እፀገነት አክሊሉ
ዓድዋ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካ፣ የጥቁር ህዝብ ታሪክ ነው። የካቲት 23/1988 አ.ም ሀገር ወራሪው ጦር በምሥራቅ አፍሪካ አከርካሪው የተመታበት ዕለት። የአለም ድሃ ሀገሮችን የናቀና ጦር መሣሪያውን የተማመነ ኃይል በጋሻ ጎራዴ የተንበረከከበት፣ የነፃነት ጮራ ከወደ ምሥራቅ አፍሪካ የፈነጠቀበት፣ ታሪካዊ የድል ቀን ዓድዋ። በ1882 አ.ም. ጥቅምት ወር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሱት የኃይለ መለኮት ልጅ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ስም በአለም ያስጠሩ ጀግና መሪ ነበሩ። ምኒልክ ንግሥናቸውን እንዳገኙ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ውል ከኢጣልያ ጋር የተደረገው ነበር። ይህም የስምምነት ውል የውጫሌው ውል በመባል ይታወቃል።
የውጫሌ ውል አንቀጽአሥራ ሰባት የጣሊያንኛው ግልባጭ፡-“ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት በኩል ማድረግ አለባት” ሲል፤ አማርኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች“ ይላል። የአማርኛው የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና ሲያስከብር በተቃራኒው የጣሊያንኛው ትርጓሜ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ልዕልና መድፈር ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል። የዳግማዊ ምኒልክ የአርቆ የማሰብ ችሎታ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዳትገባ ጥረት በማድረግ ነፃነታቸውን ጠብቀው ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነትንና ምክር መቀበል ቀጠሉ። በዚህም የተነሳ ኢጣሊያም ኢትዮጵያን ለመያዝ ቁርጥ ሀሳብ አድርጋ በኤርትራ በኩል ትግራይን መውረር ጀመረች።
ምኒልክም ሕዝቡን ለጦርነት ክተት አሉ። ታሪካዊው የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ ነጋሪት እየተጎሰመ ተላለፈ። በጊዜው እንዲህ ተደምጧል፦ “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልምርህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኹሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።”
ጣሊያኖች በጄኔራል ባራቲሪ የሚመራውን 20 ሺህ ወታደሮቻቸውን ይዘው በ1888 አ.ም.የካቲት 23 ቀን ዓድዋን ወጉ። ከ 80 ሺህ እስከ 120 ሺህ የሚገመተው የምኒልክ /የኢትዮጵያ ሠራዊትም/ በሚገባ ሲዋጋ የሀገሪቱ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥና ሀገሬን ብሎ በቁርጠኝነት ስሜት ቀፎው እንደተነካ ንብ የተነቃነቀው ኃይል የጠላትን ጦር አደናግጦ መግቢያ መውጫ በማሳጣት ቀኑን ሙሉ ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላ በሚያስደንቅ አኳኋን ድሉ የኢትዮጵያ ሆነ። ቅኝ አገዛዝ እግሬ አውጪኝ ሲል ነፃነት ከፍ አለ።
በምኒልክ መሪነት ሕዝብ ታሪክ ሰራ። ለጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ጮራው ፈነጠቀ። ኢትዮጵያ በልጆቹዋ ደምና አጥንት ሉአላዊነቷን አረጋገጠች። ልክ የዛሬ 125 አመት። ዓድዋን መለስ ብለን ስናስብ ምን እንማራለን ስንል በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ለሆኑት ዶክተር ከተቦ አብዮ ጥያቄዎችን አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፦ ዓድዋን መለስ ብለን ስናስብ ምን ትምህርት እወስዳለን ከሚለው እንነሳ፤
ዶክተር ከተቦ፦ ዓድዋ አለም አቀፋዊ ድል ነው። ነጮችን ያስጠነቀቀ ከዛም ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የነበራቸውን አተያይ እንዲፈትሹ ያደረገ ነው። ከዛ በፊት አፍሪካ እንደጨለማ አህጉር ይታይ ነበር፤ በጦርነቱ ወቅት የነበረው እንግሊዛዊ ጸሀፊ ጆርጅ በርክሌም ከዛሬ በፊት አፍሪካን እንደ ጨለማ አህጉር እናይ ነበር አሁን ግን ይህ አስተሳሰብ ቀርቷል ፤ አዲስ ሀይልም መምጣቱን ያሳያል ብሎ ጽፏል። ይህ እንግዲህ ለጥቁር ህዝቦች ያለው እንደምታ ቀላል የሚባል አይደለም። ለምሳሌ ጥቁሮች በአሜሪካ በደቡብ አፍሪካ በሌሎችም አካባቢዎች የነበረባቸውን ችግር ወዲያ ጥለው ለድል እንዲነሱም ያደረገ ነው።
በተለይም ለአፍሪካ ያለው እንደምታ በጣም ትልቅ ነው። የዓድዋ ደል የተጎናጸፍንበት ጊዜ አፍሪካን ሳንጣላ እንቀራመታት ያሉበት ጊዜ ነው። በዚህም የተነሳ መላው አፍሪካ በቀኝ ገዢዎች ቀምበር ስር የገባበት ጊዜም ነበር። ዓድዋ ግን ይህንን ሁኔታ ገለበጠ። ከአፍሪካም ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ብቻ ናቸው ነጻ አገር የሚባሉትም በዚህ ምክንያት ነው። የኢትዮጵያ ግን በተጋድሎ የተገኘ ነጻነት ስለሆነ የተለየ ነው።
ስለዚህ ዓድዋ በመላው አለም ላሉ ጥቁር ህዝቦች የሞራል ምንጭ ፣ የነጻነት ምልክት ነው። እንደውም ይህ ድል ለጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ለጃፓናውያን ራሱ ራሺያ በንቀት ያወጀችባትን ጦርነት በድል እንድታጠናቅቅ ካደረጋቸው ነገሮች መካከል የዓድዋ ድል ይጠቀሳል። በመሆኑም በመላው አለም ተጨቁነው ለነበሩ ህዝቦች በሙሉ የሞራል ምንጭ ነው ዓድዋ።
በዓድዋ ድል በመነቃቃትም በአፍሪካ ታዋቂ መሪዎች የነጻነት ተጋድሎ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። እነ ጆሞ ኬንያታ ኩዋሚ ንኩሩማና ሌሎችም ኢትዮጵያ በአለም ላይ የነጻነት ትግል ምልክት ሆና እንድትታይ ትልቅ ድጋፍ አድርገዋል። በኋላም ፓን አፍሪካኒዝም ምስረታ ላይ ዓድዋ ትልቅ አስተዋጽዖ ነበረው። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ እንዲሆን አብዛኛው የአፍሪካ አገራት ሰንደቅ አላማ አረንግዴ ቢጫና ቀይ እንዲሆን በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽዖ ከማበርከቱም በላይ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ህዝቦች በተሻለ መልኩ በራስ መተማመን እንዲኖረን አድርጓል።
ዛሬ ላይ በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ከአለፉ የአፍሪካ አገሮች አንጻር የእኛን ስነ ልቦና ብናይ የተለየ ነው።ለነጮች ያለን ግምት ራሱ በጣም ይለያል። በመሆኑም የዓድዋ ድል የሁላችን አያቶቻችን ውጤት መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ዓድዋ ከአገራዊ ነጻነቱ ባሻገር ለቀኝ ግዛት ማብቃት የነበረው አስተዋጽዖ እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ከተቦ፦ ከዓድዋ በፊት በነበረው ጊዜ ነጮች ቅኝ ለመግዛት ለማድረግ መሰልጠን እምነትና ንግድ ማስፋፋት የሚሉ መርሆዎችን ይከተሉ ነበር፤ ዓድዋ ደግሞ ይህንን ሁሉ ገለበጠ። እንኳን በአፍሪካ ኤዢያዎቹም ሳይቀሩ ለካ ከታገለን ነጻነታችንን ማግኘት እንችላለን በማለት ተነሳሱ። ከዛ በኋላ ይህንን ስንቅ በማድረግ በ1960ዎቹ ሁሉም የአፍሪካ አገራት ማለት ይቻላል ከጭቆና ቀንበር መላቀቅ ችለዋል።
ከዛ በኋላም በኮንጎ የተላከው የኢትዮጵያ ጦር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በሩዋንዳ ቡሩንዲ ደቡብ ሱዳን በሰላም አስከባሪነት የተሰማራንባቸውን አውዶች ብንመለከት የዓድዋ ድል ከነጻነት ድልነቱ ባሻገር ኢትዮጵያ እምነት የሚጣልባት ሀገር እንድትሆንና የሀላፊነት ሚናንም እንድትጫወት የራሱን አስተዋጽዖ ያበረከተም ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፦ በወቅቱ ለዓድዋ ጦርነት ለቀረበው አገራዊ ጥሪ ሁሉም ከየቦታው በአንድነት መሰባሰቡ ይታወቃል፤ ቴክኖሎጂ በሌለበት የመረጃ ልውውጡም ፈጣን ባልሆነበት በዚያን ወቅት በዚህ ደረጃ የህዝቡ መሰባሰብ ምንን ያሳያል?
ዶክተር ከተቦ፦ ልክ ነው ሚኒልክ ጥሪ ሲያደርጉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሆ ብሎ ተነስቶ ወደ ዓድዋ ዘምቷል። በነገራችን ላይ ከዛ በፊት አጼ ሚኒልክ ከራስ መንገሻ፤ ከንጉስ ተክለሀይማኖት፤ ከራስ ሚካኤል ፎሎ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን ጦርነቱ ሲታወጅ ራስ መንገሻ አዲስ አበባ መጥተው ይቀርታ ጠይቀው ልዩነታቸውን ወደኋላ በመተው ነው ወደ ጦርነቱ የገቡት። ስለዚህ በተለያዩ ነገሮች ብንጣላም በአገር ሉአላዊነት ላይ ልዩነት የለም በማለትም ነው አንድ ሆነው ጠላትን የገጠሙት።
ከዚህ አንጻር አንድነቱ ፍቅሩ ቁርጠኝነቱ ከፍ ያለ ከመሆኑም በላይ አንድ ሆነን ከወጣንም ሁሉንም ነገር ማሸነፍ እንደምንችል ደግሞ የተማርንበትም ነው።
አሁን እኔ የሚያስፈራኝ ምን መሰለሽ እናንተ የምታቀርቧቸው “የታሪክ ምሁራን” ነን የሚሉ ሰዎች የዓድዋን ድል የአንድ ወገን ብቻ አድርገው ሲያወሩ መስማት ነው። ግን ይህ ትክክል አይደለም፤ ድሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ለምሳሌ አባ ጅፋር 60 ሺ ወታደር ነው የላኩት፤ የወላይታው ካዎ ጦና፤ የወለጋው ዳጃች ኩምሳ ሁሉም ተካፍሏል። ትግሬውም አማራውም ደቡቡም ጉራጌውም ኦሮሞውም በጠቅላላው የሁሉም አስተዋጽዖ የነበረበት ነው። ይህንን እንደ ስንቅ አድርገን አሁንም አንድነታችንን አጠናክረን ወደፊት መሄድ ደግሞ ይጠበቅብናል።
በነገራችን ላይ ድል በጦርነት ብቻ አይደለ፤በኢኮኖሚወም በፖለቲካውም በሁሉም ላይ መስራት አለብን ። ታሪክ ያለፈ ቢሆንም ጥሩ ጥሩውን ወስደን በአንድነት ቆመን ወደፊት መሄድ ያስፈልጋል፤አልያ አንድ ቦታ ቆሞ መፎከሩ የትም አያደርሰንም።
አዲስ ዘመን ፦ በተለይም በዓድዋ ጦርነት ወቅት የነበረንን አንድነት መተባበርና የድል አድራጊነት ስሜት አሁን መድገም ያልቻልነው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ከተቦ፦ ብዙ ችግሮች አሉ። ትልቁ ችግራችን ግን አንዱ እዛ ማዶ ሆኖ ሌላው ወዲህ ሆኖ ይጮሃል እንጂ አንደማመጥም። መንግስት ህዝብን ማዳመጥ አለበት፤ ህዝብም በተመሳሳይ መንግስትን ማድመጥ አለበት። እኔ የበለጠ አውቃለሁ ይህ ነገር የእኔ ብቻ ነው፤ በማለት ተወጥረናል ። ነገር ግን ጥፋቱም ልማቱም የጋራችን መሆኑን ማመን ላይ ግን ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው ያለው።
በመሆኑም የአንድነትን ጠቀሜታ በመረዳት ጥላቻን በማራቅ መደማመጥ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ የኢኮኖሚም የፖለቲካም የታሪክ ምሁራንም የየራሳቸውን ሀሳብ ይሰጣሉና ይህንን አቀናጅቶ በመጠቀም ወደትክክለኛው አቅጣጫ መሄድ ደግሞ የእኛ ፋንታ ነው።
ብዝኃነት በልዩነት ውስጥ ውበት መሆኑን ማመንና መቀበል አለብን ፤ በመሆኑም ይህንን ተቀብለን ወደፊት መሄድ ያስፈልጋል። እኔ የተሻልኩ ዜጋ ነኝ የሚለው የትም አያደርስም። በተለይ በቅርብ ጊዜ የምንሰማቸው አክቲቪስቶች ከዚህ አስተሳሰብ መውጣት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፦ስለዚህ በዓድዋም ይሁን በሌሎች የአብሮነት ጊዜያቶቻችን የነበረን አንድነት አሁን ላይ አለ ማለት ይቻላል?
ዶክተር ከተቦ፦ ለእኔ አሁንም አንድነቱ አለ እላለሁ፤ የተሸረሸረ ነገር ያለ አይመስለኝም። እነዚህ አክቲቪስቶች የታሪክ ባለሙያ ብላችሁ የምታቀርቧቸው ሰዎች በተቃራኒው አቅጣጫ እየሄዱ ነው። ግን እነሱ በሄዱበት አቅጣጫ ሁሉም ይሄዳል ማለት ደግሞ አይቻልም። አብሮ የሚጠፋ የለም። እዚህ ላይ እኛ በዚህ መልኩ እንበጣጠስ ካልን እኮ የውጪዎቹ እራት ነው የምንሆነው፤ በመሆኑም የአንድነት ታሪካችንን አጉልተን ወደፊት ነው መሄድ ያለብን ። አፍራሽ ሃሳቦች ይታያሉ ግን ደግሞ ይፈታሉ ብዩ አምናለሁ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከመሪዎች ከህዝቡ ከምሁራን ከጋዜጠኞች ብዙ ይጠበቃል። ስለዚህ ሁላችንም የራሳችንን ድርሻ የምንወጣ ከሆነ የሚታዩትን ምልክቶች ከወዲሁ በማስወገድ አንድነታችንን መጠበቅ እንችላለን ።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ አካላት እነሱ በሚያስቡት ወይም በሚፈልጉት መልኩ ነገሮች አልሄድ ሲላቸው ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማልና እውን ኢትዮጵያን በቀላሉ ማፍረስ ይቻላል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ከተቦ፦ ትልቁ ነገር እንደማመጥ ወደታችም እንውረድ ነው የምለው። ፖሊሲዎች መጽሐፍ ቅዱስ ወይም ቁርአን ስላይደሉ በየጊዜው መሻሻል ያስልጋቸዋል። እንደውም እነዚህ ፖሊሲዎች ህዝቡ ምን ይላል የሚለውን ይዘው መውጣት ያለባቸውም ይመስለኛል። እዚህ ላይ መንግስት ወይም ህዝቡ እኔ ብቻ አውቃለሁ፤ አንተ እኔ የምለውን ብቻ ትሰማኛለህ የሚለው ነገር አይሰራም። ሌላውን የፖለቲካ ሰዎች ቢመልሱት ይሻላል።
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ከተቦ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013