ካንሰር በዓለማችን ገዳይ እየሆኑ ከመጡ በሽታዎች አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረትም እጅግ ፈታኝ እየሆነ መጥቷል፡፡
ከዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የካንሰር በሽታ በአሁኑ ወቅት ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ሳምባ ነቀርሳና የወባ በሽታዎች በጋራ እያደረሱ ካሉት ሞት በላይ የሰዎችን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ በሽታው በቂ ቁጥጥር ካልተደረገበትም በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ በየዓመቱ 24 ሚሊዮን ለሚጠጉ የዓለማችን ሰዎች ሞት ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያም በየዓመቱ ከ67 ሺ በላይ ሰዎች በካንሰር ህመም እንደሚያዙና ባለው የህክምና አገልግሎት ውስንነት ምክንያት 44 ሺ ያህሉ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቅርቡ ከግሎባል ናንሴንት ኮሚሽን /global lancet commission/ ጋር በመተባበር በተካሄደ የሁለት ዓመት ጥናት በኢትዮጵያ 52 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነው የሞት መጠን የሚከሰተው ደግሞ በካንሰር ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡
ከአንድ ሶስተኛ በላይ ወይም እስከ 40 በመቶ የሚሆኑትን የካንሰር ህመም አምጪ ምክንያቶችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል የጤና ባለሞያዎች ይመክራሉ፡፡ ሆኖም በከተሞች አካባቢ የሰዎች የአኗኗር ስልት እየተለወጠ መምጣቱን ተከትሎ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከልና ከትምባሆና ከአልኮል መጠጦች ራስን በማራቅ ካንሰር አምጪ ምክንያቶቹን መከላከል አልተቻለም፡፡ በዚህም ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች የልብ፣ ኩላሊት፣ መተንፈሻ አካልና የስኳር ህመምን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከፍተኛ የጤናና የልማት ችግሮች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናቸውም እየበረታ ይገኛል፡፡
የጤናው ዘርፍ የአምስት ዓመት ትራንስፎርሜሽን እቅድ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት የካንሰር ህመምን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግሥት በኩል ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የካንሰር ህክምና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ አሁንም ውስንነቶች እንዳሉ የጤናው ዘርፍ ባለሞያዎችና አመራሮች ይናገራሉ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ እንደሚናገሩት፤ በሀገሪቱ እየተሰጠ ያለው የካንሰር ህክምና አገልግሎት ከችግሩ ግዝፈት አኳያ ተደራሽነቱ ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ለዚህም የህክምና የተቋማት በአነስተኛ ብቃትና ዝግጁነት ላይ መገኘት፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ውስንነትና አነስተኛ የመድሃኒት አቅርቦት ለአገልግሎቱ ተደራሽነት ውስንነት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
አማካሪው እንደሚሉት የካንሰር ህክምና አገልግሎት የተደራሽነት ችግሮች አሁንም የሚታዩበት ቢሆንም ከቅርብ ግዚያት ወዲህ እየተከናወኑ ያሉ ማዕከላትን የማስፋፋትና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራዎች የህክምና አገልግሎቱን በብቃትና በተደራጀ የሰው ኃይል ለመስጠት ያስችላል፡፡ በተለይም በስድስት ሆስፒታሎች ላይ የተጀመረው ህክምናውን የማስፋት ስራ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ችግር ይፈታል ተብሎ ይገመታል፡፡
እንደ አማካሪው ገለፃ፤ የአብዛኛዎቹ የካንሰር ህሙማን ችግር የአካል፣ የስነልቦና፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የህመም ስቃይ በመሆኑ ከህክምና አገልግሎቱ ጎን ለጎን በህመም ስቃይ ማስታገስ ዙሪያ በርካታ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል፡፡ አዳዲስ በሚከፈቱ የካንሰር ህክምና ማዕከላትም የህመም ስቃይ ማስታገስ ህክምናን አብሮ ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የማህበራዊና ስነ ልቦና ድጋፎችን ማጠናከር ይገባል፡፡
የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤትና በኢትዮጵያ የብሄራዊ ካንሰር ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዳ ግንዛቤ በማህበረሰቡ ውስጥ እንዲፈጠርና የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
ጥረቶቹ አሁንም በቂ ባለመሆናቸውና በተለይም የካንሰር ህመም በሽታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በህክምና የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተደራሽነት ውስንነት በመኖሩ አሁንም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የተጀመሩ የካንሰር ማዕከላት የማስፋፊያ ግንባታዎችም በቶሎ ተጠናቀው ለአገልግሎቱ ፈላጊዎች ክፍት እንዲሆኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይገባል፡፡
እንደ ሰብሳቢዋ ገለፃ፤ የብሄራዊ ካንሰር ኮሚቴው ለአንድ ዓመት ያህል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተሰብስቦ የአለመወያየቱ በካንሰር ላይ የሚሰሩ ሥራዎች መቀዛቀዝ አሳይተዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ የካንሰር ህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ ተደራሽ እንዲሆን ከኮሚቴው ጋር የሚደረገውን የተዳከመ ግንኙነት በማሻሻል በአዲስ መልክ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከልም ጥረት እየተደረገ ነው የሚሉት ሰብሳቢዋ፣ በተለይ በቅርቡ እድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች የተጀመረው የማህፀን በር ካንሰር ክትባት መርሃግብር ውጤታማ እንዲሆን ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሞያዎችና በየደረጃው ያሉ አስተባባሪዎች በጋራ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በለጋ እድሜ የሚጀመር የግብረ ስጋ ግንኙነት ለማህፀን በር ካንሰር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ተማሪዎች ራሳቸውን ከግብረስጋ ግንኙነት አቅበው በእውቀትና በትምህርት ዳብረው እንዲያድጉ የሁሉም አካላት ጥረት ያስፈልጋል፡፡
በተመሳሳይም የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራና ልየታ አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ላይ ስላልተዳረሰ እድሜያቸው ከ30 እስከ 49 ዓመት የሆናቸውና የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራና ልየታ አገልግሎት በሚሰጡባቸውና አገልግሎቱ በተዳረሱባቸው ጤና ተቋማት አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች አገልግሎቱን ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ለዚህም በየአካባቢው ያለው አካል በየግዜው ቅስቀሳዎችን ማድረግና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ተቋማቱም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
ቀደም ሲል በአንድ ማእከል ብቻ ሲሰጥ የነበረው የጡት ካንሰር ምርመራና የመድሃኒት ህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በተደረገ ጥረት አገልግሎቱን የሚሰጡ ሆስፒታሎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዚህም የጡት ምርመራ በማድረግ በሽታው መኖሩን አለመኖሩን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በሽታው ሲገኝም ህክምና ከተደረገለት የመዳን እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ ሴቶች በነዚህ ሆስፒታሎች የሚሰጠውን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሁንም ግንዛቤዎችን ማስጨበጥና የቅስቀሳ ስራዎችን በተጠናከረ መልኩ ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደሚገልፁት፤ በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ሚኒስቴር የተዘጋጀው የብሄራዊ ካንሰር መከላከል እቅድ ፀድቆ ተግባራዊ መሆኑ ካንሰርን ለመከላከልና ለመቆጣጣር መንግሥት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያል፡፡ ይህም በአፍሪካ አህጉር በሀገር አቀፍ ደረጃ የካንሰር እቅድ አዘጋጅተውና በጀት መድበው በመተግበር ላይ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን አንዷ ያደርጋታል፡፡
ይህ መልካም ጅማሬ ቢሆንም ያለውን የካንሰር ችግር ለመቆጣጠርና ለመከላከል አሁንም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ፡፡ በተለይም ከፍተኛ የህክምና የአገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት የሚታይ በመሆኑ የካንሰር ህክምና ማዕከላትን ማስፋት ያስፈልጋል፡፡ ህክምናውን የሚሰጥ የሰው ኃይል እጥረትና የመድሃኒት አቅርቦት ችግሮችም የዘርፉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ፤ የካንሰር ህክምና አገልግሎት በአብዛኛው የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ በመሆኑ ከፍተኛ የአገልግሎት ጫና አስከትሏል፡፡ በርካታ ተገልጋዮችም ህክምናውን በተገቢው ሁኔታና በሰዓቱ እያገኙ አይደለም፡፡ ይህም የካንሰር ህክምና አገልግሎት የተደራሽነት ውስንነት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡
የህክምና አገልግሎት ተደራሽነቱን ችግር ለመፍታት የካንሰር ህክምና ማስፋፊያ ማዕከላት ግንባታዎችን ማካሄድ ወሳኝ መሆኑን የሚጠቅሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በአሁኑ ወቅት የጥቁር አንበሳን የካንሰር ህክምና ማዕከል ከማጠናከር ጀምሮ በጅማ፣ በሃሮማያ፣ በጐንደር፣ በመቀሌና በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ራሳቸውን የቻሉ የካንሰር ማዕከላት በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስድስት ዘመናዊ የጨረር ወይም የሬዲዮቴራፒ መሳሪያዎች ግዢም ተካሂዷል፡፡
እየተገነቡ ካሉት ስድስት የካንሰር ህክምና ማዕከላት ውስጥ ሶስቱ ከሶስት ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ ቀሪዎቹ ሶስቱ ደግሞ በስድስት ወራት ግዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም በቅርቡ የካንሰር ህክምና አገልግሎትን ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአምስት የክልል ዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል ሲሆን የተጠቃሚዎችን መንገላታትና ረጅም የህክምና ቀጠሮ የሚያስቀር ይሆናል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደሚሉት እጅግ የተራቀቁና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ እንደ መቅኒ የመለወጥ/ bone marrow taransplant/ ህክምናዎች ጭምር የሚሰጥበት የካንሰር ህመም የልቀት ማእከል ግንባታ በአዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ይህን መሰል አገልግሎት ከሚሰጡ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያን አንዷ ያደርጋታል ብለዋል፡፡ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ውጪ ሀገር የሚደረገውንም ጉዞ እንደሚቀንስ ጠቁመዋል፡፡
የካንሰር ህክምና ባለሞያዎች /oncology/ ቁጥርን ለማሳደግ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ያለውን የካንሰር ህክምና ባለሞያዎችን ቁጥር ከ13 ወደ 30 ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2011
በአስናቀ ፀጋዬ