አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረ ጋጋቶችን፣ ግጭቶችንና የነበሩ ቁርሾዎችን መፍታት የሚቻልባቸውን መንገዶች ለመቀየስ እንደሚያስችል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በሚኒስቴሩ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም የበዓሉ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ተሾመ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከየካቲት ዘጠኝ እስከ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ የሚካሄደው ስምንተኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተሞች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ልምድና ተሞክሯቸውን የሚለዋወጡበት እንደመሆኑ በአገሪቱ ለሚታዩ አለመረጋጋቶችንና ግጭቶችን ለመቀነስ፣ የነበሩ ቁርሾዎችንም ለማስወገድ የሚያስችሉ መንገዶች ለመቀየስ ያስችላል፡፡
እንደ አቶ ብርሃኑ ገለጻ፤ በፎረሙ ከተሞች የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የይቅር ባይነት እንዲሁም የአንድነት እሴት ይዘው እንዲደጋገፉ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ በከተሞች ዘላቂ ሠላምን እንዴት ማረጋገጥ ይችላል? በሚለው ዙሪያም የጋራ መግባባት መፍጠር የሚያስችል የፓናል ውይይት ይደረጋል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ጉዳይም በስፋት የሚመከርበት ይሆናል፡፡
ፎረሙም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የልማት ኃይሎች፣ የየከተሞቹ ነዋሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት እንደመሆኑ፤ በከተሞች ልማት ላይ በተቀናጀ አግባብ በመሥራት ፈጣን ዕድገት ማምጣት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከተሞች ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያከናወኑትና እያከናወኑ ያሉት ተግባር በተሞክሮነት ቀርቦ ውይት ስለሚደረግበት በከተሞች ብቻ ሳይሆን እንደ አገር በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች እልባት እንዲያገኙ፤ የነበሩ ቁርሾዎችንም ለማስወገድ የሚቻልባቸውን አሠራሮች ለማስቀመጥ ዕድል ይፈጥራል፡፡
ሚኒስቴሩ ከዚህ ቀደምም አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል ሲሠራ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፤ በፎረሙም እያንዳንዱ ከተማ በተቀመጠው አገር አቀፍ መመዘኛ መሰረት አገልግሎቶቹን በማዘመን ተገላጋዮችን ከማርካትና ህዝብን አሳትፎ ውጤት ከማምጣት አኳያ ያከናወናቸው ተግባራት እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል፡፡ የትራንስፎርሜሽን ቁልፍ አመራር፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና፣ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት፣ የቤቶች ልማት፣ የተቀናጀ መሠረተ ልማት፣ የኮንስትራክሽን፣ አረንጓዴ ልማት እንዲሁም የፅዳትና ውበት ሥራዎች፣ የፋይናንስ አመራርና ልማት ላይ በማተኮርም ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ሂደቶችም ለከተሞች ልማትና ብልጽግና ከሚኖራቸው ፋይዳ ባለፈ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፤ ቁርሾዎችም እንዲወገዱ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ለመንደፍ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት 163 በላይ ከተሞችና ድርጅቶች በፎረሙ ለመሳተፍ የተመዘገቡ መሆኑን በመጠቆም፤ ከተሞቹም በቂ ዝግጅት አድርገው መገኘት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ ጥበቃውን አስተማማኝ ለማድረግ ከሰላም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙንም ገልጸዋል፡፡ ከሠላም ጋር ተያይዞም ስጋት የሚጭር ምንም ዓይነት ችግር አለመኖሩንና በሶማሌ ክልል መግቢያ በሮችና መተላለፊያ ክልሎች ላይም ለእንገዶች አቀባበል እንደሚደረግም አመላክተዋል፡፡ በዚህ በዓል ላይ ናይሮቢ፣ ጁባ፣ ጅቡቲ፣ አርጌሳ፣ አሥመራና ኪጋሊ ተጋባዥ ሲሆኑ፤ አርጌሳ፣ ጀቡቲና ኪጋሊ የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ እህት ከተሞች እንደሚሳተፉም ተናግረዋል፡፡
«መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና» በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው ይህ በዓል፣ በአገሪቱ ያሉት ከተሞች ከሚፈጥርላቸው ትውውቅ ባሻገርም ልምድና ተሞክሮ ለመለዋወጥ፣ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ እንደሚያስችላቸው በመግለጽም፤ የተሻለ ሥራ ላከናወኑ አካላትም ዕውቅናና ሽልማት የሚሰጥበት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 4
ፍዮሪ ተወልደ