ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
የሐገር ታሪክ ከዜጎቹ ያለፈ ድክመት ጋር ቀጠሮ አለው ይባላል። ለዚህ ነው ትናንትን ላለመድገም ዛሬን በሥርዓት መኖር የሚገባን፤ ለዚህ ነው፤ ዛሬንም በምንችለው ልክ በሰላምና በፍቅር ኖረን ለነገ ልጆች ፍቅርን ልናወርስ የሚገባን።
ኢትዮጵያ ሐገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ ማጤን ያቃተው ብዙ ሰው እንዳለ አስባለሁ፤ ማሰብም ብቻ አይደለም፤ ከአገልግሎቴ ባሻገር በምድሪቱ ሁኔታዊ ክስተትና ሰቀቀኖች ዙሪያ ለአፍታም ቢሆን ሊያዋሩኝ የሚፈልጉ የቅርብና የሩቅ ወገኖቼ፣ ማጠቃለያ መንግስትንና መንግስትን በሚመሩት ድርጅቶች ጫንቃ ላይ ነገሩን ሁሉ ሲጥሉት አያለሁ። ይኼ ጉዳይ ግን ከዚያም የገዘፈ፣ ከዚያ ያለፈ ውስብስብና ቆየት ያለ ፕሮጀክት ውጤት መሆኑን በጥቂቱ ላብራራ እሞክራለሁ።
ባለፈው ጽሑፌ ላይ አበክሬ ስለሰው ልጅ እናም ስለዜጋ ሞት እናስብ እንጂ አማራ ሞተ፣ ኮንሶ ሞተ፣ ኮሬ ሞተ፣ ኦሮሞ ሞተ፣ አትበሉ ያልኩት ለዚህ ነው። እውን ይህንን ቋንቋ ተናጋሪ የነበሩ ሰዎች ስላልሞቱ አይደለም፤ አዎን ሞተዋል አዎን ተተልትለዋል፤ አዎን በጅምላ ተቀብረዋል። ይሁንናም፣ እነዚህ ሁሉ ወገኖቻችን ሞትና ስደት ማፈናቀልና ስብራት ለምን በዚህ ጊዜ ተፈለገ..? ለምን ተባብሶ እንዲቀጥልና አንዳችን አንዳችንን ባለመተማመን ስሜት እንድናይ ምናልባትም ለበቀል እንድንነሳሳ ለምን ተፈለገ? ብለን መጠየቅ የተገባ ነው።
ትግራይ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተነሳውን ግጭት በአነሳስና በአካሄድ የተፈጠረውን ጉዳይ ልብ ብላችሁ ካያችሁ፣ ከአንድ ሰፈር የተነሳው ትርምስ ፍጻሜ ግብ ሁለት ነበረ። አንደኛው፣ በምስራቅ አፍሪካ ከአፍ እስካፍንጫው ታጥቋል፤ ብለው ያመኑት “የአካባቢው ሰራዊት መሪዎች” ፣ (ምክንያቱም ኢትዮጵያ ሐገራችን ያላት ከ70 እስ 80 በመቶ የነበረው የጦር ሃይሏ ክምችት እዚያ ነበረና ) ትጥቁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ታጥቀው ነበረና፣ አዲስ አበባ በወር ውስጥ በመግባት ሙሉ በሙሉ ሐገሪቱን መቆጣጠር፣ (አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና፤ ብጻይ ሥዩም መስፍን ደጋግመው ፊታችንን ወደ አዲስ አበባ ስናዞርና ፌዴራል መንግስቱን ስንቆጣጠር እያሉ …. ቃለ-መጠይቅ ይሰጡ ነበረና፣ እማኝ ከሌላ ቦታ አልጠቅስም) ሲሆን ሁለተኛው ምሥራቅ አፍሪካን የሚያተራምስ ትልቅ ቀውስ በዙሪያው መፍጠር ዓላማቸው ነበረ።
የመጀመሪያው ዕቅድ ሲከሽፍና የዚህ እኩይ ዓላማ ጠንሳሾች አብዛኛው ክፍል፣ ሲወገዱ፣ ሁለተኛውን ግብ ማለትም፣ የአካባቢውን ሰላም የማደፍረስ እቅዳቸውን ለመተግበር ሁሉን አከል፣ እንቅስቃሴ በተሟጠጠው አካላቸው ለማድረግ እየተጣጣሩ ነው። ይህንን ወደ ተግባር ለማስኬድም፣ ባለፉት 27 ዓመታት በስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የነበረውን እያንዳንዱን መግቢያና መውጫ፣ የክረምትና የበጋ መንገዶች፣ የሚፈስሱ ጅረቶችና ደረቅ መሻገሪያዎች የኮንትሮባንድ ማመላለሻዎች፣ በኮንትራባንዲስትነት ጭምር ሲሰሩ ነበረና መሳሪያዎችን በማስገባት፣ መልከ-ብዙ በሆነው የሐገራችንን ህዝብ፣ የቆዳ ቀለም ልዩ ልዩነት ሰበብ በማቅረብና ቅጥረኞችን በመምራት ሽብር እየፈጠሩ ነው።
በየክልሉ ውስጥ ያሉትን በነውራቸው የተባረሩ የቀደሙ ጓዶቻቸውን፣ በየትናንሹ ነገር ሆደ ባሻ የሆኑ ሰዎችንና የወንጀል ግብረ አበሮቻቸውን በመቀስቀስ፣ በመያዝና የስልጣን በሩን በማመላከት፣ በመዋቅር ውስጥ ያሉትን ደግሞ በከፍተኛ ንዋይ በማማለል፣ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲውሉ በማድረግ የማመሱን ተግባር ተያይዘውታል።
ይህ እውነት ብዙ የታሪክ እውነታዎችን ያስታውሰናል። በሐገሪቱ የታጠቀውን ሃይል መሳሪያ በማድረግ አመጽ መቀስቀስና እነርሱ (ውጭዎቹ) እንደ ልባቸው የሚያዙት በራሱ የማይቆም መንግስት መመስረት አንዱ ዘዴ ሲሆን፤ ይህ ካልተቻለ ደግሞ ሐገሪቱን ወደ ትርምስ በመምራት ለአስተዳደር የማትመች በራሷ የማትቆምና “በቡሓ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ በድህነት ላይ ጦርነት የሚያምሳት ሐገር መፍጠር ነው ዓላማቸው።
ለዚህ ነው፤ ኢትዮጵያን ወደዚህ ለመክተት ጥረት እየተደረገ ያለው።
አስቂኝም በሉት አሳዛኝ በኢትዮጵያ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በስፖርታዊ ጨወታ እንዲሸነፍ የሚፈልግ እና ኢትዮጵያ የምትባለው ሐገር አንገቷን እንድትደፋ የሚፈልጉ ሰዎች ገጻቸው የተገለጠበት ወቅት የታየው አሁን ነው። ኮትዲቯር ከኢትዮጵያ የምታደርገው ጨወታ እየተላለፈ 10 ለ1 የምትሸነፍ ሐገር ይዛችሁ የት ለመድረስ ነው፤ ከሚል ውጋት ሌላ፣ “ኢትዮጵያ ጎል ተቆጠረባት” ፣ ሲባል የፍንደቃ መልእክት በአማርኛ ቋንቋ በየማህበራዊ ሚዲያው የሚያስተላልፉ፣ በአስተሳሰብ ድውያን የሆኑ ሰዎችን አስተያየት ያነበብነው፣ በዚህ ሰሞን ነው።
አስደሳቹ ነገር ግን፣ በዚህ ምስቅልቅል ውስጥ ሆነው የሐገራቸውን ደግ ሲሰሙ ደስታቸውን በአደባባይ በዚህ ክፉ ሰዓት (ኮሮናው ማለቴ ነው) ለመግለጽ የማያመነቱ እልፍ ዜጎች በምድራችን መኖራቸውን ስናይ ያጽናናናል።
ክፉዎቹ አካላት አልገባቸውም እንጂ፣ ምንም ድህነት ቢያጎሳቁለው፣ ህመምና ስደት አንጀቱን ቢያላውሰውም፣ የኑሮ አለመመቸት እንደድንጋይ መቀመጫ ቢቆረቁረውም፣ በሐገሩ ጉዳይ ግን መቼም አለሁልሽ፤ ከማለት ወደኋላ የማይመለስ ህዝብ እንዳላት ጠላቶቿ አለማወቃቸው፣ ወይም ሊያውቁ አለመፈለጋቸው ይገርማል።
መከራው ሊያስለቅሰው፣ ሐዘኑ ልቡን ሊሰብረው ይችል ይሆናል፤ እጦቱ ከሐገር ሊያስወጣው፣ ሄዶም የስደት እንጀራና እንግልት ሊያስቃየው ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ሐገሩን መቼም የማይረሳና ከሐገሩ ፍቅር የሚታቀብ ህዝብ አጥታ የማታውቅ እናት ናት፤ ኢትዮጵያ። መቼም ቢሆን እናት ድኃ ናት፤ ተብሎ ቀሚሷ አይገለብም፤ አያዋርዷትም፤ ነውሯን የአደባባይ ጌጥ አያደርጉትም።
በቅርቡ አዲሳባን፣ ባህርዳርን ናዝሬትንና ሌሎቹን ዋና ዋና ከተሞች፣ “አፈንዱ፤ አቃጥሉ፤ ሐገሪቱን እሳት በእሳት አድርጉ”፤ የሚል ጩኸት ያሰማን “የማህበራዊ ሚዲያ አርበኛ”፣ አያቶች እና ቅድም አያቶች ቢሰሙት ምን ሊሉት እንደሚችሉ ባላውቅም፤ አንድ ነገር ግን እገምታለሁ፤ “ልጄ፣ ነገ በጤናማ አእምሮ የማትደግመውን፣ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ንግግርህን፣ ምናልባት በበላኸው አስተናግራዊ የግብጽ ቅጠል ሳቢያ ሊሆን ስለሚችል፣ እርሱን የሚያረክስ ጥበብ፣ እዚሁ በዋሸራና ደብረ-ዳሞ ገዳማት አለልህና፣ መጥተህ እሽት አድርገህ ብትፈልግ በማሽተት መልክ፣ ቢሻህ ጨምቀህ ብትቀምሰው ወዲያው ትፈወሳለህና፤ ና፤ እንደሚሉት የታመነ ነው።
ይኼ ጋጠወጥነትና ሐገር አሳናሽ ድርጊት መነሻው ቀላል እንዳልሆነ አምናለሁ። በወጣትነት ዘመኑ ለአምልኮ በቀረበ ስልት፣ ስለድርጅቱ (ትህነግ)፣ ፍጹማዊነትና አይበገሬነት ሲሰማ ለኖረው ለዚህ ወጣት ልጅ፣ እንዲህ ዓይኖቹ ሥር ያ፣ የሚያደንቀውና ሁሉን ቻይ ይመስለው የነበረው ድርጅቱ፣ ፍርክስክስ ብሎ ከእጅ እንዳመለጠ ሸክላ ድስት ሲበተን ያየው ልጅ፣ በቀላሉ አምኖ ለመቀበል ቢቸግረው ያመጣው ዘዬ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። በአለቃው ሲናደድ፣ ሚስቱን እንደሚደበድብ ባል መሆኑ ነው።
ይህም ሁሉ ሆኖ አንዲትን ሐገር አሳንሶ ማየትና ለተወሰኑ ልሒቃን፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ፍቃድ አሳልፎ መስጠት ርግማንም የእይታም መንሸዋረር ነው። ምነው ቢሉ በሐገረ መንግስት ግንባታ ከእኛ ኋላ ኋላ የመጡት የ1950ዎቹና 60ዎቹ ዓ.ም ነጻ የወጡ ሐገራት እንኳን ክብርና ነጻነታቸውን ለሌሎች አሳልፈው ሲሰጡ አይታይምና።
የረባ መጓጓዣ፣ የረባ የጦር መሳሪያ፣ የረባ ስንቅና አቅርቦት ሳይኖራቸው፣ በሐገር ፍቅርና በልበ-ሙሉ፣ ድንቅ የውጊያ ጥበብ ያቆዩልንን ሐገር በዚህ ዘመናዊ ዘመን፣ ለግብፆች ተንኮልና ለሐገር ውስጥ ጋሻ ጃግሬዎቻቸው፣ ፈቃድ አሳልፎ መስጠትማ፣ ለዚህ ትውልድ እርግማን ነው።
የወጉን ሳያንስ፣ ሊያስወጉን ሲነሱ እያወቅን፣ ለመወጋት ራሳችንን በልዩነት አመቻችተንማ ልንሰጣቸው አይገባም። እንዲህ ያሉ ነውረኞች፣ በታሪክ ውስጥ በየትኛውም ጊዜ እየተነሱ ታላላቆችን ምናምንቴ ሲያደርጉ ኖረዋል። ኢትዮጵያም፣ በቤተ መንግስት ሽኩቻዎች ብዙ ወርቅ ልጆቿን ገብራለች። ምንም ጭካኔ ውስጥ ውስጡን ቢያተክናትም፣ የእርስ በእርስ መጎሻሸሙ ብዙ ብዙ የጎዳን ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ግን እስካሁን አለች፤ ወደፊትም በተሻለ አቅምና አቋም ተጠናክራ ትቀጥላለች።
ታሪክ በራሱ መንገድ ከጻፋቸው መካካዶች አንዱን በዚህ ጊዜ ላወሳችሁ እፈልጋለሁ። ሮማን ገናና ያደረጋትና እስከ ግብጽ ድረስ መጥቶ፣ ለመውረርና ቅኝ ለመግዛት የቻለው፣ ታላቁ ዩልየስ ቄሳር፣ በታላላቅ ዓውደ-ውጊያዎች የተሳካለት ነበረና ሮማን የድል ምልክት አድርጓት ነበረ። የዚያኑ ያህል ድሉ ለእኛ ብዙ አላተረፈልንም፤ የሚሉ ወገኖች በእረፍቱ ሰዓት እንዲያርፍ አልፈለጉምና ሊያጠፉት አሴሩ፣ በአንድ አመሻሽ ላይ ውጥናቸውን መተግበር ፈለጉ። ወደ መናፈሻው ለመውጣት በመተላለፊያው ላይ ሲሄድ አገኙትና ገደሉት።
የዘመኑ መሳሪያ ስለት ነበረና ወጉት፤ ለመሞት ሲያጣጥር የመጨረሻውን ስለት የሰነዘረበት የጦር ሜዳ ወዳጁና እራት አብረው የበሉት፣ ጄኔራል ብሩተስ ነበረ። እናም “ብሩተስ አንተም?” ሲል ተናገረው፤ ይባላል። ከዚያ በኋላም በቅርብ ሰው የሚፈጸም ክፉ ግድያ “ብሩታል” ነው፤ የሚባለው፣ በዚህ ምክንያት ነው፤ ይባላል።
በክህደት የተሞላ የወዳጅ ሸፍጥና ክህደት ያለበት ግድያ፣ ከግድያው በላይ ያምማል። ሮማም፣ ከእዚያን መሰል ትርምስ በኋላ እንደነበረው አልቀጠለችም። ቀስ በቀስ እየሟሟች ነው፤ የሄደችው። የአንድን ሐገርም ህያውነትም ሆነ ዝና የሚያጠፋው ነገር፣ መነሻ ከውጭ የመጣና የተጠነሰሰ ከሆነ የሚያደርሰው ጥቃትና የአፍራሽነት ጉልበት ደካማ ነው። ከውስጥ ግን ከተነሳ፣ የአጥፊነት ጉልበቱ ኃያልና የአፍራሽነት መንፈሱ ክፉ ነው፤ የሚሆነው።
ለዚህም ነው፤ የተፈጸመው ግድያ በሰው ላይና ፈጻሚውም ሰው፣ ያውም የገዛ ዜጎቻችን ናቸው፤ እያልኩ አበክሬ ልናገር የምወደው። የግብጽም ሆነ የሱዳን የአረቡ ዓለምም ሆነ የምእራባውያኑ ጣልቃ ገብነት ሊያዳክመን እንጂ፣ ሊያጠፋን የሚያስችል አቅም አይኖረውም፤ እኛ ራሳችን አቅም ስንሆናቸው ብቻ ነው፤ በጥፋታችን የምንጠፋው ብዬ የማምነው።
በመነሻዬ ላይ የሐገር ታሪክ ካለፈ ድክመት ጋር ቀጠሮ አለው፤ ብዬ ነበረ። ያ፣ ቀጠሮ የሚገጥመው ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነቱን የሚያጎላ፤ ከጋራ ትውፊቱ ይልቅ የግል ተረቱን የሚያደንቅ፣ ከእውነተኛ ታሪኩ ይልቅ የፈጠራ ትርክቶቹን ማባዛት የሚወድና ይህም አርቆ ከማያስተውል ስሜታዊ ትውልድ ጋር መግጠም፣ ሲጀምር ነው። ያኔም ተረቱን አምኖ እውነቱን ይክዳል፤ ልዩነቱን አራግቦ አንድነቱን ያላላል፤ ይህንንም አለመፈለጉ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትም ይንበረካካል ማለት ነው። ሐገርም ቀስ በቀስ መሟሸሽና ለአጥፊዎቿ የተመቸች ምድር ትሆናለች።
ማንም አጥፊ ሃይል ሲመጣ፣ አሞካሽቶ እንጂ አዋርዶ፣ አጋንኖ እንጂ አንኳስሶ እንደማይቀርብ የታመነ ነው። አንድ የውጭ ኃይል አላግባብ ሲያሞግስህና ያለጀብዱህ ሲያወድስህ “ለምን እንዲህ ደገፈኝ፤ ”ለማለት ካልቻልክ ለአፍራሽ ግቡ እያመቻችህ መሆኑን እንዳትስት ፣ አሻንጉሊቱ እያደረገህ መሆኑን አትርሣ። ለዚህም መንፈሳቸው የወደቀ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት ያኮረፉና ሆድ የባሳቸው ባዕድ አክባሪ፣ ወገን አክሳሪ፣ ባንዳዎች በየስፍራው አይጠፉም።
ጣሊያን በ1928 ዓ.ም ወርሮን አምስት አመት ቆይቶ ሊወጣ፣ ለዚያች አጭር እድሜ፣ በእርሱ ጫማ ሥር ያደሩ ሰዎችን ማንነት፣ ታሪክ አሳይቶን አልፏል። የሚገርመው ታሪክ ታዝቧቸውና አርሟቸው አልፏል። አሁንም ለሌሎች መሳሪያና አርጩሜዎች እኛው ካልሆንን ገራፊው ከውጭ አይመጣም።
ያኔም ተፍ ተፍ ሲሉ የነበሩትንና ከጣሊያን በሚጣልላቸው ሶልዲ፣ (የጊዜው ገንዘብ) ፍርፋሪ፣ በየጠጅ ቤቱ እዩን እዩን ይሉ የነበሩትን የዘመን ሞልቃቆች የታዘቡት፣ የወቅቱ ባለቅኔዎች፡-
ጣሊያን ይወጣና ሶልዲውም ያልቅና፣
ያስተዛዝበናል ይኼ ቀን ያልፍና። እንዳሏቸው ታሪክ አቆይቶናል።
ቀደም ሲል፣ በመነሻዬ ላይ እንዳልኩት ኢትዮጵያ ሐገራችን ከወደቀችም፣ እንዳትነሳ አድርገን የምናፈርሣት እኛው ልጆቿ እንጂ፤ የውጭ ወራሪ ኃይሎች አይደሉም። ወራሪማ ለበርካታ ጊዜ ሞክሮ ሳይሳካለት መሄዱን ከጥንት የግሪክ ፀሐፍት እስከ ሮማ ወራሪዎችና በኋለኛውም ዘመን ደርቡሽ በሉት፣ ማህዲስት፣ ግብጽ ራሷና ጣሊያንም በሉት ሌላ ስም ያለው የውጭ ወራሪ አካል፣ ሞክሯታል እንጂ አልረታትም፤ ወርሯታል እንጂ አልገዛትም።
አንድ ነገር ላክልና እንሰነባበት፣ ብዙዎቻችን አንዳች ውድቀት በሥራችን፣ አንዳች እንከን በትዳራችን፣ አንዳች እንቅፋት በጉዟችን ሲገጥመን ጣታችንን ወደ ውጭ መጠንቆልና እርሱ ነው፤ እርሷ ናት፤ አለፍ ሲልም እነርሱ ናቸው ማለት እንወዳለን እንጂ፤ ወደ ውስጣችንና ወደራሳችን በማስተዋል አናይም። ለዚህ ውድቀት፣ ለዚህ መሰናክልና ለዚህ የትዳር መናጋት የእኔ አስተዋጽኦ ምንድነው ብለን አንጠይቅም። በሐገርም ጉዳይ አስቸጋሪና ውሰብሰብ ያለ ነገር፣ ሲገጥመን “እኛ ምን እያደረግን ነው፤” ብለን መጠየቅና ከአፍራሽ ድርጊትና አስተዋፆዋችን መቆጠብ ይገባናል እንጂ፣ ወደምስራቅም ወደሰሜንም መጠቆም ምንም አያዋጣም። የእነርሱ አስተዋጽኦ አባባሽነት እንጂ ወሳኙን ሚና የሚጫወተው የእኛ ሴራና ደንቃራ ነው።
አበባ ላይሆንለት ፤ እባብ ካረባ ጎረቤት ፣
የከፋው በቤታችን ውስጥ ፤ ሸረሪት ማርባት ነው ውጋት ። (ያልታተመ)
እናም ፣ እርስ በእርሳችን እንጠባበቅ እንጂ አንራራቅ፤ እርስ በእርሳችን እንደጋገፍ እንጂ አንጠላለፍ። ከውጭ ባለው ሃይል ላይ ሆይ ሆይታ ስንይዝ፣ እንደዘበት በጉያችን ያደባ ክፉ አጥፊ፣ እንደቋያ እሣት እንዳያግለበልበን እንጠንቀቅ። ውስጣችንን አጥርተን እንይ፤ እንወስን፣ በአንድ ልብ ለሀገር ዘብ እንሁን!!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር ተከብራ እንድትኖር እግዚአብሔር ይባርከን!!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 9/2013