ፍሬህይወት አወቀ
በቀደመው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ተካትቶ ይሰጥ የነበረው የእጅ ሥራ ትምህርት ለበርካታ ተማሪዎች የእጅ ሥራ ሞያን እንዲለምዱ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው የእጅ ሥራ ትምህርት ተምረው ቤታቸውን ከማስጌጥ ባለፈ የእጅ ሥራዎችን ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን የቻሉ በርካቶች ናቸው፡፡ በወቅቱ የእጅ ሥራ ክፍለጊዜን በጉጉት ይጠብቁና ይናፍቁ የነበሩ ተማሪዎች ዛሬም ድረስ በዘርፉ ተሰማርተው እየሰሩ ተጠቃሚ ሆነዋል።
በወቅቱ እንደ አንድ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተመድቦለት ይሰጥ የነበረው የእጅ ሥራ ትምህርት የኪሮሽ ሥራ፣ የጥልፍ ሥራ፣ የሸክላ ሥራና የቅርጻ ቅርጾች ስራ ውጤቶች የሚታይበት ነበር፡፡ በመሆኑም ወቅቱ አጠቃላይ ሀገር በቀል የሆነው የእደ ጥበብ ዘርፍ ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ለአብዛኞቹ ተማሪዎች በውስጣቸው የነበረውን ተሰጥኦ አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ አድርጓል፡፡ በዚህም የገቢ ምንጭ ከማግኘት ባለፈ የእደጥበብ ዘርፉ ለትውልድ መተላለፍ እንዲችልና እንዳይጠፋ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ ያሉ በርካታ የእጅ ሥራ ባለሙያዎች አሉ፡፡
‹‹ከልጅነት ጀምሮ ያደግኩበት የእጅ ሥራ ዛሬም ድረስ አብሮኝ አለ›› የሚሉት ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ሀይሌ በቀድሞው የትምህርት ሥርት የእጅ ሥራ ተምረው ያለፉ የ68 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ ተወልደው ባደጉበት አዳማ ከተማ የአስር ልጆች እናት ሆነዋል፡፡ የእጅ ሥራ ልምድ ከልጅነታቸው ጀምረው እየሰሩ የመጡት ሥራ ቢሆንም በባልትና ሥራውም ኑሯቸውን ይመራሉ፡፡ በባልትና ሥራቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንደ ብስኩትና ኩኪስ የመሳሰሉ ደረቅ ምግቦችን በማዘጋጀት ለሱፐርማርኬት ያቀርባሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከልጅነታቸው ጀምረው የሚያውቁትን የእጅ ሥራ በመስራት ኑሯቸውን ይደጉማሉ፡፡ ለአስሩም ልጆቻቸው የእጅ ሥራውንም ሆነ ባልትና ዝግጅቱን በማስተማር አብረዋቸው እንዲሰሩ አድርገዋል፡፡ የባልትና በተለይም የኩኪስ ሥራውን ለሴት ልጆቻቸው አከፋፍለው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እርሳቸውም ከልጅነት እስከ ዕውቀት አብሯቸው የኖረውን የእጅ ሥራ ሰርተው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ ወልደው በሚተኙበት ወቅት በርካታ የእጅ ሥራዎችን በመስራት የሚያሳልፉ መሆኑን ያስታወሱት ወይዘሮዋ፤ የእጅ ሙያ ሁልጊዜም አብሮን የሚኖር በመሆኑ በፈለግነው ጊዜ ልንጠቀምበት የሚቻል ነው ይላሉ፡፡
ከሚሰሯቸው የእጅ ሥራዎች መካከልም ቦርሳ፣ ሹራብ፣ ቀሚስ፣ ቀለል ያሉ ቲሸርቶችና የተለያዩ የአልጋ ልብስና መጋረጃዎች እንዲሁም ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ ቁጥሮች የተጠለፉበት ጌጦች ይገኙበታል፡፡ ለሥራው የሚያስፈልጋቸው ጥራት ያለው ክር እንደመሆኑ ክሩን ማግኘት አስቸጋሪ ስለሚሆን የአብዛኛው አልባሳት ዋጋ ውድ ነው፡፡ ለዋጋው ውድነት ከክሩ መወደድና መጥፋ በተጨማሪም በእጅ የሚሰሩ አልባሳት ረዘም ያለ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቁ ቢሆኑም አልባሳቱ እጅግ ያማሩና ውበት ያላቸው ናቸው፡፡
ትላልቅ አልባሳት በተለይም የአልጋ ልብስና የአዋቂ ሰው የሚሰሩ ልብሶች ከአንድ ወር የበለጠ ጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ በተመሳሳይ የልጆች ካልሲ፣ ኮፍያ፣ ሹራብና የአንገት ልብስ አይነት ትናንሽ አልባሳት ደግሞ የሳምንት ጊዜን ይወስዳሉ፡፡ ነገር ግን ፋብሪካ በሰዓት ብቻ በርካታ አልባሳትን ያመርታል፡፡ ሥራው ረዘም ላለ ጊዜ አይንን የሚይዝ እና የክሩ ብናኝ ለጤና አስቸጋሪ በመሆኑ መነጽር መጠቀም መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ የእጅ ሥራዎቻቸው ወደ ገበያው በስፋት መግባት ባይችልም አንድ ጊዜ የሰሩላቸው ሰዎች ተመላልሰው ይገዟቸዋል፤ ለሌሎችም ያስተዋውቁላቸዋል፡፡
ደስ ብሏቸው የሚሰሩት የእጅ ሥራ ለልጆቻቸው ያስተማሩ ከመሆኑም በላይ ፍላጎት ላለው ለማንኛውም ሰው የማስተማር ፍላጎት አላቸው፡፡ ምክንያቱም የእጅ ሙያ ያለው ሰው በልቶ ማደር ይችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ እርሳቸውም ከወላጆቻቸው የወረሱት እና በትምህርት ቤት የእጅ ሥራ ክፍለ ጊዜ ያዳበሩት መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ትምህርት ቤት የሰሩት የእጅ ሥራ በወላጆች ቀን በጨረታ በውደ ዋጋ ይሸጥ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
‹‹ማንኛውም ሰው ስልጠናውን ወስዶ ሙያውን ገንዘብ ማድረግ ከቻለ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በሀገሪቱ ያለው የሥራ አጥ ቁጥርም ይቀንሳል፡፡ በዚህም የሀገር ኢኮኖሚ ይሻሻላል›› የሚሉት ወይዘሮዋ ማንኛውም ሰው በተለያየ ሞያ ተሳትፎ ለሀገር እድገት የራሱን አስተዋጽኦ ቢያበረክት መልካም ነው፡፡ የዕውቀት ትንሽ የለውም ፡፡ ሁሉም ሰው ሥራ ሳይንቅ ዕውቀት ከቀሰመና ተሳታፊ ከሆነ ችግር ከሀገራችን ይጠፋል በማለት ለሥራ ያላቸውን ፍቅር አካፍለውናል፡፡
እርሳቸውም ያላቸውን ሞያ ለልጆቻቸው በማስተማራቸው ለሀገር ሸክማ ሳይሆኑ እራሳቸውን ማስተዳደር እንደቻሉ በምሳሌነት ተናግረው፤ ሁሉም ሰው ልጆቹን የተለያየ እውቀት እንዲያገኝ ዕውቀቱንም ወደ ሥራ መቀየር እንዲችሉ አቅጣጫ ማሳየት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በቀጣይም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ ቢያገኙ ዘርፉን ከዚህ በበለጠ የማስፋትና በተለይም የእጅ ሥራውን ለትውልድ የማስተላለፍ ፍላጎት አላቸው፡፡ እኛም ፍላጎታቸው እንዲሞላ ተመኘን ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 8/2013