ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
ታክሲ ውስጥ ነው፤ ወደ ሃያ ሁለት እየሄደ። ፊቱን ወደ ግራ አዙሮ በመስተዋቱ ወደ ውጪ ያያል። አዲስ አበባን ይመለከታል፤ ጉዷን፣ ቆነጃጅቷን..ትናንቱን ዛሬውን ሁሉ። ማየት ይወዳል። በተለይ ቆንጆ በተለይ ዳሌ በተለይ ከንፈር ነፍሱ ነው። አዲስ አበባ ትገርመዋለች። አንዲት ፉንጋ ሴት እንዳይገባባት አዋጅ የወጣባት ይመስለዋል። ወደዚያ ወደዚህ ሲል ውብ ብቻ ነው የሚያየው። የነፍስ መደሰቻ ሴት ናት ይላል። ወንድ ልጅ የሴትን ያህል ውበት መግለጫ የለውም ሲል ያስባል። በዘመኑ እንደ ሴት ልጅ አስደናቂ ፍጥረት አላየም። ገሀነምም መንግስት ሰማያትም በሴት ልጅ ነፍስ ላይ ያሉ ይመስለዋል።
ስራ ሲፈታ መሄጃው ወደ ትናንት ነው። በዛሬው ውስጥ ያልኖረው ትናንት አለ። የታክሲዋ ኋላ ወንበር ላይ ሆኖ ሃሳብ ወሰደው። መክሊት መጣችበት። ዝም ካለ ከእሷ ሌላ የሚያስባት ሴት የለችም። መክሊት የህይወቱ ምርጥ ትዝታው ናት። በትናንቱ ላይ የቀለማት ውብ ስዕሉ። እንደ እሷ ደስታን የሰጠው ማንም የለም። ገነትን በእውን ነው ያሳየችው። እያንዳንዱ ተፈጥሮዋ ይገርመዋል። ለመላዕክትነት ተፈጥራ በማይታወቅ ምክንያት ሰው የሆነች ይመስለዋል። እግዜር ከፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በእሷ የሚደነቅ ይመስለዋል። በፍቅሯ ረክቷል፡፡
በውበቷ ነፍሱ ስቃለች። ከእሷ ጋር ያሳለፈው ጊዜ አዳምና ሄዋን ገነት ውስጥ ያሳለፉት ጊዜ ይመስለዋል። እሷን ፍለጋ አምስት ዓመት ለፍቷል። በየቀኑ ከማማርና ከመቆንጀት ባለፈ ግን እንከኗን ሊደርስበት አልቻለም። በዘመኑ ሁሉ የምታስገርመው ሴት ናት። ሰው እንዴት ያለ አንዳች እንከን ይፈጠራል? ሲል ራሱን ደጋግሞ ጠይቆ ያውቃል። ስታወራ ትገለዋለች፣ ስትስቅ ታስደንቀዋለች። ዝም ስትል፣ ስትኮሳተር በዚህ ሁሉ ውስጥ ያፈቅራታል፡፡
ለአስር ሰው የሚበቃ ረጅም አንገት አላት። ጀርባዋ ላይ የተጎዘጎዘ ረጅም ጸጉር፤ ጠዋትና ማታ የሚቀባባ አይንና ከንፈር። እንደ ሰንበሌጥ የቀጠነ ወገብ፣ አይን ከማያስነቅል ዳሌ ጋር ፣ እንዲህ ናት።
በመቃ አንገቷ ላይ ሃምሳ ግራም የአንገት ሀብል አድርጋ እንደ ጥርኝ ዝባድ ከርቀት የሚያውደውን ሽቶዋን ተቀብታ ወደ እሱ ስትመጣ የሚማርከው ምንም አልነበረም። አምራና ተውባ ከመላዕክት ወገን የሚመስል ሳቋን እየሳቀች በሚያያት እልፍ ወንድ መሀል አልፋ ከንፈሩን ስትስመው የሚሰማውን ኩራት መቼም አይረሳውም።
በህይወቱ በእሷ ነው የተባረከው። ማንም ያልሳቀውን ሳቅ ስቋል። ደግሞም ማንም ያላዘነውን ኀዘንም አዝኗል። እሷ ገነቱም ሲኦሉም ናት። ያልዋሸችው ጊዜ አልነበረም። ከነውሸቷ ነበር የሚያፈቅራት። ከነበደሏ ነበር የሚከተላት። እየከዳችው እያታለለችውም ይወዳት ነበር። ከማንም ጋር ውላና አድራ ስትመጣ ስቆ ይቀበላታል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ስትተዋወቀው በውሸት ነበር። እንደ እሷ ውሸት የተካነ አያውቅም። ጭፈራ ቤት ከወንድ ጋር እያያት እናቴ ታማ ሆስፒታል ነኝ ብላው ታውቃለች። አንድ ቀን ለስራ ጉዳይ ከከተማ ወጣ ብሎ ነበር እመለሳለሁ ሳይላት ድንገት ቤት ሲመጣ መኝታ ክፍሉ ውስጥ ከማያውቀው ወንድ ጋር ስትባልግ አገኛት።
ከዛን ጊዜ ወዲህ አይቷት አያውቅም። በስራዋ አፍራ ነው መሰለኝ እንደ ወጣች አልተመለሰችም። እሱ ግን በመሄዷ ዛሬም ድረስ ይከፋል። እንደዛም እየሆነች ባሏ ሆኖ መኖርን ይፈልግ ነበር።
እንዲህ እያሰበ ከጎኑ የሆነ ደስ የሚል ሽቶ አወደው። አልዞረም፣ ከነሃሳቡ ነው…. አዲሳባን እያያት። መክሊትን እያሰበ። እንዲህ የምታውደው እሷ ነበረች፣ ጠይሟ መክሊት፡፡
‹ከኋላ ሂሳብ›። የረዳቱን ድምጽ ሰማው። እሱን እንደሆነ አልጠፋውም። በረዳቱ ድምጽ ከሃሳቡ ወጣ። አጠገቡ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየ። መላ ሰውነቷ በዝምታ ውስጥ የሚስቅ መልከመልካም ሴት። ከመላዕክት ጎን የተቀመጠ ነው የመሰለው። ቆንጆ ማየት ይወድ የለ፣ እስካሁን ሳያያት በመቅረቱ ተቆጨ። የሚያስጠላ አንድም የሰውነት ክፍል የላትም። ልጅ ናት፣ አንድ ፍሬ። ሃያዎቹ ግድም። እንደ ንጋት ሰማይ ፍክት ያለ ቆዳ አላት። ማንም የሚያየው ውበት። ነፍሱ ቃተተች። ተገርሞ ሳያበቃ..
‹ጀለሴ ሂሳብ ክፈይና ትመሰጫለሽ› የረዳቱ ድምጽ ዝምታውን ሰብሮ ገባበት፡፡
ምን አባክ ትጮሃለክ በሚል አስተያየት እያየው ሂሳቡን ከፈለ፡፡
አጠገቡ የተቀመጠችውን ሴት በቆረጣ አያት። በዝምታ እየሳቀች አገኛት። በዝምታ የሚስቅ ብዙ ውበት አላት። የሰከነ ግን ደግሞ የሚያረካ፣ ዝም ያለ ግን ደግሞ የሚናገር ተፈጥሮ። የሆነ ውብ ህልም ውስጥ ከተተችው። መጀመሪያ መክሊትን ያያት ቀን እንዲህ እንደ አሁኑ ሆኖ ነበር።
ቆንጆ ሴቶች ከቁንጅና ሌላ ምንም የላቸውም የሚለው ታዲዮስ በሃሳቡ መጣ። ታዲዮስ እንደ ሲግመንድ ፍሩድ በሴት ልጅ ተፈጥሮ ላይ ግራ የተጋባ እስካሁንም ድረስ የሴት ነፍስ ምን እንደምትፈልግ ያላወቀ ወርቅ እየሰጠ ጠጠር የሚቀበል፣ እያፈቀረ የሚከዳ ወጣት ነው። እሱም መክሊትን ቀርቦ እስከተከዳበት ጊዜ ድረስ የታዲዮስ ፍልስፍና እብደት ይመስለው ነበር፣ ቢሆንም ግን በሴት ልጅ ተስፋ ቆርጦ አያውቅም፡፡
አያት እንደ ቅድሙ ናት፣ በዝምታ በሚስቅ ፊት። ሽቶዋ ነፍሱ ድረስ ገባ። ታክሲው ውስጥ የተከፈተው የዘጠኝ ሰአቱ ዜና ስለ ኮሮና ቫይረስ ይተነትናል። ከአስራ ሁለቱ ተሳፋሪዎች ግማሾቹ ጆሯቸውን ለዜናው ሰጥተዋል። የተቀረው ስለ ኑሮ መወደድ፣ ስለ ስራ መጥፋት፣ ስለ ትምህርት ቤት መዘጋት እንዲህ ያስባል። እሱ አጠገቡ ስላለችው ቆንጆ ሴት ያሰላስላል። የእሷን ሃሳብ አምላክ ይወቀው ግን እንደ ቅድሙ ናት ፣ በብዙ ውበት በብዙ ዝምታ፡፡
ዝም ብሎ ሊለያት አልፈለገም ሁሉም ሴቶች አንድ አይደሉም ምናልባት በዚች ሴት እባረክ ይሆናል ሲል አሰበ። ዝምታዋ አስፈራው፣ ወንድ ላለማናገር ምላ ከቤት የወጣችም መሰለው። የሆነው ይሁን እንጂ ዛሬ ሳያናግራት አይቀርም። የሰአቱን ዜና ታኮ ወሬ ቢጀምርላት ጥሩ እንደሚሆን አሰበ። ‹በኮሮና ላለመያዝ ከወንድ ይልቅ ሴት መሆን የተሻለ እንደሆነ ታውቂያለሽ? ሊላት አፉን ሲከፍት የሆነ ሃሳብ መጣለት። ለምን ስለቁንጅናዋ፣ ስለ ተቀባችው ሽቶ አልነግራትም ብሎ ‹ሽቶሽ በጣም ደስ ይላል› አላት፡፡
‹አመሰግናለሁ› ፈገግታ በመከነበት ፊት መለሰችለት።
‹ሽቶ የሚወዱ ሴቶች ምን አይነት ስብዕና እንዳላቸው ታውቂያለሽ?
‹አላውቅም› እንዲነግራት በመጓጓት ወደ ጎን ዞራ እያየችው።
ሴቶች ስለራሳቸው መስማት እንደሚወዱ ያውቃል። የትኛዋም ሴት ስለ ውበቷ የሚነግራትን ወንድ ገፍታ አታውቅም። ‹የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ….ስሜቷን ለማየት ቆመ፡፡
ፊቷ ላይ ጉጉት ተፈጠረ። እንደ ዛሬ ወሬ ለመስማት ጓጉታ አታውቅም። አይን አይኑን…ከንፈር ከንፈሩን እያየች ጠበቀችው፡፡
‹ሽቶ በጣም ነው የምወደው..› ሳይጠይቃት ተናገረች።
እያሸነፋት መሰለው። በዚች ሴት መባረክ አለበት። ማሸነፊያ ቃላት በመመራረጥ ላይ ሳለ ስልኳ ጮኽ፡፡
ቦርሳዋን በርብራ አነሳችው፡፡
‹የኔ ማር የት ነሽ? የአንድ አፍቃሪ ወንድ ድምጽ ተሰማ።
‹የጓደኛዬ እናት ታመው ሆስፒታል ነኝ›፡፡
ጠላት። የወደዳትን ያህል ተጸየፋት። ቆንጆ ሆና መልካም ሴት እግዜር አልፈጠረም ይሆን? ራሱን እንዲህ እየጠየቀ ያለመውረጃው ቦታ ትቷት ወረደ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013