አስናቀ ፀጋዬ
ወጣቶች የራሳቸውን ቢዝነስ አቋቁመው ኑሮን ለማሸነፍ ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር በማህበር ተደራጅተው በልዩ ልዩ የቢዝነስ መስኮች ውስጥ በመሳተፍ ገቢ ለማግኘት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። በተለይ በአሁኑ ወቅት በግል የራሳቸውን ቢዝነስ ከመጀመር ይልቅ መንግስት በሚያመቻቸው የስራ እድል ፈጠራዎች ውስጥ በማህበር በመደራጀትና በመረጡት የቢዝነስ መስክ ውስጥ በመግባት ይሰራሉ።
በዚህም ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ከጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ተነስተው ወደ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሸጋገር ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ለመለወጥ በቅተዋል። ያንኑ ያህል ደግሞ የሚደርሱበትን አላማ በቅጡ ያልተረዱና ነገ ለመለወጥ ዛሬ ላይ ያልጣሩ ወጣቶች ህልማቸውን ሳያሳኩ ቀርተዋል።
ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በጋራ ሲሰሩ እያንዳንዳቸው የራሳቸውን የስራ ፍላጎትና አካሄድ ቢኖራቸውም ለቆሙበት የቢዝነስ አለማ ግን አንድ መሆን እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ። ለአንድ አላማ የቆሙና እኩል ጥረት የሚያደርጉ ማህበራትም ውጤታማ ሲሆኑ ይታያል። በተቃራኒው ደግሞ አላማቸው ለየቅል የሆኑ ማህበራት በቀላሉ ይፈርሳሉ። በአላማ ልዩነት አባላቱ ቢጎሉበትም በቀሩት አባላት የውጤት መስመር ላይ ካሉና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ አነስተኛ ጥቃቅን ማህበራት ውስጥ ደግሞ አንዱ በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ የተደራጀው ኡስማን፣ ኑረዲንና ጓደኞቻቸው ህብረት ሽርክና ማህበር ነው።
አቶ ኡስማን ረቡማ የኡስማን፣ ኑረዲንና ጓደኞቻቸው ህብረት ሽርክና ማህበር አባልና ስራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ማህበሩ መንግስት ባመቻቸው የስራ እድል ፈጠራ 400 ሺ ብር ብድር በመውሰድ በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ አምስት አባላትን ይዞ ከአንድ አመት ከስምንት ወር በፊት ተቋቁሟል። ማህበሩ ወደስራ ከመግባቱ በፊትም አባላቱ በየግላቸው የፈሳሽ ሳሙና አመራረት ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።
ወደ ፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ ለመግባት ማህበሩን የገፋፋው የፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ በኢትዮጵያ ብዙም ያልተሰራበት በመሆኑና ቢሰራበት አትራፊ ያደርጋል በሚል ግምት ነበር። በሳሙና ማምረት ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ ግለሰብ ልምዳቸውን ለማህበሩ አባላት በማካፈላቸው ደግሞ አባላት ወደ ሳሙና ማምረት ስራ ለመግባት ይበልጥ አነሳስቷቸዋል። አባላቱ ስልጠናና የሞያ ድጋፍ ከዚሁ ግለሰብ በማግኘታቸው ስለፈሳሽ ሳሙና አመራረት ይበልጥ እንዲረዱ አስችሏቸዋል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ማህበሩ ‹‹ዊነር›› የተሰኘ ፈሳሽ ሳሙና የማምረት ስራውን እንደጀመረ በአባላቱ በኩል ስለፈሳሽ ሳሙና አመራረትና ገበያ ብዙም ግንዛቤ ባለመኖሩ ከሽያጭ ትርፍ ማግኘት አልቻለም። አባላት ደሞዝ የሚያገኙበትም ማህበሩ ከተበደረው ገንዘብ እንጂ ከትርፍ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ከማህበሩ አባላት ውስጥ ሁለቱ ተስፋ ቆርጠው ከማህበሩ ወጡ። አባላት ከመርሃግብሩ ሲወጡ የማህበሩ ካፒታል አሽቆልቁሎ 11 ሺ ብር ብቻ ቀርቶ ነበር።
ይሁን እንጂ አቶ ኡስማንና ቀሪ የማህበሩ አባላት በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ ውጤት እንደሚመጣ አስቀድመው በመገንዘባቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ሶስት ሆነው ስራውን አስቀጠሉ። ቀደም ሲል ምርቱን ለማከፋፈል ለመኪና ኪራይና ነዳጅ ወጪ የሚያወጡትን ወጪ በመተው በራሳቸው ሸከም በእግር እያጓጓዙ ለሱቆችና እቤት ለቤት ማድረስ ጀመሩ። በዚህም ምርቶቻቸውን በሚገባ ማስተዋወቅ ከመቻላቸውም በላይ ተጠቃሚዎች የፈሳሽ ሳሙናውን እንዲወዱት አደረጉ።
የማህበሩ አባላት አምስት እያሉ ደሞዝ የሚከፈለው ከብድር ገንዘብ ላይ የነበረ በመሆኑ ማህበሩ ወደ ተጨማሪ የሰው ቅጥር አልገባም። ይሁንና ሁለቱ አባላት ከወጡ በኋላ በነሱ ፋንታ ቀሪው የማህበሩ አባላት ሁለት ሰዎችን ከውጪ ቀጠሩ። ሰራተኞቹ ፈሳሽ ሳሙናውን እያመረቱ ሲያቀርቡ አቶ ኡስማንና ጓደኞቻቸው ምርቶቹን ለሆቴሎች፣ ለምግብ ቤቶች፣ ለሱቆችና ለመኖሪያ ቤቶች ወስደው መሸጥ ቀጠሉ።
ማህበሩ እንደተመሰረተ መጀመሪያ አካባቢ በቀን ከአንድ ሺ ሊትር በላይ ፈሳሽ ሳሙና በማምረት አሽጎ ያከማች የነበረ ሲሆን ምርቱ በብዛት እየተከማቸ ሲመጣ እንደገና መኪና ተከራይቶ ማከፋፈል ጀመረ። ሆኖም ሽያጩ የታሰበውን ያህል ሊሆንለት አልቻለም። እንዲያም ሆኖ ግን ማህበሩ ፈሳሽ ሳሙና የማምረት ስራውን በኪሳራ አስቀጠለ።
በኋላ ላይ ግን ማህበሩ ፈሳሸ ሳሙና በገፍ ማምረቱን ትቶ መጠነኛ ምርት ማምረት ጀመረ። አነስተኛ ዳማስ መኪና ተከራይቶም ምርቶቹን ለገበያ ማቅረብ ያዘ። በተቻለው አቅምም ለአካባቢው ህብረተሰብ ምርቱን በፕላስቲክ ኮዳ በማሽግ አቀረበ ። በግዜው የፈሳሽ ሳሙና ምርቱን እንደየሊትሩ መጠን በተለያየ ዋጋ ይሸጥ ነበር።
በግዜው ማህበሩ ለገበያ ሲያቀርብ የነበረው የፈሳሽ ሳሙና ምርት ጥራት ያለው ከመሆኑ አኳያ ሌሎች የፈሳሽ ሳሙናዎች በሚቀርቡበት ዋጋ መቅረብ ባይኖርበትም ህብረተሰቡ ምርቱን እንዲያውቀውና ጥራቱን ተረድቶ እንዲገዛ በተመሳሳይ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርብ ተገደደ ። በሂደትም ህብረተሰቡ ሳሙናውን እየወደደው በመምጣቱና የመግዛት ፍላጎቱም በመጨመሩ ማህበሩ በምርቱ ዋጋ ላይ ሁለትና ሶስት ብር ጨመረ። ዋጋው ቢጨምርም ከሳሙናው ውፍረትና ጥራት አኳያ ህብረተሰቡ ምርቱን ይበልጥ በመውደዱ ለመግዛት አላመነታም።
አቶ ኡስማን እንደሚሉት በአሁኑ ግዜ የማህበሩ ተጠቃሚነት ጎልቶ ባይታይም ለሰዎች የስራ እድል ከመፍጠር አንፃር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ቀደም ሲል ከማህበሩ አባልነት በወጡት ምትክ የተተኩትን ሁለት ሰራተኞች ጨምሮ ሰላሳ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል። ሶስት መኪናዎችን በመከራይትም ምርቶቹን በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ ያከፋፍላል። ለመኪና ኪራይም በየወሩ 74 ሺ ብር ይከፍላል።
በኬሚካል ግብአት እጥረት አብዛኞቹ የፈሳሽ ሳሙና አምራቾች ስራ ባቆሙበት በዚህ ግዜ ማህበሩ ኬሚካሎችን በችርቻሮም ቢሆን ገዝቶ ሳሙናውን በማምረት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ የሳሙና ማሸጊያ ፕላስቲኮችም እንደልብ አለመገኘት ማህበሩ ምርቱን በተፈለገው ልክ አሽጎ በፍጥነት ለገበያ ለማቅረብ ፈትኖታል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ማህበሩ የቤትና የመኪና ኪራይ ወጪውን በሚገባ መሸፈን ችሏል። ትርፍ ባያገኘም ከኪሳራ ተላቆ መነሻ ካፒታሉ 800 ሺ ብር ደርሷል። በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የፈሳሽ ሳሙና ኬሚካል እንደልብ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ባይሆንም ማህበሩ በቀን ሶስት ሺ ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ያመርታል።
በአሁኑ ግዜ ማህበሩ የልብስ፣ የእጅና የእቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙናዎችን አምርቶ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን የልብስ ፈሳሽ ሳሙና ከ140 ብር እንደየሊትሩ 35 ብር ድረስ ለገበያ ያቀርባል። የእቃ ማጠቢያ ፈሳሽ ሳሙናውን ደግሞ ከ 140 ብር እስከ 30 ብር ይሸጣል። የእጅ ፈሳሽ ሳሙና በ 30 ብር ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል።
ከነዚህ ምርቶች በተጨማሪ ማህበሩ በረኪናና የሴራሚክ ማጠቢያዎችንም እያመረተ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ያቀርባል። በግብአት እጥረት ምርታቸው ቆመ እንጂ ማህበሩ ሻምፖና ኮንዲሽነሮችን እንዲሁም የመስተዋት ማፅጃዎችን ያመርት ነበር። ሆኖም በአሁኑ ወቅት በፈሳሽ ሳሙና ማምረት ላይ ብቻ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል።
የኮሮና ወረርሽኝ ወደሀገሪቱ ከገባ ወዲህ ፈሳሽ ሳሙናን ጨምሮ የፅዳት እቃዎች ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ እንዳለ ሆኖ የማህበሩም ምርቶችም ተፈላጊነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ እንደነበር አቶ ኡስማን ያስታውሳሉ። እንደዚያም ሆኖ ግን በኬሚካል ጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት የታሰበውን ያህል ፈሳሽ ሳሙና አምርቶ ለገበያ ማቅረብ እንዳልተቻለ ይጠቅሳሉ። የሳሙና ማሸጊያ ፕላስቲክ እቃዎች እጥረትም በተመሳሳይ ማህበሩ ያሰበውን የፈሳሽ ሳሙና ምርት አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ችግር ፈጥሮበት እንደነበርም ስራ አስኪያጁ ይናገራሉ።
አሁንም ቢሆን የፈሳሽ ሳሙና ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም በጥሬ እቃ አቅርቦት በኩል ያለው ችግር ግን እስካሁን ድረስ እንዳልተፈታ ያመለክታሉ። ከውጪ የሚገባውን ጥሬ እቃ በሀገር ውስጥ አምርቶ የሚያቀርብ ፋብሪካም እስካሁን ድረስ እንደሌለ ይጠቁማሉ። ከዚህ አኳያ አብዛኞቹ ፈሳሽ ሳሙና አምራቾች የተዘጉና ለመዘጋት ከጫፍ የደረሱ ቢሆንም ማህበሩ ግን ራሱን ለማስቀጠል እየታገለ መሆኑን ይናገራሉ።
ትርፍ ባያገኝም ሁሌም በማምረት ኪሳራ ውስጥ እንዳይገባ እየሰራ እንደሚገኝም ይገልፃሉ። የጥሬ እቃ አቅርቦት ችግር የሚቃለል ከሆነም ማህበሩ ወደ ትርፍ የመሸጋገር ተስፋ እንዳለው ስራ አስኪያጁ ይጠቁማሉ። ዛሬ በኪሳራ ሰርቶ ያገኘው የገበያ ተደራሽነት ነገ ተጠቃሚ ሊያደርገው እንደሚችለውም ያላቸውን ተስፋ ያስቀምጣሉ ።
ከዚህ አንፃር ለፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች በበቂ ሁኔታ እንዲኖሩ በተለይ መንግስት እነዚህ ጥሬ እቃዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ የፈሳሽ ሳሙና ዋና ዋና ጥሬ እቃዎች ወደሀገር ውስጥ የሚገቡበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ይጠቅሳሉ። ጥሬ እቃው በሀገር ውስጥ እንዲመረት በመንግስት በኩል ድጋፍ ሊኖር እንደሚገባም ያመለክታሉ። በዘርፉ የተማሩና ስልጠና የወሰዱ ካሉም ጥሬ እቃውን ወደማምረት መሸጋገር እንዳለባቸውም ይናገራሉ።
ማህበራቸው እስካሁን ድረስ ታግሎ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገሩት አቶ ኡስማን፤ በቀጣይ የፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራውን በማስፋትና ሌሎች ምርቶችን ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ እቅድ እንዳለው ይገልፃሉ። ምርቶቹንም በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው የማቅረብና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ የመሆን ራዕይ ሰንቀዋል።
እስካሁን ባለው ሂደት እኔና የስራ ባልደረቦቼ የፈሳሽ ሳሙና በማምረትና ለተጠቃሚው በማቅረብ ረገድ ውጤታማ ሆነናል የሚሉት አቶ ኡስማን ማህበሩ የትርፍ ተጠቃሚ ባይሆንም ለሌሎች ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩ የውጤታማነቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን ይገልፃሉ። የማህበሩ አባላት ከስራ አጥነት ወደ ስራ ባለቤትነት መሸጋገራቸውም አንድ ውጤት ነው ይላሉ። ማህበሩ በዚህ መልኩ ከቀጠለና ነገሮች እየተስተካከሉ ከሄዱ ውጤታማ የማይሆንበት ምንም ምክንያት እንደሌለም ይጠቅሳሉ።
ማህበሩ ከመንግስት በኩል የመስሪያ ሼዶችን ቢያገኝ ከዚህም በላይ የመስራት አቅም እንዳለውም አመልክተው፤ አንዳንድ ባንኮችም የድርጅቱን የመክፈል አቅም አይተው ተሽከርካሪዎችን በብድር የሚያገኙበትን ስርአት ቢያመቻቹለት ሰርቶ የመመለስ አቅም እንዳለውም ይጠቁማሉ።
በተመሳሳይ ሌሎችም በዚህ የፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራ ገብተው እንዲሰሩና ውጤታማ እንዲሆኑ በቅድሚያ ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚገባና ይህን ራእያቸውን እውን ለማድረግ በፍላጎትና በተነሳሽነት ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ኡስማን ይመክራሉ። ወደፈሳሽ ሳሙና ማምረት ስራው ከመግባታቸው በፊት ስለአመራረቱ አስቀድመው በቂ ስልጠና መውሰድ እንደሚኖርባቸውም ይጠቁማሉ። ስልጠናውን ወስደው ወደ ሳሙና ማምረት ስራ ከገቡ በኋላም በሳሙና አመራረት ዙሪያ ያሉ አዳዲስ እውቀቶችን መሻትና ራሳቸውንም በመረጃ ብቁ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ።
የሚሰሩት ስራ ሁልግዜ ለገንዘብ ብቻ መሆን እንደ ሌለበትና ከዚህ ይልቅ ጥራትን በማስቀደም ህብረተሰቡን ማገልገል እንደሚኖርባቸው ገልፀው፤ እያንዳንዱ የሚሰ ሯቸው ስራዎች ሁሉ በስሌት መሆን እንደሚገባቸውና የሚያዋጣውን ከማያዋጣው እንዲሁም ትርፉን ከኪሳራው ለይተው መስራት እንዳለባቸውም መልእክታቸውን ያስተ ላልፋሉ።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013