበር።
በእጅ ሰላምታ መለዋወጥ መጀመራችን ያመጣልን ነገር የነበረንን የሰላምታ አሰጣጥ ስርዓት መለወጥ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ የሰላምታ መለዋወጥ ወቅት በሰላም አውሎ ወይም አሳድሮ በሰላም ላገናኘን አምላካችን እናቀርበው የነበረውን ምስጋና ሳይቀር እንድንረሳ እና በምትኩ ደህና ወይም ሃይ መባባልን የሰላምታ አሰጣጥ ባህላችን አድርገን እንድንለምደው ጭምር ነበር ያደረገን። ከዚህም ጋር አብሮ ቢታወስ ጉዳት የለውም ብየ ያሰብኩት ሌላ የነበረን ባህል ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ወደ ተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ መንገደኞች በመስቀለኛ መንገድ ላይ በሚገናኙበት ጊዜ በሁለቱም አቅጣጫ የሚሄዱት መንገደኞች መንገዱን አቋርጠው ሳያልፉ ይቆሙና መጀመሪያ እናንተ አቋርጣችሁ እለፉ በመባባል ይገባበዙና አንደኛው ወገን ግብዣውን ተቀብሎ መንገዱን አቋርጦ ካለፈ በኋላ ተመሰጋግነው ይለያዩ እና መንገዳቸውን ይቀጥሉ ነበር።
እዚህ ላይ የኮረና ቫይረስ መከሰትን አስመልክቶ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ያስችላሉ ተብለው ከሚሰጡት ምክሮችና ማስጠንቀቂያዎች በመነሳት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰጡት አንዳንድ ማብራሪያዎች፤ የኮሮና በሽታ፤ የነበሩንን ኃይማኖታዊና ማህበራዊ እሴቶቻችንን የበለጠ ልናከብራቸውና ልንከተላቸው እንደሚገባ የሚያሳይ ነው።
ማጠቃለያ
1. እኔ_ይህ የኮሮና ቫይረስ በዘመኑ ትውልድ ከኃይማኖት ህግጋት በማፈንገጡ ፤ ሃሰት በመዳፈሩና ፍርድ በማዛባቱ ከፈጣሪ የታዘዘ መቅሰፍት ነው የሚለውን የኃይማኖት አባቶች ምክርና አስተምህሮ እቀበላለሁ፤ ምክንያቱም በየአጋጣሚው የምመለከተው የህብረተሰባችን ተግባር ከህሊና ዳኝነት የራቀና ገንዘብን በማምለክ ላይ ብቻ የተመሰረተ እንደሆነ ስለምረዳ ነው ስለሆነም ለህብረተሰባችን የምሰጠው ማሳሰቢያ ሁላችንም ገንዘብን ከማምለክ አባዜ ወጥተን የአባቶቻችን የማይተኩ ጥሩ ማህበራዊ እሴቶችን እያስታወስን በህሊና ዳኝነት እንድንመራና ይህን የታዘዘ መቅሰፍት ለማለፍ እንድንችል ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡንን ምክሮችና ትእዛዞች አክብረን ተግባራዊ እናድርግ ፤
2. የነበሩን ማህበራዊ እሴቶች ከዚህ በላይ ያቀረብኳቸው ብቻ አይደሉም፤ በሁሉም የሐገሪቱ ክልሎችና ብሔረሰቦች ዘንድ ተግባራዊ ይሆኑ የነበሩ በጣም ጠቃሚና በርካታ ማህበራዊ ህጎች እንደነበሩ ይታወቃል ፤ ይሁን እንጂ ሁሉንም ዘርዝሮ ለመጨረስ በዚህ አነስተኛ ማስታወሻ ስለማይቻል ለማሳያ ያህል ከላይ የተጠቀሱትን ብቻ ያቀረብኩ ሲሆን ከላይ ከተጠቀስኳቸው እሴቶቻችን መካከል አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ የሚኖራቸው ተፈላጊነትና ጠቃሚነት ያን ያህል እንደማይሆን እረዳለሁ፤ ነገር ግን ከላይ ከተጠቀሱትና ከነበሩን ማህበራዊ እሴቶቻችን ውስጥ በተለይ፤ ህግና ህጋዊነትን ተከትሎ ስራን ማከናወን፤ ከአድልዎ የጸዳና በእውነት ላይ ብቻ የተመሠረተ የሽምግልና ዳኝነት መስጠት፤ በጉቦ፤ በሌላ ጥቅማጥቅም ወይም ማህበራዊ ግንኙነት ተደልሎ ፍርድ አለማዛባት ፤አንድ ወገን ሲቸገር ችግሩን እንደጋራ ችግር በመቁጠር ተረዳድቶ ችግሩን ማስወገድ እንጂ በወገን ችግር ለመክበር አለመፈለግ፤ ትንሹ ትልቁን ማክበር፤ በሃሰት አለመመስከር፤ በመንግስትና በህዝብ የተሰጠን አደራ ከግል ጥቅም አስበልጦ ማየት፤ አደራን በአግባቡ መወጣት፤ ሌባንና ሌብነትን እጅግ አድርጎ መፀየፍ፤ የሚሉትና የመሳሰሉት በጣም ጠቃሚና አስፈላጊ የነበሩት ማህበራዊ ህጎቻችን ቀስ በቀስ ተሸርሽረው እየጠፉና እያጣናቸው ስለሆነ ሁላችንም በጥሞና ብናስብባቸውና የህይወታችን መመሪያ ብናደርጋቸው የጋራ ተጠቃሚ ያደርጉናል የሚል እምነት አለኝ ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013