ጌቴሴማኔ ዘ-ማርያም
የዘንድሮን የዓድዋን በዓል ሲያከብር የዛሬ 125 ዓመት ወደ ኋላ መለስ ብሎ የማያስታውስና የጥንቶቹን የማያመሰግን ዜጋ ካለ እሱ ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ ለመጥራት አያስፈድርም፡፡ ወይም ይሄ ዜጋ ዛሬ የቆመባትን ሀገር ታሪክ አያውቅም። አለዚያም ይህችን ዛሬ የቆመባትን ምድር ትተውለት የሄዱትን ጀግኖች መሪዎች፣ አባትና እናት አርበኞች ብሎም ለሀገራቸው ህልውና ሲሉ በየትኛውም ግንባር ውድና የማይተካ ሕይወታቸውን ገብረው ያለፉትን መላ ኢትዮጵያዊያኖች በሙሉ የሚክድ የበላበትን ወጪት ሰባሪ ነው። ወይም የዛሬ 125 ዓመት ከፋሽሽት ኢጣሊያ አስተሳሰብ ጋር በማበር የገዛ ሀገሩን ለወራሪ ጠላት አሳልፎ የሰጠ ባንዳ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።
በእርግጥ ዛሬ ከ125 ዓመት በኋላም እንዲህ ዓይነቶቹ ዜጎች አይጠፉም። ትላንትም ግጠው ሲያስግጡ የኖሩበትን ልማድ የማይዘነጉ አሉ። ዛሬም መጥምጠው የተውትን የእምዬን ኢትዮጵያ ደረቅ ጡት ዳግመኛ ለብቻቸው ለመመጥመጥና ለማስመጥመጥም የሚቋምጡ እንደ ጁንታውና ተከታዮቹ ዓይነት ፍጡራን ይኖራሉ።
ጎበዝ! ለአብነት እስኪ በየአካባቢያችን ከምንሰማውና ከምናየው እናንሳ። ማን ይሙት ሰው ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመወለድ ‹‹ኮባ ሆኖ አሜሪካን ውስጥ መብቀል›› የሚመኝ በቅኝ አስተሳሰብ የተገዛ አሳፋሪ ዜጋ የለም።
ዕውነት ዛሬስ ላቡን ጠብ አድርጎ ሰርቶ የገጠመውን የኢኮኖሚ ችግር ከመወጣትና ድህነቱን ከማሸነፍ እጁን አጣጥፎ ቁጭ ባለበት መክበርን በመናፈቅ በአጉል ምኞት የሚዳክር ዜጋ የለም ? እኔ እንዳስተዋልኩት እንዲህ ዓይነት ትውልድ እንዲህ ዓይነት ወጣት አሁንም ሀገራችን ውስጥ አለ።
ሆኖም ግን ሁልጊዜ ወቃሽ መሆን ጥሩ አይደለምና አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ወጣቶችም እንዳሉ በአንድ ወቅት የገጠመኝን ሁኔታ ማስታወሱ በቂ ነው፡፡
ቀኑ የካቲት 12 ነው፡፡ ከስድስት ኪሎ ካዛንቺስ እየሄደ ባለ ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬያለሁ። ጊዜው ከቀትር በኋላ ነበር። ከወደ በስተኋላተማሪዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያወሩ ይሰማሉ፡፡ ዕድሚያቸው በታዳጊነትና ወጣት ደረጃ ይገኛል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ይመስላሉ።
ጨዋታቸው በዕለቱ በዓሉ የተዘከረበትን የሰማዕታት ቀንን የተመለከተ ነበር። የብዙ ተሳፋሪዎችን ቀልብ በመሳቡም የወጣቶቹ ጨዋታ እየጎላ ሲመጣ የተሣፋሪው ድምፅ ፀጥ አለ። ጨዋታው በዝግታ የሚያሽከረክረውን የታክሲ ሹፌሩን ቀልብ ሁሉ ለመሳቡ ሹፌሩ ፍጥነቱን ቀንሶ በዝግታ ማሽከርከር መጀመሩን ማስተዋል ብቻ ይበቃል። በፋሺስት ኢጣሊያ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጨፈጨፉትን 30 ሺህ ዜጎች እያነሱ በመሆኑ ደስ አለኝ።
ዕውነት ለመናገር እኔ በአርባ ምናምን ዓመቴ ዜጎቹ የተጨፈጨፉበትን ዓ.ም ቢጠይቁኝ መዛግብት ካላገላበጥኩ አስታውሼ አልናገርም። ‹‹የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም›› ሲሉ ደስ ብሎኝ ጆሮዬን ለታዳጊዎቹና ወጣቶች ሰጠሁ። ከጨዋታቸው የዕለቱ ውሏቸው ለተጨፈጨፉት ዜጎች መታሰቢያ የተሰራው ሀውልት መሆኑንም ተረድቻለሁ።
ሃውልቱ ጋር የተነሱትን ፎቶ ሁሉ ከየሞባይላቸው እያወጡ ያዩ ነበር። አንዱ ወጣት ከመካከላቸው ከአርበኞች የአርበኛ ጎፈሬና ልብስ ተውሶ በመልበስ ሲሸልል የተነሳውን ምስል ካዩ በኋላ ታክሲ ውስጥ ቀረርቶና ሽለላ ሁሉ ጀምረው ነበር።
በዚህ መካከልም ጨዋታቸው ወደ ሌላው በዘመናዊው ዓለም የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ከሚነሳባቸው ክስተቶች መካከል አንዱ ለመሆን ወደ በቃውና ዘንድሮ ለ125ኛ ጊዜ ወደ የሚከበረው የዓድዋ ድል ታሪክ ተሸጋገረ። የዓድዋ ድል ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መነቃቃትንና ተስፋን የሰጠ ክስተት መሆኑ ፤ድሉ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የአፍሪካ ድል መሆኑን ወጣቶቹ ተስማምተዋል ።
በድሉ የጎላ ድርሻ የነበራቸውን ዳግማዊ አፄ ምኒልክንና ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱንም አነሱ። የዓድዋ ጦርነት በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ የአፄ ሚኒልክ የክተት አዋጅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን ታሪክ ፀሐፊዎችን ዋቢ አድርገው ሁሉ በመናገራቸው ወጣቶቹ በዓድዋ ላይ ጥሩ የዕውቀት መሰረት እንዳላቸው መገመት ይቻላል ።
በተለይ ባለቤታቸው በጦርነቱ ወቅት ኢጣሊያን ውሃ እንዳታገኝ ያደረጉትን ታሪክ ሲተነትኑት ታሪክ አዋቂ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክ ፀሐፊም ይመስሉ ነበር። በዘመኑ የነበሩ ባንዶች ለጦርነቱ መከሰትም ሆነ ለድሉ ፈተና እንደነበሩም ሳያሰምሩበት አላለፉም። ወጣቶቹ ቀላል አልነበሩም።
ስማቸው በባንድነት የሚነሳ የአንድ ሁለት ሰዎችንም ስም ጠቀሱ። ጨዋታው የጣማቸው ከማይመስሉት ሁለት ተሳፋሪዎች መካከል አዛውንት የሚመስሉት አንዱ ‹እከሌ ነው ባንዳ ›በማለት በንዴት ብው ብለው ተነሱ። ወጣቶቹ ታሪክ ጠቅሰው ሊያስረዷቸው ቢሞክሩም አልሰሟቸውም ።ወደ ኋላ ወደ ወጣቶቹ ዞር ብለውም መሳደብ ጀመሩ። በስድብቻው ውስጥ ወጣቶቹ ታክሲ ውስጥ ያሰሙት በሀገር ፍቅር ስሜት የተሞላ ፉከራና ቀረርቶ ተሳፋሪውን የሚረብሽ ህገወጥ ተግባር መሆኑን ያነሱ ነበር።
በሽማግሌው ሁኔታ የተበሳጨችው ተሳፋሪ በምፀት ሳቅ አጀባችው።ይባስ ብለው የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱን በድሉ የነበረ የአመራርነትና የዜግነት ድርሻ የሚያንቋሽሽ ቃላት መናገር ሲጀምሩ። ታክሲው ተቀወጠ።
ተሳፋሪው አዛውንቱን አላናግር አላቸው። ከጎናቸው የነበረው ወጣቱ ልጅ እየተበሳጨ እየገሰፀም ‹‹ገና መውረጃዬ አልደረሰም›› በማለት አሻፈረኝ ቢሉትም እጃቸውን እየጎተተ ይዞልን ወረደ። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ዕድሜ ሲገፋ በተለይ ሌላውን አጥፍቶ ያስጠፋል።ዛሬ ላይ በገዛ ስንፍናውም ሆነ ዕድል ሳይቀናውና ሁኔታዎች ሳይመቻችለት ቀርቶ ሥራ መፍጠር ባይችል ቢያንስ ንፁህ አየር እየተነፈሰ የሚኖርባት ሀገር አስረክበውናል፡፡
አያቴ ነፍሳቸውን ይማረውና ይሄን ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ብዙ ወጣቶች መክረው አስተሳሰባቸውን ያቀኑ ነበር። እስከ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ጣሊያን ቢኖር እነሱ የመኖር ህልውና እንደማይኖራቸው እንኳን የማያገናዝቡ ከንቱ ግለሰቦች ቁጥር ቀላል አይደለም። አያቴ ይሄንንም አስታውሰው በማንሳት ይመልሱ ነበር። በተለይ ያኔ በኢጣሊያን ጊዜ ያዩትን ዕውነታ ጠቅሰው አመለካከት ያቀኑ የነበረበት ተሞክሩ በፍፁም አይዘነጋኝም።
በወቅቱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ጣሊያኑ ጎረቤታቸው መፀዳጃ ሲጠቀም ቦርሳው ፓስፖርቱን፣ አለኝ የሚለውን ገንዘቡንና አድራሻዎች እንደያዘ መፀዳጃው ጉድጓድ ውስጥ ይገባበታል። ያኔ የእሳት አደጋ መኪና የሚባል አልነበረም።
ታዲያ አማራጭ ያጣው ጣሊያን ሆዬ ቦርሳውን እንዲያወጣለት አበሻውን ዘበኛ በገመድ አስሮ ወደ መፀዳጃው ጉድጓድ ይሰድደዋል።ጣሊያን ተዋርዶ ባይወጣ ኖሮ አሁንም የኢትዮጵያውያን ዕጣ ፋንታ ተመሳሳይ ይሆን ነበር፡፡ ወገን!‹‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ ሀበሻ›› የሚለውም ግጥም መልዕክቱ ብዙ ነው፡፡ በመሆኑም ዓድዋን በውለታው ደርዝ እናስታውስና እናክብረው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2013