አይለወጤው የእናት ፍቅር የሚጀምረው በምጥ ወቅት ነው ይባላል። ምጥ ለእናት ትልቅ ፈተና፤ ትልቅ አይረሴ ትዝታ ነው። ታዲያ ጉዳዩ ትዝታ ብቻ ሆኖ አያልፍም አንዳንዴ አስፈላጊው እንክብካቤና ጥንቃቄ ካልተደረገ ከደም መፍሰስ ጋር በተያያዘ እናትንም ሆነ ህፃኑን ለከፋ ጉዳት ይዳርጋል። ምጥ ዛሬም ድረስ ለከባድ ችግሮች መገለጫ እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህም ነው አንዳንድ እናቶች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር ሲገልፁ «አምጬ የወለድኩት ነው» ሲሉ የሚደመጡት።
እናት ለልጇ ያላት ፍቅር ውሎ ሲያድር ይጨምራል እንጂ አይቀንስም። አስር ወልዳ ቢሆን እንኳ ለአስራ አንደኛው ያልተነካ አዲስና ንፁህ ፍቅር ይኖራታል። ምክንያቱም አምጣ ነውና የምትወልደው። የአንድ እናት ህይወት ህልፈት ደግሞ ለጨቅላው ህፃን ብቻ ሳይሆን ለመላው ቤተሰብ የችግር መነሻ ይሆናል። እናም እናትን መንከባከብ ቤተሰብን መንከባከብ፤ ብሎም ፍቅርንና ሀገርም መንከባከብ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ሰሞኑን የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በየዓመቱ የሚከበረውን የጤናማ እናትነት ወርን አስመልክቶ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ይህው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላሳኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ13ተኛ ጊዜ የተዘጋጀውና «በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል» በሚል መሪ ቃል ነበር የሚከበረው። የጤናማ እናትነት ወር ዋና ዓለማው ለእናቶች ክብካቤንና ጥበቃን ለማድረግ ግንዛቤን ማስጨበጥ ታሳቢ ተደርጎ ነው። በተለይም እናቶች በእርግዝና ወቅት በወሊድ ጊዜና የተለያዩ ጥቃቶችን ተከትሎ ለከፋ ችግር ይዳረጋሉ። ለችግር የሚዳርጓቸውን ሁኔታዎች ቀድሞ በማወቅ ለመቀነስ እንዲቻል ለህብረተሰቡም ሆነ ለእናቶች ግንዛቤ መፍጠርን አላምው ያደረገ መድረክ ነበር።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር መሰረት ዘላለም በውይይቱ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፤ የዓለም ጤና ድርጅት እ.አ.አ በ2016 ያወጣው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በዓመቱ ውስጥ ከ3 መቶ ሺ በላይ እናቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሲታይ ደግሞ እ.አ.አ በ1990 ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው የሚያልፈው እናቶች ቁጥር በዓመት 1ሺ250 ይደርስ ነበር። ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ይሄንን ቁጥር ለመቀነስ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል። በአሁኑ ወቅት የሞት ቁጥሩን ወደ 353 በማውረድ ህይወታቸው የሚያልፈውን እናቶች 72 በመቶ ለመቀነስ ተችሏል። ይሁን እንጂ ዛሬም ጥቂት የማይባሉ እናቶች በወሊድ ምክንያት ለሞት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
የሚያሳዝነውና ትኩረት የሚፈልገው ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ለእነዚህ እናቶች ሞት ምክንያት የሚሆኑት አብዛኞዎቹ ችግሮች መከላከልና መዳን የሚችሉ መሆናቸው ነው። ከነዚህም መካከል ሃምሳ በመቶ የሚሆነው በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ጊዜና እንዲሁም ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰት ነው።
በአጠቃለይ እናቶችን ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለህልፈተ ህይወት እየዳረጉ ያሉት ችግሮች በተገቢው መንገድ አለመቀነስ ሶስት መሰረታዊ ምክንያቶች መኖራቸውን ዳይሬክተሯ ይናገራሉ። የመጀመሪያው በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ማነስ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ እናቶች ከእርግዝና ወቅት ጀምረው አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የቤት ውስጥ እንክብካቤ አይደረግላቸውም።
በሁለተኛነት ዛሬም ድረስ በከተሞች መሻሻል ቢታይም በተለይ በገጠሩ አካባቢና በከተማም አንዳንድ እናቶች በቤት ውስጥ ለመውለድ ሙከራ የሚያደርጉ በመኖራቸው ነው። በሶስተኛነት ደረጃ ደግሞ እናቶች ዘግይተውም ሆነ በወቅቱ የጤና ተቋማት ከደረሱ በኋላ የሚገጥማቸው ችግር ነው። ከቁሳቁስ እጥረትም ሆነ ከባለሙያ ስነ ምግባርና አቅም ጋር በተያያዘ ተገቢውን አገልግሎት ባለማግኘታቸው የችግሩ ሰለባ ሲሆኑ ይታያሉ።
በመሆኑን ይህን ችግር ለማቃለል በማህበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ በመፍጠርና በማስተማር ህብረተሰቡን ማንቃት ይገባል። በጤና ተቋማትም አስፈላጊውን ቁሳቁስ በማሟላትና በሆስፒታል ያሉ ባለሙያዎችን ስነምግባርና ክህሎት በማዳበር መቆጣጠር ይቻላል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ይህን ለማድረግ ከፌዴራል እስከ ወረዳና ማህበረሰቡ ድረስ በተዘረጋ መዋቅር እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ዶክተር መሰረት ጠቁመዋል።
«በሀገር አቀፍ ደረጃ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ ቢሆንም ከሚጠበቀው አንፃር ግን ብዙ መስራት ይቀራል» የሚሉት ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስትር የእናቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ አቶ ዘነበ አካለ ናቸው። አቶ ዘነበ እንደሚያብራሩት፤ ባለፉት ሁለት አሰርት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች እንደ ሀገር ትልቅ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።
ያለውን ለውጥ ግን እንደ ሀገር ለማየት አይቻልም። ምክንያቱም በሀገር ውስጥም ሆኖ ሰፊውን የለውጥ ድርሻ የሚይዘው በከተማ ያለው ነው። በመሆኑም በገጠርም ተደራሽ እንዲሆን መስራት ይጠበቃል። ከሌሎች ያደጉ ሀገራት ጋር በንፅፅር ሲታይም ዛሬም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለምሳሌ በአሜሪካ ከ3 ሺ 400 እናቶች አንድ እናት ትሞታለች። በኢትዮጵያ ደግሞ ከ37 እናቶች አንዷ ትሞታለች። በአሜሪካ ሀገር ተደራሽነቱም ጥራቱም የተጠበቀ በመሆኑ ቁጥሩ አይቀንስም አይጨምርም። በኢትዮጵያ ግን እየቀነሰ ቢሆንም አካሄዱ ዘገምተኛ ነው። በየትኛውም ሀገር የእናቶችን ሞት ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት አይቻልም። ነገር ግን መቆጣጠር የሚቻለውን አለመቆጣጠር ክፍተት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ዘነበ ገለፃ ከሆነ፤ኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ከሚያልፈው እናቶች አብዛኛዎቹ በወቅቱ የህክምና አገልግሎት ካለማግኘታቸው ጋር የሚያያዝ ነው። ከከተማ ውጪ ያሉት አብዛኛዎቹ እናቶች እቤት ለመውለድ ሞክረው ብዙ ደም ከፈሰሳቸውና ከተጎዱ በኋላ ወደ ጤና ተቋም ይመጣሉ። ቀሪዎቹም እናቶች አገልግሎቱን አውቀው ለማግኘት ፈልገው ነገር ግን ወደ ጤና ተቋማት ጉዞ የሚጀምሩት ምጥ ከጀመራቸው በኋላ ነው። በመሆኑም በመንገድ ርቀትና ምቹ ባልሆነ ጉዞ ከተጎዱ በኋላ ጤና ተቋም ይደርሳሉ። ስለዚህም በወቅቱ ጤና ተቋም እንዲደርሱ ማድረግ ቢቻል70 በመቶ የሚሆኑትን መታደግ ይቻላል።
ጤና ተቋም ከገቡ በኋላ በፍጥነት አገልግሎት አለማግኘት። በኢትዮጵያ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን እናቶች በየዓመቱ ያረግዛሉ። ከነዚህ ውስጥ መከላከል የማይቻለው እንዳለ ሆኖ መከላከል የሚቻለውን ለመቆጣጠር ጠንካራና ተደራሽ የሆነ ስራ መስራት እንደሚጠበቅ ያስረዳሉ።
የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታምሩ አሰፋ በበኩላቸው፤ ዛሬም ድረስ በዓለም ላይ 830 እናቶች በየቀኑ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት ይዳረጋሉ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 99 በመቶ የሚሆኑት በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ባሉ እናቶች ላይ የሚደርስ ነው። የዚህ ሃምሳ በመቶ ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የሚከሰት ነው። በዓለም ላይ በየዓመቱ 14 ሚሊዮን እናቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ በወሊድ ጊዜና ከወሊድ በኋላ የደም መፍሰስ እንደሚያጋጥማቸው ይናገራሉ።
የደም መፍሰስ ችግር ደግሞ ተተኪ ደም እስከተገኘ ድረስ እናቶች ለህልፈተ ህይወት ሊዳረጉ አይችሉም። የደም እጥረት አስቸጋሪና ለሞት የሚዳርግ ችርግ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ ያለማንም እርዳታ በህብረተሰብ መልካም ፈቃድና ተሳትፎ የሚገኝ መሆኑ ደግሞ አንድ ተስፋ ነው። ለዚህም የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ከዓመት እስከ ዓመት የሚቆይ የደም ልገሳ ፕሮግራም ይዘጋጃል። በመሆኑም ህብረተሰቡ በቀላል ድጋፍ የእናቶችን ህይወት መታደግ እንደሚችል በመገንዘብ በደም ልገሳ ሊሳተፍ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
«ስለ እናት ህይወት መመካከር፤ ስለጨቅላ ህፃናት ብሎም ስለመላው ቤተሰብ መመካከር ነው» ያሉት ዶክተር ታምሩ፤ በቤት ውስጥ በእርግዝና ጊዜ ለእናቶች ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ። አንዲት እናት ጤና ጣቢያ ከደረሰች በሰላም እንደምትገላገል እርግጠኛ መሆን እንዳለብን ማስተማር ይገባል። እርግዝናቸውን ካወቁ ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ አራት ጊዜ ክትትል በማድረግ በሀኪሞች የሚሰጠውን ትእዛዝና ምክር በአግባቡ መተግበርም ይገባል።
አዳዲስ ምልክቶች ሲኖሩ ወደ ጤና ተቋም መምጣት። ከወለዱ በኋላም ቢያንስ 24 ሰአት በጤና ተቋም ማሳለፍ። እንዲሁም እናቶች በእርግዝና ወቅት በጤና ተቋማት የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ማስተማር የሁሉም ሀላፊነት መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
በህብረተሰቡ ዘንድ የት? ምን? አገልግሎት እንደሚሰጥ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ታምሩ፤ ለምሳሌ የቅዱስ ጴጥሮስ ቲቢ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚታወ ቀው ከቲቢ በሽታ ጋር ብቻ እንደሆነ ይታሰባል። በመሆኑም በተሟላ መሳሪያና የሰው ሀይል ለረጅም ጊዜ የማዋለድ አገልግሎት ጀምሮ የቆየ ቢሆንም የሚመጣ ተገልጋይ አልነበረም።
ከአምስት ዓመት በፊት በዓመት በሆስፒታሉ የሚወልዱት እናቶች ቁጥር ከሁለት መቶ ያልበለጠ ነበር። በተደጋጋሚ በተደረገው የማስተዋወቅ ስራ ዘንድሮ ባለፈው ስድስት ወር ብቻ አንድ ሺ700 እናቶች አገልግሎቱን ማግኘት ችለዋል። የማስተማሩና የማስተዋወቁ ስራ እንደተጠበቀ ሆኖ በአዲስ አበባና በከተሞች የተጀመረው የቁሳቁስም ሆነ የባለሙያ ድጋፍ በክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠል እንደአለበትም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ