አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ የገንዘብ ኖት ቢቀየር ያለአግባ በግለሰቦች እጅ የሚገኝን ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ ስለሚያ ደርግ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እንደሚረዳአስተያየታቸውን ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰጡ ምሑራን ገለጹ፡፡
በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደተናገሩት፤ በአንድ አገር በተለያዩ ምክንያቶች ገንዘብ ከባንክ ይልቅ በግለሰቦች እጅ ሊከማች እና በግለሰቦች እጅ የሚገኘው ገንዘብ ሲበዛ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡ በዚህ መልኩ በሚደርስ ተጽዕኖ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆልን ለመታደግ ደግሞ በግለሰቦች እጅ የተከማቸውን ገንዘብ ለመሰብሰብና ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግ የገንዘብ ኖት መቀየር የግድ ይሆናል፡፡
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለጻ፤ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ገንዘብ መለወጥ አስፈ ላጊ የሚሆንባቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ገንዘብን ማሸሽ ወይም ሰዎች ገንዘብን ከኢኮኖሚው አርቀው በራሳቸው ካዝና ማስቀመጥ አንዱ ሲሆን፤ ይሄን ችግር ለማቃለልና ኢኮኖሚውንም ለማረጋጋት የገንዘብ ኖት መቀየር ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ገንዘብ ከኢኮኖሚው ሲወጣ መንግሥት የገንዘብ ኖት ቢቀይር የተደበቁ ገንዘቦች ወደ ባንክ ገብተው የኢኮኖሚው አካል እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ኢኮኖሚውን ያላገናዘበ የገንዘብ ዝውውር ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት ያለው በመሆኑ፣ ጉዳዩ በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ይፈልጋል፡፡
ሆኖም ይሄን ሁኔታ ለመቆጣጠር የታተመ ገንዘብ አቅርቦትና ፍላጎት መጣጣም እንዳለባቸው የሚገልጹት አቶ ፍሬዘር፤ ገንዘብ ለማሳተም የሚወጣው ወጪም ከግምት መግባት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ገንዘብ ሲቀየር ለህትመቱ ስለሚወጣው ዋጋ እንዴትና ለምን የሚሉት ነገሮች መታየት እንዳለባቸው ጠቅሰ ዋል፡፡ በምሳሌነት አንድ ብር የገንዘብ ኖት ቶሎ ስለሚበላሽና የአገልግሎት ዘመኑ አጭር ስለሆነ ወጪ ለመቀነስ ወደ ሳንቲም ደረጃ እንዲወርድ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መላኩ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የገንዘብ ኖት ሲቀየር የህዝብ ኑሮና ደህንነት በመጠበቅ ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም ያረጋጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም የገንዘብ ኖት ቢቀየር ከኢኮኖሚው የሸሸውን ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚው እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ፤ በአገሪቱ ያሉ አርቴፊሻል ብሮች ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በህገወጥ መንገድ የሚታተሙ ብሮችን ለመቆጣጠርም ያስችላል፡፡
«በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው ከሚያውቀው ውጪ የተሰራጨው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ ነው» ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ይሄም ብሄራዊ ባንክ በኢኮኖሚው ምን ያክል ገንዘብ እንዳለው መቆጣጠር እንዳይችል ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ ይሄን የገንዘብ ስርጭት ለመቆጣጠር የገንዘብ ኖት መቀየር የመጀመሪያ አማራጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በተለይም በኮንትሮባንድና በሙስና የተሰበሰቡ ገንዘቦችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የገንዘብ ኖት መቀየር ኢኮኖሚውን ከማረጋጋት ባለፈ መንግሥት የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ እንዲያውቅ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ ገንዘብ በኢኮ ኖሚው ላይ ሲበዛ የዋጋ ግሽበት ያመጣል፡፡ ለዚህ ደግሞ የገንዘብ ኖቱ ቢቀየር የዋጋ ግሽበት የመቆጣጠር አቅምም ይኖራል፡፡ የገንዘብ ኖት ሲለወጥ ችግር ሊኖረው፤ በኢንቨስትመንት ላይም መቀነስ ሊታይ ቢችልም፤ ከረጅም ግብ አንፃር ከታየ ውጤት ያመጣል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት4/2011
መርድ ክፍሉ