እስማኤል አረቦ
ከ125 ዓመት በፊት እንዲህ ሆነ፡፡ምኒልክም ሕዝቡን ለጦርነት ክተት አሉ። ታሪካዊው የአፄ ምኒልክ የክተት አዋጅ ነጋሪት እየተጎሰመ ተላለፈ። በጊዜው እንዲህ ተደምጧል፡፡ “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡
ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡
አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትልበ በሃዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።”
ጣሊያኖች በጄኔራል ባራቲዬሪ የሚመራውን 20 ሺህ ወታደሮቻቸውን ይዘው በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን ዓድዋን ወጉ። ከ80 ሺህ እስከ 120 ሺህ የሚገመተው የምኒልክ /የኢትዮጵያ ሠራዊትም/ በሚገባ ሲዋጋ የሀገሪቱ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥና ሀገሬን ብሎ በቁርጠኝነት ስሜት ቀፎው እንደተነካ ንብ የተነቃነቀው ኃይል የጠላትን ጦር አደናግጦ መግቢያ መውጫ በማሳጣት ቀኑን ሙሉ ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላ በሚያስደንቅ አኳኋን ድሉ የኢትዮጵያ ሆነ። ቅኝ አገዛዝ እግሬ አውጪኝ ሲል ነፃነት ከፍ አለ።
እንደ ኢትዮጵያዊያን ዘመን ቀመር በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ይህ ሆነ፡፡ አገር በወራሪ ጠላት ተደፈረች። ነፃነት የሚያሳጣ ሉዓላዊነትን የሚጥስ ባዕድ ድንበር ተሻግሮ በነፃነት ዘመናትን የተሻገረችውን አገር ኢትዮጵያን ተዳፈረ፡፡ ይሄኔ ደመ መራሩ ኢትዮጵያዊ ከያለበት ተጠራርቶ የአገሩን ሉዓላዊነት ለማስከበር ራሱን በመሰዋት አገር ለማቆየት ተመመ፡፡ በወቅቱ የነበረበትን የውስጥ ችግር ለይደር አቆይቶ አገሬን በሚል የአንድነት ስሜት ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል አመራ፡፡
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ካነገበውና ምስራቅ አፍሪካን በሙሉ በቅኝ ግዛቴ ስር አውላለሁ ካለው የኢጣሊያ ጦር ጋር የዚህች ታላቅ አገር ህዝብ በጀግንነት ተዋደቀ። ለነፃነትና ለአገር ባለው ጥልቅ ፍቅር ደሙን አፈሰሰ። ለሚወዳት አገሩ ምትክ የሌለው ራሱን ከፈለ፡፡ አገሩን ለመጠበቅ ክቡሩ የሰው ልጅ አጥንቱን ከሰከሰ፡፡ ሉዓላዊነቱ እንዳይነጠቅ ራሱን ያለ ስስት ለመስዋዕትነት ከፊት አሰለፈ፡፡
ዘንድሮም በ125ኛው የዓድዋ ድል በዓል የታየውም ኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር ስሜት ጥልቅ መሆኑንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎመራ እንደሚሄድ ነው፡፡ የዓድዋ ድል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። ከዚያም አልፎ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የዓድዋ በዓልን በድምቀት አክብረው ውለዋል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ‹‹በዓድዋ የተገኘው ድል በህዳሴው ግድብ ላይ ይደገማል›› በሚል መርህ አድዋን አክብረውት ውለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት እንደሚገልጹት የ125 ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በድምቀት ለማክበር መንግስት ኮሚቴ አቋቁሞ ሲንቀሳቀስ ቆየ ሲሆን የዲያስፖራው አባላትም ድሉን በያሉበት እንዲያከብሩት በትኩረት ተሰርቷል፡፡
በዚሁ መሰረትም እለቱ የዓድዋን ድል መሰረት ያደረጉ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽን እና የመዝናኛ ዝግጅቶችን በማድረግ ተከብሯል፡፡ይህ ደግሞ በዲያስፖራው ዘንድ ሀገራዊ ስሜት እንዲጎለበትና የእርስ በእርስ መቀራረብ እንዲኖር አስችሏል፡፡
በኮሎራዶ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ገ/መድህን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በኮሎዳሮ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለአለፉት አራት አመታት የዓድዋ ድል በአልን በድምቀት ሲያከብሩት የቆዩ ሲሆን የዘንድሮውን የ125ኛ የድል በዓል በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በኮሎራዶ ብቻ ከ40 ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ስለሆነ በርካቶቹ ዕለቱን በድምቀት ማክበራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከዕለቱ በፊት በነበሩት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የዲያስፖራው አባላትን በበይነ መረብ በማወያየት ዕለቱን የሚያጎሉና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መሰራታቸውንም አቶ ሳሙኤል ጠቁመዋል፡፡አቶ ሳሙኤል አክለው እንደገለጹትም፤ ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ቀን በመሆኑ በአሜሪካ ደረጃ ከሚከበረው የጥቁር ህዝቦች ወር ጋር የሚገጣጠም በመሆኑም ጭምር እለቱን ከኢትዮጵያውያን አልፎ ሌሎች አፍሪካውያንም እንዲያከብሩት የማስተሳሰር ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሶስት ሺህ እንደሚዘል ይነገራል፡፡ ይህ የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ በፖለቲካ ተጽእኖ፣ለትምህርት ወዘተ ሀገሩን ለቆ የወጣና ኑሮውንም በአውሮፓና አሜሪካ የመሰረተ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ እስካሁን በነበረው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና ልማት እንዲረጋገጥ ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡በተለይም የኢህአዴግ መንግስት የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶችንና አፈናዎችን በመቃወም የነበረው መንግስት በህዝብ አመጽ እንዲገረሰስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡
በዶክተር አብይ የሚመራው የለውጥ መንግስት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ የዲያስፖራው ተሳትፎ ከመቃወም በዘለለ በተለያዩ ልማቶች ላይ አሻራውን ወደ ማሳረፍ ተሸጋግሯል፡፡ለህዳሴ ግድብ፣ለገበታ ለሀገር፣ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍና በየጊዜው ለሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያለውን ገንዘብ በማዋጣትና በሀሳብና በዕውቀት በመደገፍ ሀገራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡በተለይም በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ያሳየው ሀገራዊ ተቆርቋሪነትና አለሁ ባይነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ከሀገሩ ቢወጣም ሀገሩ ግን ከልቡ አልወጣችም፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2013